ስፖርት፤ መስከረም 19 ቀን፣ 2011 ዓ.ም
ሰኞ፣ መስከረም 19 2012ትናንት የጀርመን መዲና በርሊን ከተማ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ደምቃ ነው ያመሸችው። መላ ዓለምን ባስደመመ መልኩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንዶች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው ገብተዋል። በሴቶችም አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃው ከኢትዮጵያውያን እጅ አልወጣም። በበርሊኑ ማራቶን አንደኛ በመውጣት ለድል የበቁትን አትሌቶች ከዛው ከበርሊን ከተማ አነጋግረናል። የዶሃ የዓለም የስፖርት ፉክክርን፤ የጀርመን ቡንደስሊጋ እና የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎችንም እንቃኛለን።
ብዙዎች «አንበሳ» የሚለውን ገላጭ ቃል ከስሙ ያስቀድማሉ፤ ስለ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሲናገሩ። እዚህ ጀርመን ደግሞ «እጅግ ልዩው ኮከብ» ሲሉ ያወድሱታል። በእርግጥም ትናንት በ46ኛው የበርሊን ማራቶን አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ልዩ ኮከብነቱን አስመስክሯል።
ከሦስት ወር በፊት ከገጠመው ኅመም አገግሞ በበርሊን ጎዳናዎች በፍጥነት የሮጠው ቀነኒሳ 42 ኪሎ ሜትሩን ሲያጠናቅቅ ሁለት ሰከንድ ብቻ በመዘግየቱ የዓለምን ክብር ወሰን ለጥቂት ሳይሰብር ቀርቷል፤ የአንደኛነቱን ክብር ግን ተጎናጽፏል። 2 ሰአት ከ1 ደቂቃ ከ41 ሰከንዶች ሮጦ የትናንቱን የበርሊን ማራቶን ያሸነፈው አትሌት ቀነኒሳ ከውድድሩ በኋላ በተለይ ለዶይቸ ቬለ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ ክብር ወሰን ለጥቂት ሳይሰብር በመቅረቱ መቆጨቱን ገልጧል። ግን ደግሞ ወደ ውድድሩ የገባው ለክብር ወሰን ሳይሆን በውድድሩ አሸናፊ ለመኾን እንደነበር ተናግሯል። ትናንት በውድድሩ ስፍራ የነበረው የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል ከውድድሩ በኋላ አነጋግሮታል።
«በውነቱ ክብረወሰን እሰብራለሁ የሚል ግምት አልነበረኝም ዛሬ። ምክንያቱም የዛሬ ሦስት ወር ታምሜ ነበር፤ እናም እሱን ለመታከም አውሮጳ የተወሰኑ ወራት ቆይቼ ነበር። በዚህ ውድድር ላይ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እና ጥሩ ከዚህ በፊት ከነበረኝ የተሻለ የግል ሰአት ለመሮጥ ነበር፤ ግን መቶ በመቶ ክብር ወሰንን ግብ አድርጌ አልመጣሁም። ምክንያቱም ዝግጅቱም ትንሽ ጊዜ ነው፤ ከኅመም [አገግሜ] ነው የመጣሁት። ከእዛ አንጻር ምናልባት እንደሰው ሊሰማኝ ይችላል። ማራቶን ላይ በሁለት፤ ሦስት ሰከንድ ክብር ወሰን ከመስበር ውጪ መኾን ትንሽ ያው ያማል። ግን ይኼ ለወደፊቱ የበለጠ እንድሠራ ያበረታታኛል እንጂ ሞራሌን አይነካም። ምክንያቱም እንደማደርገው ያው አቅሙ አለኝ፤ ያንን ደግሞ ማንም ሰው ያውቃል። በማራቶን የተገመተውን እንዳላስመዘገብኩ ማንም ሰው ያውቃል። ስለዚህ ይኼ አሁን ያገነሁት ውጤት ለወደፊት ትልቅ ሞራል እና የተሻለ ሠርቼ የተሻለ ሰአት ማስመዝገብ እንደምችል ተስፋ የሰጠኝ ነው።»
ቀነኒሳ በውድድሩ 30 ኪሎ ሜትር አካባቢ በተሰማው የጡንቻ መሸማቀቅ ኅመም የተነሳ የሩጫ ፍጥነቱን ጋብ አድርጎ ኅመሙ መለስ ብሎ ሲቀንስለት ፍጥነቱን መጨመሩን አክሎ ተናግሯል። በኅመሙ የተነሳ ወደ ኋላ ቢቀርም በስተመጨረሻ ግን ሌሎች ሯጮች ላይ ሊደርስባቸው እንደሚችል «በውስጡ እምነት» እንደነበረው፤ ተስፋ መቁረጥ እንደማይገባውም ከራሱ ጋር እየተነጋገረ ይሮጥ እንደነበር ገልጧል።
ለቀጣዩ የቶኪዮ ኦሎምፒክ መሮጥ እንደሚፈልግ ኾኖም ገና ውድድሮች እንደሚቀሩ፤ ብዙ አትሌቶችም ስላሉ የሁሉም ዕድል መታየት እንዳለበት ተናግሯል። ወቅታዊ ብቃት እና ሰአት ከግምት ውስጥ ስለሚገባም ወደፊት ያ ታይቶ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚመረጥ ከኾነ «ደስ እንደሚለው፤ ካልኾነም ሌሎች ውድድሮች» ስላሉ እነሱ ላይ «እታየለሁ ብዬ እገምታለሁ» ሲል ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረገው ቃለ-መጠይቅ ገልጧል።
በትናንትናው ዕለት በሴቶች የማራቶን ፉክክር የአንደኛነት ደረጃን የተጎናጸፈችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት አሸቴ በከሬ በአንደኛነት በማጠናቀቋ ደስታዋን ገልጣለች። በውድድሩ መሀል 30 ኪሎ ሜትር አካባቢ ፍጥነቷን የምትቆጣጠርበት የእጅ ሰአቷ መሥራት በመቆሙ አፈትልካ መውጣት አለመቻሏን ተናግራለች።
በትናንቱ የበርሊን ማራቶን የሩጫ ውድድር ቀነኒሳን ተከትለው ብርሃኑ ለገሰ እና ሲሳይ ለማ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል። በሴቶች የማራቶን ፉክክር አትሌት አሸቴ በከሪ አንደኛ፤ ኢትዮጵያዊትዋ አትሌት ማሬ ዲባባ ሁለተኛ፣ ኬንያዊትዋ አትሌት ሳሌ ቼፒጎ ሦስተኛ ሆነዉ አጠናቀዋል። ለጀርመን የምትሮጠው ትውልደ-ኢትዮጵያዊቷ ጀርመናዊ አትሌት ሜላት ይሣቅ ስድስተኛ ወጥታለች።
በሌላ የአትሌቲክስ ውድድር፦ የዓለም አትሌትኪስ ፌደሬሽኖች ማኅበር (IAAF) የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር በካታር ዶሃ መደረጉ እያወዛገበ ነው። ወትሮም የሀገሪቱ የሙቀት መጠን እንዲሁም የሙስና ጉዳዮች አሳሳቢ ነው የተባለባት ካታር ውድድሩ ከተጀመረ በኋላ መጠነ ሰፊ ትችት እየደረሰባት ነው።
የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር በካታር መካሄዱ ትክክል አልነበረም፤ የማራቶን ሯጮችም በሙቀቱ የተነሳ ሕይወታቸው ሊያልፍ ይችል ነበር ሲል የቀድሞው የማራቶን የዓለም ክብር ወሰን ባለቤት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ለአሶሲየትድ ፕሬስ መናገሩን የዜና ምንጩ ዛሬ ዘግቧል። ያለፈው ዐርብ የተጀመረው የዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር የሚጠናቀቀው የፊታችን እሁድ ሲኾን፤ በቅዳሜው የማራቶን ውድድር የተሳተፉ ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ውድድሩ እኩለ ሌሊት ላይ ቢከናወንም እጅግ ሞቃታማና ወበቃማ በመኾኑ ውድድራቸውን ሊያጠናቅቁ አልቻሉም። ሙቀቱ 40 ዲግሪ ሴልሲየስ አካባቢ ነበር ተብሏል። በሙቀቱ የተነሳ 68 ሴት አትሌቶች ውድድሩን ሲያቍርጡ፤ ለ30 አትሌቶች ሕክምና አገልግሎት ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት የነበረው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ «በእንዲህ ያለ የአየር ኹኔታ ሰዎች እኮ ሊሞቱ ይችላሉ» ሲል ስጋቱን ገልጧል። የዓለም አትሌትኪስ ፌደሬሽኖች ማኅበር የዶሃው ውድድር እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1991 ቶክዮ እንዲሁም በ2013 ሞስኮው ውስጥ በተደረገው ውድድር ወቅት ከነበረው የአየር ኹኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው ሲል ውድድሩ ካታር ውስጥ መዘጋጀቱን ትክክል አይደለም የሚለውን ተከላክሏል። በዘንድሮው የዶሃ ማራቶን ኬንያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲች አሸናፊ ኾናለች። የወንዶች የዶሃ ማራቶን የፊታችን እሁድ ሊከናወን ቀጠሮ ተይዞለታል።
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ከመሪዎቹ መካከል ባየር ሙይንሽን ብቻ ተሳክቶለታል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ አቻ ሲለያይ ላይፕሲሽ ሽንፈት ቀምሷል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከቬርደር ብሬመን ጋር ባደረገው የቅዳሜው ግጥሚያ በገዛ ሜዳው ሁለት እኩል አቻ በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። ላይፕሲሽ በሻልከ የ3 ለ1 ሽንፈት ደርሶበት ከደረጃው አሽቆልቁሏል። ባየር ሙይንሽን ግን ዘንድሮ ወደ ቡንደስሊጋው ያደገው ፓዴርቦርንን 3 ለ2 አሸንፏል። በእርግጥ ከታች ያደገ ቡድን ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ላይ 2 ግብ ማስቆጠሩ አነጋጋሪ ቢኾንም ባየር ሙይንሽን በ14 ነጥብ የመሪነቱን ስፍራ እንዲቆናጠጥ አስችሎታል። ላይፕሲሽ በ13 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ሲገኝ፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ 11 ነጥብ ይዞ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ደግሞ ዘንድሮ የዓለማችን ምርጡ አሰልጣኝ የሚል ክብር የተጎናጸፉት ጀርመናዊው አሰልጣኝ የሚመሩት ሊቨርፑል በመሪነቱ እየገሰገሰ ነው። እስካሁን በተከናወኑ ግጥሚያዎች ጀርመናዊው አሰልጣኝ አንድም ጊዜ የሚረታቸው አሰልጣኝ አልተገኘም። ቅዳሜ ዕለት ሼፊልድ ዩናይትድን 1 ለ0 ድል ያደረገው ሊቨርፑል 21 ነጥብ ይዞ በፕሬሚየር ሊጉ በመሪነት ተቆናጧል። ከትናንት በስትያ ኤቨርተንን 3 ለ1 ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ ከሊቨርፑል በ5 ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተላል። ላይስተር ሲቲ 14 ነጥብ ይዞ በሦስተና ደረጃ ላይ ይገኛል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ