ስፖርት፤ ሚያዝያ 21 ቀን፣ 2011 ዓ.ም
ሰኞ፣ ሚያዝያ 21 2011በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሣምንቱ ማሳረጊያ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ከዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ሊቨርፑል በግብ ሲንበሸበሽ፤ ማንቸስተር ሲቲ እንደምንም ብሎ አንድ ግብ አስቆጥሯል። ሊቨርፑል በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 20ኛ ላይ የሚገኘው ሁደርስፌልድን ዐርብ እለት 5 ለ0 የግብ ጎተራ ሲያደርግ፤ ማንቸስተር ሲቲ ነጥብ እንዲጥል ተስፋ በማድረግ ነበር።
ለሊቨርፑል አምስቱንም ግቦች ያስቆጠሩት አፍሪቃውያን ተጨዋቾች ናቸው። ጊኒያዊው ናቢ ኬይታ ሊቨርፑልን መሪ ያደረገችውን ግብ ሲያስቆጥር ጨዋታው ከተጀመረ አንድ ደቂቃም አላለፈም ነበር። ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ማኔ ሁለተኛዋን በ23ኛው ደቂቃ እንዲሁም አራተኛዋን ግብ በ66ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፏል። ግብጻዊው ሞሐመድ ሳላህ፤ የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ 45 ደቂቃ አልፎ በጭማሪው አንድ ደቂቃ ላይ ለሊቨርፑል ሦስተኛዋን ለራሱ የመጀመሪያዋን ግብ አስቆጥሯል። 83ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በእርጋታ የተሞላው ግብጻዊ አምስተኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል። ሊቨርፑል ረቡዕ ምሽት ከባርሴሎና ጋር ለሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ የሚያደርገው ጨዋታ በበርካቶች ዘንድ ይጠበቃል።
ትናንት ማንቸስተር ሲቲ የመጀመሪያው አጋማሽ እስኪፈጸም ግብ ማስቆጠር ተስኖት ቆይቶ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን በ63ኛው ደቂቃ ላይ ሠርጂዮ አጉዌሮ ያስቆጠራት ግብ ማንቸስተር ሲቲን ዳግም ወደ መሪነቱ መልሶታል። ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች የሚቀሩት የዘንድሮ ፕሬሚየር ሊግ ፍጻሜው ምን እንደሚኾን ከወዲሁ መገመት ቢከብድም፤ አሁን ባለው ውጤት መሠረት ማንቸስተር ሲቲ 92 ነጥብ እና 68 ንጹህ ግቦች ይዞ ይመራል። ሊቨርፑል ከማንቸስተር ሲቲ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ፤ በአራት ንጹህ ግቦች ተበልጦ በሁለተኛነት ደረጃ ላይ ይገኛል።
ለሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ነገ ማታ የሆላንዱ አያክስ አምስተርዳምን የሚገጥመው ቶትንሐም፤ ቸልሲ፣ አርሰናል እና ማንቸስተር ዩናይትድ በፕሬሚየር ሊጉ ለኹለተኛ ተከታታይ ሳምንት ማሸነፍ ተስኗቸዋል። እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሦስተኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ይዘዋል።
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ከኑረንበርግ ጋር ባደረገው ግጥሚያ አንድ እኩል ተለያይቶ ነጥብ ጥሏል፤ ኾኖም መሪነቱን በ71 ነጥብ እንዳስጠበቀ ነው። ኪንግስሌይ ኮማን ባየርን በአምስት ነጥብ ሊመራ የሚያስችለውን ወርቃማ እድል አምክኗል። ባየር ሙይንሽንን በኹለት ነጥብ ዝቅ ብሎ የሚከተለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ለሻልከ እጅ ሰጥቶ 4 ለ2 ድል ተነስቷል። በማሪዮ ጎይትስ ቀዳሚ ግብ መሪ የነበረው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በአወዛጋቢው ፍጹም ቅጣት ምት መሪነቱን አጥቷል። ማርኮ ሮይስን እና ሚሻኤል ቮልፍን በቀይ ካርድ ያጣው ዶርትሙንድ በ30 ደቂቃ ጨዋታ ሁሉ ነገሩ ከእጁ አፈትልኳል።
64 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይፕሲሽ ፍራይቡርግን 2 ለ1 ድል አድርጎ በቀጣይ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን አስጠብቋል። ሌላው በሳምንቱ አስገራሚ የቡንደስሊጋ ግጥሚያ የረዥም ጊዜ ልምድ ያለው ቬርደር ብሬመን በአዳጊው ፎርቱና ዱይስልዶርፍ 4 ለ1 መንኮታኮቱ ነበር።
አትሌቲክስ
በሐምቡርግ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት ድል ቀንቷቸዋል። በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዲባቤ ኩማ 2 ሰአት ከ24 ደቂቃ ከ42 ሰከንድ በመሮጥ አንደኛ ወጥታለች። በቀዝቃዛው እና ዝናባማው የትናንቱ የሀምቡርግ ማራቶን በወንዶች ፉክክርም ድሉ የኢትዮጵያውያን ነበር። ታዱ አባተ የአንደኛነት ድሉን የተገጎናጸፈው የሀገሩ ልጅ አየለ አብሽሮን በማስከተል 2 ሰአት ከ8 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ በመሮጥ ነው። እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በ2012 የኦሎምፒክ ባለድሉ ኡጋንዳዊው ሽቴፋን ኪፕሮትቺ በሦስተኛነት አጠናቋል። በሴቶቹ ፉክክር ኬንያዊቷ ማግዳሊኔ ማሳይ እና ታንዛኒያዊቷ ፋይሉና ማታንጋ የኹለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ ይዘዋል።
ኢትዮጵያውያኑ በሐምቡርግ ድል ሲጎናጸፉ በለንደኑ ማራቶን የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል። ከለንደኑ ማራቶን ጥቂት ቀደም ብሎ የመገናኛ አውታር ትኩረትን ስቦ የነበረው ሞ ፋራህ በአምሰተኛነት አጠናቋል። ሞ ፋራህ ከንግዲህ በማራቶን የሚያሸንፈው መቼ እንደኾን ተጠይቆ ማሸነፍ የሚችለው በለንደኑ ማራቶን አሸናፊ የኾነው ኤሊውድ ከማራቶን ከተገለለ ብቻ እንደኾን ተናግሯል። «በቃ ጡረታ ይውጣ» ሲልም ለኤሊውድ ኪፕቾጌ እጅ ሰጥቷል። ያም ብቻ አይደለም በትናንቱ ፉክክር ሞ ፋራህ ለኢትዮጵያውያንም እጅ ሰጥቷል።
ባሳለፍነው ሳምንት የስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን አዘጋጅነት አዲስ አበባ ውስጥ ተከናውኖ ነበር። የፓሪሷ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ የስፖርት ሰውን አነጋግራ ቀጣዩን ዘገባ ከፓሪስ ልካልናለች።
አኹን ደግሞ አጫጭር የስፖርት ዜና እናሰማችኋለን። የማንቸስተር ሲቲው አማካይ ራሂም ስተርሊንግ በእግር ኳስ ስፖርት ጸሐፊዎች የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች ተብሎ ዛሬ ተሰይሟል።
በሌላ ዜና፦ ሼፊልድ ዩናይትድ ከ12 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ፕሬሚየር ሊጉ ለመመለስ እድሉን አስፍቷል። ትናንት ከአስቶን ቪላ ጋር አንድ እኩል የተለያየው ሼፊልድ ዩናይትድ ስቶክ ሲቲን ካሸነፈ ዋንጫ የማንሳት ተስፋው ይበልጥ ይለመልማል። ኖርዊች ሲቲ የፊታችን እሁድ በመጨረሻ ጨዋታው በአስቶን ቪላ ከተሸነፈ ምናልባትም ሼፊልድ ዩናይትድ የሁለተኛ ዲቪዚዮን ዋንጫውን ሊያነሳ ይችላል።
አርጀንቲናዊው አጥቂ የኤሚሊያኖ ሳላ አባት ሆራቺዮ ልጃቸው በአውሮፕላን አደጋ ሕይወቱን ባጣ በሦስተኛ ወሩ ሞተው ተገኙ። የከባድ ጭነት መኪና አሽከርካሪ የነበሩት የ58 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ባለፈው ሳምንት ሞተው የተገኙት በልብ ድካም የተነሳ መኾኑን ፖሊስ ገልጧል። ለፈረንሳዩ ናንቴ ቡድን ይጫወት የነበረው አርጀንቲናዊው አጥቂ ኤሚሊያኖ ራውል ሳላን እና አብራሪውን አሳፍራ የነበረችው ማሊቡ N264DB አነስተኛ አውሮፕላን ደብዛዋ የጠፋው ሰኞ ጥር 13 ቀን፣ 2011 ዓ.ም ወደ እንግሊዙ ካርዲፍ ቡድን ሲያቀኑ ነበር። ጥር 27 ቀን፣ 2011 ዓ.ም ደግሞ ከራዳር ውጪ ተሰውራ የነበረችው አነስተኛ አውሮፕላን በፈረንሳይና ብሪታንያ መሀል ከባሕር ጠለል ስር ተከስክሳ መገኘቷ ተዘገበ።
የኤሚሊያኖ ሳላ አስክሬን ፎቶግራፍ በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ማንነቱ ባልታወቀ ግለሰብ ተሰራጭቶ ነበር። የብሪታንያ ፖሊስ የተጨዋቹን ፎቶግራፍ ማን እንዳነሳው እና ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይም በመጀመሪ እንዳወጣ ለማወቅ ማንነት ማጣራት መጀመሩን ትናንት ዐስታውቋል። ከሳላ ጋር አብሮ የነበረው የአነስተኛዋ አውሮፕላን አብራሪ የ59 ዓመቱ ዳቪድ ኢቦስቶን አስክሬን ግን አሁንም ድረስ አልተገኘም።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ