ስፖርት፤ መጋቢት 17 ቀን፣ 2010 ዓ.ም
ሰኞ፣ መጋቢት 17 2010ዑራጓይ እና ዌልስ በቻይና ካፕ ዋንጫ ፍጻሜ ዛሬ ተፋልመዋል። የሪያል ማድሪዱ ጋሬት ቤል የሚገኝበት የዌልስ ንን የሚያሰለጥነው ሪን ጊግስ ምኞቱ አልሰመረም። በአንጻሩ የባርሴሎናው የግብ አዳኝ ሉዊስ ሱዋሬዝ ከሀገሩ የዑራጓይ ልጆች ጋር ፈንጥዟል። ፎርሙላ አንድ የመጀመሪያ ዙር ውድድር የኮምፒውተር ስህተት የዓለማችን ምርጥ የመኪና ሽቅድምድም አሽከርካሪን ለሽንፈት ዳርጓል።
ቻይና ናኒንግ ውስጥ ዛሬ ከሰአት በኋላ በተከናወነው የቻይና ዋንጫ ፍጻሜ ኡራጓይ ብዙ ጓጉታ የነበረችው ዌልስን አንድ ለዜሮ ድል አድርጋ ዋንጫውን ዘንድሮም የደቡብ አሜሪካ አድርጋለች። በዛሬው የፍጻሜ ጨዋታ የፓሪስ ሴን ጀርሜኑ አጥቂ ኤዲሰን ካቫኒ በ49ኛው ደቂቃ ላይ ከክሪስቲያን ሮድሪጌዝ የተላከለትን ኳስ በተረጋጋ ኹናቴ ከመረብ አሳርፏል። በብሔራዊ ቡድኑም 42ኛ ግቡ ኾኖ ተመዝግቦለታል።
የባለፈውን ዓመት እና የመጀመሪያ ዙሩን የቻይና ካፕ እግር ኳስ ዋንጫ ድል ያደረገችው ሌላኛዋ የደቡብ አሜሪካ ቡድን ቺሊ ነበረች። ዛሬ ለሦስተኛ ደረጃ በተደረገው ጨዋታ ቀደም ሲል በዌልስ 6 ለ0 ከባድ ሽንፈት ደርሶባት የነበረችው አዘጋጇ ቻይና በቼክ ሪፐብሊክ 4 ለ1 ተሸንፋለች። በቻይና ካፕ ከተሰለፉ አራት ቡድኖች መካከል ለዘንድሮ የሩስያ የዓለም ዋንጫ ያለፈችው ብቸኛ ሀገር ዑራጓይ ነች። ዛሬ በዑራጓይ ድል አድራጊነት የተጠናቀቀው የቻይና ካፕ ሐሙስ ዕለት ነበር የጀመረው።
የ28 ዓመቱ የዌልስ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ጋሬት ቤል ለሀገሩ ተሰልፎ ዋንጫ ማሸነፍ ከምንም በላይ የሚመኘነው ነገር እንደነበር ከጨዋታው አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። «የዋንጫ ጨዋታ ማሸነፍ ደስ ይላል፤ ግን ለሀገርህ ሲኾን የበለጠ ለየት ያለ ነገር ነው» ያለው ቤል ምኞቱ አልተሳካለትም። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በአብዛኛው በመከላከል ላይ አተኩሮ የነበረው የዌልስ ቡድን በኹለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ማጥቃቱ ላይ ባዘነበለው ለራጓይ ቡድን እጅ ሰጥቷል።
የዓለም ዋንጫ የወዳጅነት ጨዋታዎች ዛሬ ማታም ይከናወናሉ። ፖርቹጋል ከኔዘርላንድ ኖርዌይ ከአልባንያ፤ ማልታ ከፊንላንድ እንዲሁም ቡልጋሪያ ከካዛክስታን ይጫወታሉ። ሰኔ ወር ላይ ለሚጀምረው የዓለም ዋንጫ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ጠንካራ ፉክክር እንደሚጠብቀው ተገልጧል። የጀርመን ቡድን ከሜክሲኮ ፣ ከስዊድን እና ደቡብ ኮሪያ ጋር ነው የተደለደለው።
የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ
በዓለም ዋንጫ የወዳጅነት ጨዋታዎች ተቋርጦ የነበረው የፕሬሚየር ሊጉ ጨዋታ የፊታችን ቅዳሜ ዳግም ይጀምራል። ቅዳሜ ከሰአት በኋላ ሊቨርፑል ከክሪስታል ፓላስ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ የሚንደረደረው የፕሬሚየር ሊግ በአጠቃላይ ስምንት ጨዋታዎች ይስተናገዱበታል። በበነጋታው እሁድ ደግሞ አርሰናል ከስቶክ ሲቲ እንዲሁም ቸልሲ ከቶትንሀም ይጋጠማሉ።
በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ሥልጠና፦ ፍጥነት እና ጉልበት ወይንስ ተጠጋግቶ የመጫወት ቴክኒክ የሚለው ክርክር የቆየ ነው። የስፖርት ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ «በመጠጋጋት መጫወት» የሚል የስልጠና ዘይቤ አለው። ክርክሩ እንዳለ ኾኖ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአንድ ጎልማሳ እድሜ ያኽል ካስቆጠረ በኋላ ለአፍሪቃ ዋንጫ ያለፈው በቅርቡ ነበር። ብሔራዊ ቡድኑ በአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው መሪነት በ29ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ለመሳተፍ የበቃው ለ31 ዓመታት ከተሳትፎ ውጭ ከኾነ በኋላ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ያም ብቻ አይደለም ብሔራዊ ቡድኑ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያም ደርሶ ነበር። ጋዜጠኛ ገነነ ለፍጥነት እና ጉልበት ሠርተን ውጤት ካላገኘን ወደ ቴክኒኩ መዞር አለብን ይላል። ለዚሁ የአሰለጣጠን ስልት የሚኾን የሥልጠና መተግበሪያ ማኑዋል እንዳዘጋጀም ተገልጧል።
አትሌቲክስ
በ23ኛው የዓለም አገር አቋራጭ የአትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያ በአንደኝነት አጠናቃለች። ስፔን ቫሌንሺያ ውስጥ ቅዳሜ እለት በተከናወነው የግማሽ ማራቶን ውድድር አትሌት ነፃነት ጉደታ በኬንያዊት አትሌት ከዐሥር ዓመት በላይ ተይዞ የቆየውን ክብር ወሰን ማሻሻል ችላለች። አትሌት ነፃነት ክብር ወሰን ሠብራ አሸናፊ የኾነችው አንድ ሰአት ከስድስት ደቂቃ ከ11 ሰከንዶች በመሮጥ ነው። በውድድሩ ነጻነት ከኬንያዊቷ ጆይስሊን ቼፕኮስጌ በ43 ሰከንዶች ቀድማ ነው የገባቸው።
ባለፉት ኹለት ዓመታት የተከናወኑ ውድድሮች ላይ አሸናፊ የነበሩት ኬንያውያን ነበሩ። የውድድሩ ክብር ወሰን ለ11 ዓመታት ተይዞ የቆየውም በትውልደ ኬንያ ኔዘርላንዳዊዊቷ አትሌት ሎርናህ ኪፕላጋት ነበር። ኪፕላጋት ክብር ወሰኑን ለሰበረችው ኢትዮጵያዊት አትሌት ነጻነት በትዊተር መልእክቷ እንኳን ደስ ያለሽ ብላታለች።
«የእኔን የዓለም ክብር-ወሰን በ15 ሰከንዶች በመስበርሽ እንኳን ደስ ያለሽ! 11 ዓመታት ፈጅቷል ኾኖም አኹን አዲስ ክብር ወሰን ስላለን ደስተኛ ነን። ክብር-ወሰንን የግል ማድረግ አይቻልም፤ ለተወሰነ ጊዜ ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንጂ።» ብላለች።
በቅዳሜው 23ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ውድድር ሌላኛዋ ኬኒያዊት ፓውሊን ካሙሉ ሦስተኛ ወጥታለች። በወንዶች ተመሳሳይ ውድድር ኬኒያዊው ጄኦፍሪ ካምዎሮር በአንድ ሰአት ከኹለት ሰከንድ አንደኛ ሲወጣ፤ የብሪታንያው ሯጭ አብራሃም ቼሮቤን ከ20 ሰከንዶች በኋላ ኹለተኛ ወጥቷል። የኤርትራው አሮን ክፍሌ በአንድ ሰአት ከሰላሳ አንድ ሰከንድ በሦስተኛነት አጠናቋል።
ኢትዮጵያ ነፃነት ካስገኘችው ወርቅ በተጨማሪ በቡድን በሴቶችም በወንዶችም ኹለት የወርቅ ሜዳሊያዎች አግኝታለች። በድምሩ በአጠቃላይ ሦስት የወርቅ ሜዳልያዎችን በማግኘት ከዓለምም ከአፍሪቃም 1ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቃለች፡፡ ኬንያ በሦስት የብር ሜዳሊያ ኹለተኛ እንዲሁምባሕሪን በአንድ የብር እና በሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎች ሦስተኛ ወጥታለች። አንድ የነሐስ ሜዳሊያ ያገኘችው ኤርትራ በአራተኛነት አጠናቃለች።
የመኪና ሽቅድምድም
በአውስትራሊያ ግራንድ ፕሪ የመጀመሪያ ዙር የዘንድሮ የመኪና ሽቅድምድም ውድድር ጀርመናዊው የፌራሪ አሽከርካሪ ሠባስቲያን ፌትል ትናንት ለሊት ለዛሬ አጥቢያ አሸነፊ ኾነ። በዓለም የመኪና ሽቅድምድም ፉክክር ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ ዋንጫውን በእጁ ያስገባል ተብሎ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው የብሪታንያው ተወዳዳሪ ሌዊስ ሐሚልተን ከተሽከርካሪው ጋር የተገናኘው ኮምፒውተር መረጃዎችን በማዛባቱ የተነሳ በመጀመሪያ ዙር ውድድሩ ኹለተኛ ወጥቷል። ስለ መወዳደሪያ ተሽከርካሪዎች የውድድር ብቃት ለመናገር ጊዜው አኹን አይደለም ብሏል።
«ውድድሩ አራተኛ ዙር እስኪደርስ ድረስ ብዙ ማለት አይቻልም» ሲል አክሏል። በርካቶች በጉጉት ሲጠብቁት በነበረው በዚህ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የመጀመሪያ ዙር ፉክክር ጀርመን ውስጥ RTL በተሰኘው የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ 2,58 ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል። ባለፈው ዓመት የመክፈቻ ውድድሩን የተመለከተው ሰው ቁጥር 2,27 ነበር።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
ነጋሽ መሐመድ