1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት መጋቢት 12 ቀን፤ 2008 ዓ.ም.

ሰኞ፣ መጋቢት 12 2008

ኢትዮጵያ በዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድር ዩናይትድ ስቴትስን ተከትላ ከዓለም ሁለተኛ፤ ከአፍሪቃ አንደኛ ወጥታለች። ኬንያ ዘንድሮ በ25ኛ ነው ያጠናቀቀችው፤ ጀርመን 12 ደረጃ ይዛለች።

https://p.dw.com/p/1IHBj
China Beijing 2015 IAAF Weltmeisterschaft Genzebe Dibaba
ምስል picture-alliance/dpa/S. Suki

ማንቸስተር ዩናይትድ በወጣቱ አጥቂው ማንቸስተር ሲቲን አሸንፎዋል። ሊቨርፑል እየመራ ቆይቶ በመሸነፉ ወደ ላይ የመውጣት እድሉን አጥብቧል። በላሊጋው መሪው ባርሴሎና ነጥብ ሲጥል ሪያል ማድሪድ በሰፋ ልዩነት አሸንፏል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ግስጋሴውን ቀጥሏል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ግን እየተጠጋው ነው።

ፖርትላንድ፤ ኦሬገን፤ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተከናወነው የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያ ከኃያላኑ ልቃ ከፊት ተሰልፋለች። ኢትዮጵያ አስተናጋጇ ሀገር ዩናይትድ ስቴትስን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃን መቀዳጀት ችላለች። በውድድሩ ኢትዮጵያ አምስት ሜዳሊያዎችን ነው ያገኘችው። በወንዶች እና በሴቶች የ3000 ሜትር የሩጫ ፉክክር፤ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና ገንዘቤ ዲባባ ለኢትዮጵያ ወርቅ አስገኝተዋል። መሠረት ደፋር በገንዘቤ ዲባባ ተበልጣ ሁለተኛ በመውጣት ለሀገሯ ብር ማስገኘት ችላለች። ለኢትዮጵያ ሌላኛው ብር እና ነሐስ ሜዳሊያ የተገኘው በ1500 ሜትር የሴቶች የሩጫ ፉክክር በዳዊት ሥዩም እና በጉዳፍ ጸጋዬ ነው። አክሱማዊት እምባዬ በዚሁ ውድድር አራተኛ ወጥታለች።

ኢትዮጵያን ተከትላ ከአፍሪቃ እስከ 25ኛ ደረጃ ድረስ መግባት የቻለችው ብቸኛ አገር ቡሩንዲ ብቻ ናት። ቡሩንዲ በአንድ ወርቅ እና አንድ ብር የ5ኛ ደረጃ ማግኘት ችላለች። የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ዋነኛ ተፎካካሪ ኬንያ በሁለት ነሐስ ተወስና፤ ደካማ በሆነ መልኩ በ25ኛ ደረጃ አጠናቃለች። ኢትዮጵያ ደረጃዋ በዋናነት ከፍ ሊል የቻለው በ3000 ሜትር በተቀዳጀችው ድል ነው። ይህ በተደጋጋሚ ያስገኘችው ድል እንዲጠበቅ መትጋቱ ሊቀጥል ይገባል። ሆኖም እንደ 800 እና 1500 ሜትር ባሉ የአጭር እና መካከለኛ ርቀት ውድድሮች ላይ ግን ፌዴሬሽኑ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል።

በፖርትላንዱ የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ፉክክር ጀርመን በ2 ብር እና በአንድ ነሐስ ብቻ፤ ያለምንም ወርቅ ከኢትዮጵያ በ12 ደረጃ ዝቅ ብላ በ14ኛ ወጥታለች። አጠቃላይ ውድድሩን በ13 የወርቅ፤ በ6 የብር እና በ 4 የነሐስ በድምሩ በ23 ሜዳሊያዎች ያሸነፈችው ዩናይትድ ስቴትስ ናት።

በርካታ የመገናኛ አውታሮች ኢትዮጵያ ያገኘችውን ድል ሲያወድሱ የሰሞኑ የዶፒንግ ጥርጣሬን ሲያነሱ ተስተውሏል። ሁኔታው በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት የረዥም ጊዜ ክብር ላይ ጥላ ማጥላቱ አልቀረም።

በኃይል ሰጪ መድኃኒት ማላትም ዶፒንግ ውዝግብ የተነሳ ሩስያ ዘንድሮ በፖርትላንዱ የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር አልተሳተፈችም። የሚጠበቅባትን አላሟላችም በሚል የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ሩስያን ከውድድሩ ማገዱ ይታወሳል። የፖርትላንዱ የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ውድድር የተከናወነው ከሐሙስ፤ መጋቢት 8 እስከ እሁድ፤ መጋቢት 11 ድረስ ነበር።

ቻይና ውስጥ ትናንት በተከናወነው የውሺ ማራቶን የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያ በወንዶችም በሴቶችም አሸናፊ ሆናለች። በወንዶች ታደሠ ያዬ ዳቢ 2:15:24 በማጠናቀቅ አንደኛ ወጥቷል። የኬንያዎቹ ሂላሪ ኪፕጎጊ እና ላባን ኪፕኬሞይ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል። በሴቶች ተመሳሳይ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ የሹሜ አያሌው እጅጉ 2:42:06 በመግባት በአንደኛነት አጠናቃለች። እሷንም ተከትለው የገቡት ሁለት ኬንያውያት ናቸው፤ ናዖሚ ንዱታ እና ሮዛሊን ዴቪድ።

በአፍሪቃ የእግር ኳስ ቡድኖች የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጎስ በኮንጎ ዲሞክራሲዊ ሪፐብሊኩ ቱ ፕዊሳ ማዜምቤ ትናንት አንድ ለባዶ ተሸንፏል። ባለፈው ሣምንት ባሕርዳር ውስጥ በደጋፊው ፊት ሁለት እኩል የወጣው ቅዱስ ጊዮርጎስ በፈረንሣዊው አሠልጣኝ ሑበርት ቬሉድ ከሚመራው ቱ ፕዊሳ ማዜምቤ ጋር የመልስ ጨዋታውን ያከናወነው ሉቡምባሺ፤ ኮንጎ ዲሞክራሲዊ ሪፐብሊክ ውስጥ ነበር። በአጠቃላይ የደርሶ መልስ ውጤት ቱ ፕዊሳ ማዜምቤ ማለትም ኃያሉ ማዜምቤ በ3 ለ2 አጠቃላይ ድምር አላፊ ኾኗል።

ኃያሉ ማዜምቤ ዘንድሮም ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ አሸናፊ ሆኖ ዋንጫውን ለመውሰድ ቆርጦ መነሳቱን ገልጧል። በሚያዝያ ወር ላይ ከሞሮኮው የቀድሞው ባለድል ዊዳድ ካዛብላንካ ጋር ይፋለማል። በነገራችን ላይ ሌላኛው የካዛብላንካው ጠንካራ ቡድን ራያ ካዛብላንካ ትናንት ከቻባ ሆቻይሞ ጋር በነበረው ጨዋታ ሥርዓት አልበኛ ደጋፊዎች በፈጠሩት ብጥብጥ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ፤ 54ቱ መቁሰላቸው ተነግሯል። ሥርዓት አልበኛ ደጋፊዎቹ አንደኛው ወገን ወደ ሌላኛው ርችቶችን በመተኮስ የሞሐማድ አምስተኛ የእግር ኳስ ሜዳን በከፊል መጉዳታቸው ተገልጧል። ከሜዳው ውጪ የነበሩ 11 ተሽከርካሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። 30 ያኽል ደጋፊዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። የግጭቱ መንሥዔ የእግር ኳስ ቡድኖቹ የቆየ ባላንጣነት የፈጠረው ብቻ ይሁን ሌላ ሰበብ ይኑረው ግልጽ የሆነ ነገር የለም።

Africa Cup Fans
ምስል P. Pabandji/AFP/Getty Images
Symbolbild Leichtathletik Laufen
ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ በማርኩስ ራሽፎርድ የተነሳ የማንቸስተር ዩናይትድ የትናንትና ድል የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል። የኦልትራፎርድ አዲስ ኮከብ ማርኩስ ራሽፎርድ የዋይኔ ሩኒን ክብርወሠን መስበር ችሏል። በማንቸስተር ዩናይትድ የማንቸስተር ሲቲ ግጥሚያ ታሪክ በእድሜ አነስ ብሎ ግብ በማስቆጠር ዋይኔ ሩኒን የሚስተካከል አልነበረም። አሁን ግን ማርኩስ ራሽፎርድ የዋይኔ ሩኒን ቦታ ተረክቧል። የ18 ዓመቱ ወጣት ማርኩስ ራሽፎርድ በማንቸስተር ሲቲ ሜዳ ላይ ያስቆጠራት ብቸና ግብ ቡድኑን አሸናፊ አድርጋለች። ግቧ የተቆጠረችው በ16ኛው ደቂቃ ላይ ነበር።

ዋይኔ ሩኒ ማንቸስተር ሲቲ ላይ ግብ ሲያስቆጥር የ19 ዓመት ወጣት ነበር። የማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ሉዊ ቫን ጋል ወጣቱ አጥቂ ማርኩስ ራሽፎርድን «የምር አጥቂ» ሲሉ አወድሰውታል። «ወድጄዋለሁ ግን ገና 18 ዓመቱ ነው፤ ስለዚህ ይኽ ብቃቱ በዚሁ ይቀጥል እንደሆነ ለማየት መጠበቅ አለብን» ሲሉ አክለዋል።

ማንቸስተር ዩናይትድ በዌስትሐም ዩናትድ የሚበለጠው በግብ ክፍያ ብቻ ነው፤ ሁለቱም 50 ነጥብ አላቸው። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀራቸዋል። ዌስትሐም ዩናይትድ 4ኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው በማንቸስተር ሲቲ በአንድ ነጥብ ይበለጣል። አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዌስትሐም ዩናትድ ከቸልሲ ጋር ቅዳሜ እለት ሁለት እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። ቸልሲ በሊቨርፑል በሦስት ነጥብ ተበልጦ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። እሱም አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል።

ቶትንሀም በርመስን 3 ለ0 በማሸነፍ ነጥቡን 61 አድርሷል። ክሪስታል ፓላስን 1 ለ0 ካሸነፈው ከመሪው ላይሰስተር ሲቲ ጋር የ5 ነጥብ ልዩነት ነው ያላቸው። በሦስተኛ ደረጃ ላይ 55 ነጥብ ያለው አርሰናል ኤቨርተንን 2 ለ0 ድል አድርጓል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። ትናንት ኒውካስል እና ሰንደርላን አንድ እኩል ወጥተዋል። ሊቨርፑል በኮቲንሆ ድንቅ ግብ እና በዳንኤል ስቱሪጅ ሁለተኛ ግብ ሳውዝሐምፕተንን ሲመራ ቆይቶ የማታ ማታ 3 ለ0 ተሸንፎ ወጥቷል። 9ኛ ደረጃውም 44 ነጥቡም እዛው ባለበት ተወስኗል። ሊቨርፑል ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ይቀሩታል። ተመሳሳይ ነጥብ የነበረው ሳውዝሐምፕተን አሁን በ47 ነጥብ 7 ደረጃ ላይ ይገኛል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ኮለኝን 1 ለ0 አሸንፎ ነጥቡን 69 አድርሷል። አውስቡርግን 3 ለ1 ድል ያደረገው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ5 ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተለዋል። ትናንት ሽቱጋርት በባየር ሌቨርኩሰን 2 ለባዶ ተሸንፏል። አይንትራኅት ፍራንክፉርት ሐኖቨርን 1 ለ0 ድል አድርጎ እዛው የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ አስቀርቶታል።

Fußball Bundesliga Bayer Leverkusen vs VfB Stuttgart
ምስል Getty Images/A.Grimm
Großbritannien Europa League, FC Liverpool - Manchester United
ምስል Reuters/C. Recine

በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድ ሴቪላን ትናንት 4 ለባዶ በማንኮታኮት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት በ3 ዝቅ ማድረግ ችሏል። ጋሬት ቤል፤ ካሪም ቤንዜማ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶን አንድ ላይ ማሰለፍ የተሳካለት አሠልጣኝ ዚነዲን ዚዳን ተጨዋቾቼን ገና ምን አያችኋቸው ብሏል። አትሌቲኮ ማድሪድ በመሪው ባርሴሎና በ9 ነጥብ የሚበለጠው 67 ነጥብ አለው። ባርሴሎና ከቪላሪያል ጋር 2 እኩል አቻ ወጥቷል። ከቪላሪያል 54 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የዓለም ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ባለድሉ ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች ካናዳዊው ሚሎ ራዎኒክን በኢንዲያን ዌልስ ግጥሚያ ትናንት ካሊፎርኒያ ውስጥ 6-2 6-0 አሸንፎታል። «በርካታ ተመልካቾች በወንዶች የሜዳ ቴኒስ ላይ ስለሚታደሙ፤ የበለጠ ሊከፈለን ይገባል» ሲል ተደምጧል። ለዚህም የቴኒስ ፕሮፌሽናሎች ማኅበር ከፍተኛ ትግል ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስቧል።

የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ላይ የሙስና ቅሌት ማንዣበቡ ለቻይና ባለሀብቶች እንደጠቀመ አንድ የቻይና ባለ ሀብት ተናግረዋል። ዋንግ ጂያንሊን የተባሉት ባለሀብት ግዙፍ ኩባንያዎች ከፊፋ ጋር የማስታወቂያ ትብብር ማድረጋቸውን በማቋረጣቸው የቻይና ባለሀብቶች ዕድሉን በመጠቀም የማስታወቂያ ግዱ ውስጥ ገብተዋል ብለዋል። የ61 ዓመቱ ቻይናዊ ቢሊየነር «ከሁለት እና ሦስት ዓመታት በፊት የቻይና እና የእስያ ኩባንያዎች ብንፈልግም የፊፋ ስፖንሰር መሆን አንችልም ነበር፤ ጥቂት የምዕራቡ ዓለም ኩባንያዎች በመውጣታቸው ግን የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን ችለናል » ሲሉ ተደምጠዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ