1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት ሪፖርት

ሰኞ፣ ነሐሴ 6 2005

ባለፈው አርብ ምሽት ሞስኮ ላይ የተከፈተው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማሕበር ሻምፒዮና አስደናቂ ውጤቶችን በማስመዝገብ እንደቀጠለ ነው።

https://p.dw.com/p/19ODq
ምስል Reuters

በትናንቱ ዕለት ምንም እንኳ ያልተጠበቀ ባይሆንም በተለይ የዩሤይን ቦልትና የጥሩነሽ ዲባባ የአሯሯጥ ውበት ከሞስኮው ስታዲዮም ባሻገር በዓለም ዙሪያ ውድድሩን በቴሌቪዥን አማካይነት የተከታተሉ አያሌ ተመልካቾችን እጅግ የማረከ ነበር።

Leichtathletik WM 2013 Moskau Usain Bolt
ምስል Reuters

በአንድ መቶ ሜትር ሩጫ የጃሜይካው መንኮራኩር ዩሤይን ቦልት በተለየ ጥንካሬ በ9,77 ሤኮንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አሜሪካዊው ጃስቲን ጋትሊን በ 9,85 ሤኮንድ ጊዜ ለሁለተኝነት በቅቷል። ሶሥተኛ በመሆን ለጃሜይካ ተጨማሪ የናስ ሜዳሊያ ያስገኘው ደግሞ ኔስታ ካርተር ነበር። የጃሜይካ ኮከብ በምሽቱ በዩሤይን ቦልት አማካይነት ፈክቶ ሲታይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማም በጥሩነሽ ዲባባና በበላይነሽ ኦልጂራ ታላቅ ድል ደምቆ ሊውለበለብ በቅቷል።

Russland Leichtathletik WM in Moskau Tirunesh Dibaba und Belaynesh Oljira
ምስል Haimanot Tiruneh

ጥሩነሽ ትዕግሥትና የታክቲክ ብስለት በሰመረበት ሩጫዋ በ 30 ደቂቃ ከ 43,35 ሤኮንድ ጊዜ ለሶሥተኛ የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያዋ ስትበቃ ከኔያዊት ተፎካካሪዋ ግሌዲይስ ቼሮኖ ሁለተኛ እንዲሁም በላይነሽ ኦልጂራ ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። ጥሩነሽ የመጨረሻውን አንድ መቶ ሜትር በፍጥነት በመሮጥ ተፎካካሪዎቿን ፈትለክ ብላ ስታመልጥ በሞስኮው ስታዲዮም የተገኘው ተመልካች በጭብጨባና በሆታ አድናቆቱን ገልጾላታል። የትናንቱ ምሽት ድል በተከታታይ 11ኛው መሆኑም ነበር። እዚህ ላይ በላይነሽ ኦልጂራ ኬንያውያት አትሌቶችን በማዳከም ለድሉ ያደረገችው ታላቅ የቡድን አስተዋጽኦም ሊጠቀስና ሊወደስ የሚገባው ጉዳይ ነው።

14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከፊታችን ሰንበት የሚዘልቅ ሲሆን በሂደቱ ገና ብዙ አስደናቂ ውጤቶች እንደሚታዩ ጨርሶ ጥርጥር የለውም። የኢትዮጵያን አትሌቶች በተመለከተ እስካሁን ያደረጉት ተሳትፎ፣ ውጤትና ቀጣይ ተሥፋ ምን እንደሚመስል ውድድሩን በስፍራው በመሆን በቀጥታ በመከታተል ላይ የምትገኘውን ወኪላችንን ሃይማኖት ጥሩነህን ከጥቂት ሰዓታት በፊት በስልክ አነጋግሬ ነበር።

Tennis Italian Open Rafael Nadal
ምስል picture-alliance/dpa

ከዚህ ሌላ ሰንበቱን በካናዳ በተካሄዱ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያዎች በወንዶች የዓለም አራተኛው ራፋኤል ናዳልና አሜሪካዊቱ ሤሬና ዊሊያምስ ለድል በቅተዋል። የስፓኙ ተወላጅ ካናዳዊውን ሚሎሽ ራኦኒችን 6-2,6-2 ሲረታ የዓለም አንደኛዋ ሤሬና ዊሊያምስ ደግሞ የሩሜኒያ ተጋጣሚዋን ሶራና ኪርስቴያን በለየለት 6-2,6-0 ውጤት አሰናብታለች።

FIFA Confederations Cup Brasilien 2013 Halbfinale Diego Lugano Uruguay
ምስል Reuters

በተቀረ በእግር ኳሱ ዓለም በዚህ በአውሮፓ የቀደምቱ ሊጋዎች ውድድር ቀስ በቀስ በመጀመር ላይ ሲሆን በሣምንቱ ሂደት በዓለምአቀፍ ደረጃ 50 ገደማ የሚጠጉ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በዚህ በአውሮፓ ከሚደረጉት መካከል ያለፈው ሰኔ ወር የኮንፌደሬሽን ዋንጫ አሸናፊ ብራዚል ከስዊትዘርላንድ የምታካሂደው ግጥሚያ አንዱ ሲሆን እንግሊዝ ከስኮትላንድ በለንደኑ ዌምብሌይ ስታዲዮም፤ ቤልጂግ ከፈረንሣይና ስዊድን ከኖርዌይ ይገኙበታል።

የዓለምና የአውሮፓ ሻምፒዮን የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን ባሕር ማዶ ወደ ኤኩዋዶር የሚያመራ ሲሆን የኤሩጉዋይ ቡድንም ወደ ጃፓን ተጓዥ ነው። ከዚህ በተቀረ ጀርመን ፓራጉዋይን የምታስተናግድ ሲሆን ሜክሢኮ ከአይቮሪ ኮስት፤ ኢጣሊያ ከአርጄንቲናና ዩ ኤስ አሜሪካ ከቦስኒያ ይጋጠማሉ።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ