1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ሚያዝያ  14 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ ሚያዝያ 14 2011

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ የዋንጫ ትንቅንቃቸው ተጠናክሯል። ኹለቱ ቡድኖች የደረጃ ሰንጠረዡን ተራ በተራ በበላይነት እየተፈራረቁበት ነው። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ በሳምንቱ ማሳረጊያ በግብ የተንበሸበሸው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከኃያሉ ባየር ሙይንሽን  ጋር ያለው ልዩነት የአንድ ነጥብ ብቻ ነው።

https://p.dw.com/p/3HEMH
1. Bundesliga | SC Freiburg - Borussia Dortmund | Torjubel (0:3)
ምስል picture-alliance/dpa/S. Gollnow

ሳምንታዊ የስፖርት ዘገባ 14.08.2011

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ የዋንጫ ትንቅንቃቸው ተጠናክሯል። ኹለቱ ቡድኖች የደረጃ ሰንጠረዡን ተራ በተራ በበላይነት እየተፈራረቁበት ነው። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ በሳምንቱ ማሳረጊያ በግብ የተንበሸበሸው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከኃያሉ ባየር ሙይንሽን  ጋር ያለው ልዩነት የአንድ ነጥብ ብቻ ነው። በላሊጋው መሪው ባርሴሎና እና በ2 ነጥብ ልዩነት የሚከተለው አትሌቲኮ ማድሪድ ዳግም ድል ቀንቷቸዋል። የኦሎምፒክ ባለድሉ ኬንያዊ አትሌት አስቤል ኪፕሮፕ የተከለከለ ኃይል ሰጪ ንጥረ-ነገር ተጠቅመሀል በሚል የአራት ዓመት እገዳ ተጥሎበታል። 

በጀርመናዊው አሰልጣኝ ቶማስ ቱኅል የሚሰለጥነው ፓሪ ሳንጀርሜን በፈረንሳይ የመጀመሪያ ሊግ ውድድር ከወዲሁ የዋንጫው ባለድል መኾኑን አረጋገጠ። የውድድር ዘመኑ ሊጠናቀቅ 5 ጨዋታዎች እየቀሩ ነው ፓሪ ሳንጀርሜን  84 ነጥብ  ይዞ ከወዲሁ ዋንጫውን ገቢ ማድረጉን ያረጋገጠው። ትናንት ከቱሉዝ ጋር ተጋጥሞ ያለምንም ግብ የተለያየው ሊሌ ኦሊምፒክ ስፖርቲንግ ቡድን 65 ነጥብ ይዞ በኹለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት ሞናኮን 3 ለ1 ድል ያደረገው ፓሪ ሳንጀርሜን አሰልጣኝ ጀርመናዊው ቶማስ ቱኅል ከእንግዲህ በነጥብ ማንም የማይደርስባቸው በመኾኑ በፈረንሳይ ሊግ የመጀመሪያ ዋንጫቸውን ይወስዳሉ ማለት ነው።

ሌላኛው ጀርመናዊ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቡድናቸውን ከሦስት ዐሥርተ-ዓመታት ወዲህ የዋንጫ ባለቤት ለማድረግ ከጫፍ ተጠግተዋል። የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ትናንት እጅግ በሰፋ የጨዋታ ብልጫ ካርዲፍ ሲቲን 2 ለ0 ድል በማድረግ በደረጃ ሰንጠረዡ ዳግም የበላይነታቸውን አስጠብቀዋል። ለሊቨርፑል 2ኛዋ ግብ በፍጹም ቅጣት ምት እንድትገኝ ያስደረገው ግብጻዊው ሞሐመድ ሳላኅ በተከላካይ ቢያዝም አወዳደቁ ላይ ግን ግነት አሳይቷል። ካርዲፎችን ግነቱ ያናደዳቸውን ያህል አጋጣሚውን የተጠቀመበት መንገድ ለሊቨርፑሎች አስፈንድቋል። ሊቨርፑል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ሲቲን በ2 ነጥብ በልጦ 88 ነጥቦች ሰብስቧል። 

Fußball 1. Bundesliga | Borussia Mönchengladbach - RB Leipzig | 0:2
ምስል imago/U. Kraft

የፊታችን ረቡዕ ወደ ኦልትራፎርድ አቅንቶ ለሚጋጠመው ማንቸስተር ሲቲ ቀጣዩ ግጥሚያ የሞት ሽረት መኾኑ አያጠራጥርም። ማንቸስተር ሲቲ ረቡዕ የሚገጥመው ትናንት በኤቨርተን የ4 ለ0 ከባድ ሽንፈት እልህ ውስጥ የገባውን ማንቸስተር ዩናይትድን ነው። ያም በመኾኑ ተስተካካይ ጨዋታው ለማንቸስተር ሲቲ ፈታኝ ሊኾን ይችላል።  ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት በሰፊ ልዩነት ለሽንፈት መዳረጉ ለቀጣዩ ዙር ሻምፒዮንስ ሊግ ለማለፍ የሚያደርገው ጉዞ ላይ ወርቃማ እድሉን አሳጥቶታል። ያም በኾኑ የረቡዕ ግጥሚያ ከምንም በላይ መኾኑን ተከላካዩ አሽሌ ያንግ ተናግሯል። ማንቸስተር ዩናይትድ 64 ነጥብ ይዞ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በ2 ነጥብ የሚበልጠው ቸልሲ ዛሬ ማታ ከበርንሌይ ጋር ይጋጠማል።  15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው በርንሌይ ቸልሲን የሚያሸንፍ ከኾነ ማንቸስተር ዩናይትድ ይበልጥ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ አይቀርም። በእሁዱ ጨዋታ በውድድር ዘመኑ አራተኛ ኾኖ የመጨረስ ዕድላቸውን በጎዲሰን ፓርክ ከእጃቸው ያስወጡት የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ኦሌ ሶልስካዬር ደጋፊዎቻቸውን ይቅርታ ጠይቀዋል። 

«አምስት ደቂቃ ብቻ በቂ አይደለም» በምሬት የተዋጠው የ21 ዓመቱ ወጣት አማካይ በሳምንቱ ማሳረጊያ በምሬት የተናገረው ነበር። በባየር ሙይንሽን ቆይታው ደስተኛ ያልኾነው ፖርቹጋላዊ  ሬናቶ ዛንቼስ፦ «አምስት ደቂቃ ብቻ በቂ አይደለም። ወጣት ነኝ፤ ብዙ መጫወት እፈልጋለኹ» ብሏል በምሬት። «በውሰት አለያም በሽያጭ ወደ ሌላ ቡድን መዛወሬ የትኛው እንደሚበጀኝ የምናየው ይኾናል» ብሏል የባየር ሙይንሽን ቆይታው ማብቃቱን በማስረገጥ። ሬናቶ ዛንቼስ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2016 ዓም በ35 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ ከቤኔፊካ ወደ ባየር ሙይንሽን ሲመጣ ብዙ ተወርቶለት ነበር። በቡድኑ ቆይታው ግን በደንብ መሰለፍ ባለመቻሉ ከቡድኑ ለመለየት ከውሳኔ ላይ ደርሷል።

በቡንደስ ሊጋው ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ከተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር ዋንጫውን ለማንሳት ትንቅንቅ ላይ ነው።  የሬናቶ ዛንቼስን ልብ የሰበረው ባየር ሙይንሽን በቡንደስ ሊጋው 70 ነጥብ ሰብስቧል መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ብዙም እንዳይኩራራ ግን ቦሩስያ ዶርትሙንድ በአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ ነው የሚከተለው።

በስፔን ላሊጋውን ባርሴሎና በ77 ነጥብ እየመራ ነው። አትሌቲኮ ማድሪድ በ68 ነጥብ ይከተላል። ትናንት አትሌቲክ  ቢልባዎን 3 ለ0 ያሰናበተው ሪያል ማድሪድ 64 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የእለቱ ድንቅ ኾኖ የቆየው ፈረንሳዊው አጥቂ ካሪም ቤንዜማ 47ኛው ደቂቃ ላይ በከፍታ ዘሎ ከጉልበቱ ሸብረክ በማለት በጭንቅላት ገጭቶ ያስቆጠራት ግብ ድንቅ ተብላለታለች።  በ76ኛው ደቂቃ ላይም ካሪም ቤንዜማ እንደዛው ዘሎ በጭንቅላት በመግጨት ኹለተኛ ግቡን አስቆጥሯል።

Fussball  1. Bundesliga | Hertha BSC vs Hannover 96
ምስል imago/Contrast

ከረፍት መልስ ተቀይሮ የገባው የዌልሱ አጥቂ ጋሬት ቤል ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያገኛትን ኳስ ከአግዳሚው በላይ በመምታት ስቷል። በማድሪድ የአምስት የጨዋታ ዘመን አራት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ያነሳ፤ በኹለቱ ፍጻሜዎች ላይ ወሳኝ ግቦችን ያስቆጠረው ጋሬት ቤል ላይ ደጋፊዎች መጮኻቸው ግራ እንዳጋባው አሰልጣኝ ዚነዲን ዜዳን ተናግሯል። «በእውነቱ ምንም ዐላውቅም፤ ከምር ምንም አልገባኝም» ብሏል። የሪያል ማድሪዱ አሰልጣኝ። 90 ደቂቃው መደበኛ የጨዋታ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው አንድ ደቂቃ ላይ ካሪም ቤንዜማ ሦስተኛ ግቡን ከመረብ በማሳረፍ ሔትትሪክ ሠርቷል።  

በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ወራጅ ቃጣናውን ተጠግተው 11ኛ እና 12ኛ ደረጃ ላይ በሚገኙት በደቡብ ፖሊስና በወላይታ ዲቻ የአግር ኳስ ቡድን  ደጋፊዎች መካከል በተፈጠርው ግጭት 37 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። በሁለቱ ደጋፊዎች መካከል ቅዳሜ እለት የተፈጠረው ግጭት ወደ ተለያዩ የከተማው ክፍሎች ከተዛመተ በኋላ በረድ ያለው ትናንት ነበር። ፖሊስ በኹከቱ ተሳታፊ ናቸው ብሎ የጠረጠራቸውን ሰላሳ ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ መጀመሩን የከተማው ፖሊስ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮማንደር መስፍን ለዶይቸቬለ ገልጸዋል። በሁከቱ በአስራ ስምንት ሰዎች ላይ መፈንከትን ጨምሮ ቀላልና ከባድ አካላዊ ጉዳት መድረሱን፤ በሁለት የፖሊስና በስምንት የግለሰብ  ተሽከረካሪዎች ላይም የመሰባበር ጉዳት መድረሱን ዋና አዛዡ ተናግረዋል። በግርግሩ ጉዳት የደረሰባችው ሰዎች በሀዋሳ  አዳሬ ሆስፒታል የህክምና ርዳት እየተደረገላችው እንደሚገኝ የጠቆሙት ዋና አዛዡ  በአሁኑ ውቅት በከተማው ይስተዋል የነበረው የደጥታ ስጋት ሙሉ በሙሉ በመቀረፉ ኅብረተሰቡ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱን ማረጋገጣቸውን የሀዋሳው ወኪላችን  ሸዋንግዛው ወጋየሁ የላከልን ዘገባ ያመለክታል ።

አትሌቲክስ

ከትውልድ መንደሯ ኮፈሌ እስከ ዓለም ታላላቅ የአትሌቲክስ መንደሮች ተካፋይ ኾናለች፤ አትሌት ገለቴ ቡርቃ። ሀገሯን ወክላ በተካፈለችባቸው ከ1500 እስከ 10000 ሜትር ርቀቶችም ብቃቷን አስመስክራለች፤ አኩሪ ድልም አስመዝግባለች።  ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ፊቷን ወደ ማራቶን ያዞረችው አትሌት ገለቴ  ሰሞኑን በፈረንሳይ መዲና በተኪያሄደው የፓሪስ ማራቶን  የሩጫ ውድድር አሸናፊ መኾኗ ይታወሳል። በፓሪስ ቆይታዋ 2 ሰአት ከ22 ደቂቃ  ከ47 ሰከንድ ሮጣ ስላሸነፈችበት የፓሪሱ ማራቶን ውጤት እና ስለቀጣይ የውድድር እቅዷ ለዶይቸ ቬለ ተናግራለች። ሃይማኖት ጥሩነህ አነጋግራታለች።

Leichtathletik Paris Marathon Siegerin Gelete Burka
ምስል Reuters/R. Duvignau

ከዚሁ ከአትሌቲክስ ዜና ሳንወጣ፦ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2008 የቻይና ኦሎምፒክ የ1500 ሜትር ባለድሉ  ኬንያዊ  አትሌት ለአራት ዓመታት ከስፖርት ውድድሮች ታግዷል። ኬንያዊ አትሌት አስቤል ኪፕሮፕ የአራት ዓመት እገዳ የተጣለበት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2017 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ በተደረገለት ምርመራ ኤሪትሮፖይቲን የተሰኘ ኃይል ሰጪ ንጥረ-ነገር በደሙ ውስጥ በመገኘቱ ነው። የ29 ዓመቱ ሯጭ ጥፋተኛ አይደለኹም ሲል ቢከራከርም፤ የአትሌቶች ልእልና ኅብረት (AIU) ግን ጥፋተኛ መኾኑን ተናግሯል።  ባለፈው ቅዳሜ ጥፋተኛ በሚል እገዳ የተጣለበት ኬኒያዊ  አትሌት በዓለም የሩጫ ፉክክር ሦስት ወርቆችን ያገኘው ይኽን የተከለከለ ኃይል ሰጪ ንጥረ-ነገር በመጠቀም ነው ተብሏል።

ኮትዲቯር መዲና አቢጃን ውስጥ በተከናወነው ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች የአፍሪቃ አትሌቶች ፉክክር ላይ ደቡብ አፍሪቃ እና ኬንያ ልቀው ወጥተዋል። በሳምንቱ ማሳረጊያ ላይ በተጠናቀቀው ውድድር ኬንያ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ላይ አጠቃላይ 28 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በአንደኛነት አጠናቃለች። ከ28ቱ ሜዳሊያዎች 13ቱ ወርቅ ናቸው።ከ18 ዓመት በታች ታዳጊዎች ባከናወኑት ውድድር  ደቡብ አፍሪቃ በበኩሏ 32 ሜዳሊያ በማግኘት አንደኛ ወጥታለች። በዚህ ውድድር ዘርፍ 18 ሜዳሊያዎቿ የወርቅ ናቸው።  ኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች 11 ሜዳሊያ በማግኘት፤ ከ20 ዓመት በታች ተፎካካሪዎች ደግሞ 22 ሜዳሊያ በመሰብሰብ በ4ኛ ደረጃ አጠናቃለች።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሃይማኖት ጥሩነህ

ተስፋለም ወልደየስ