1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ታኅሣሥ 22 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2011

በአዲስ አበባ ስታዲየም ስለተከናወነው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የቡና እግር ኳስ ቡድኖች ጨዋታ እና የደጋፊዎች ኹኔታ በተመለከተ ጨዋታውን ከስታዲየም ከተከታተለ የስፖርት ተንታኝ ጋር የተደረገ ቃለመጠይቅ ይኖረናል። የፕሬሚየር ሊግ፣ የቡንደስሊጋ ጨዋታዎች ቅኝት እንዲሁም የሜዳ ቴኒስን የሚመለከቱ ዘገባዎች ይኖሩናል። 

https://p.dw.com/p/3ApKa
Premier League Wolverhampton vs Liverpool Mohamed Salah
ምስል picture-alliance/SOLO Syndication

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በኢትዮጵያ ቡና ቡድኖች መካከል የሚደረገው የእግር ኳስ ጨዋታ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቅ ነው። ኾኖም የኩለቱ ቡድኖች የትናንቱ ግጥሚያ መላ ቅጡ ጠፍቶት ደጋፊዎችን ማማረሩ ሊታሰብበት እንደሚገባ የእግር ኳስ ተንታኞች እየተናገሩ ነው።  በትናንቱ  ጨዋታ ቡድኖቹ ያለምንም ግብ ነው የተለያዩት።   በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ግስጋሴውን እንደቀጠለ ነው። በሳምንቱ መጨረሻ  ግጥሚያ አርሰናልን አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ አደባይቷል።  ትናንት ሳውዝሀምፕተንን  በጨዋታ በልጦ በሰፊ ግብ ልዩነት ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ በበኩሉ ከሊቨርፑል ጋር የነበረውን ነጥብ ለማጥበብ ችሏል። ማንቸስተር ዩናይትድ በተከታታይ ማሸነፉን ቀጥሏል። በቡንደስሊጋው ቦሩስያ ዶርትሙንድ አኹንም መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው።

ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከመሻገራችን በፊት የትናንትናውን የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታ ግጥሚያ እንቃኝ። የፕሬሚየር ሊጉ ስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲከናወን የሁለቱ ቡድኖች ኃላፊዎች በታዳሚዎች ዘንድ ሲተቃቀፉ ታይተዋል። የሰላም ሚንስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በተገኙበት የተከናወነውን የትናንቱ ጨዋታ ለመመልከት የታደመው ደጋፊ ሰላማዊ እንደነበር ተጠቅሷል። የትሪቡን ስፖርት ዋና ዘአጋጅ ፍቅር ይልቃል የትናንቱን ጨዋታ ቡድኖቹ፦ «ከደጋፊዎቹ ያነሰ ትእይንት ያሳዩበት» ሲል ገልጦታል።

ፕሬሚየር ሊግ

ቅዳሜ እለት አርሰናልን 5 ለ1 ያንኮታኮተው ሊቨርፑል የእንግሊዙ ፕሬሚየር ሊግን በ7 ነጥብ ልዩነት እየመራ ይገኛል። የቶትንሐም ሆትስፐር ግስጋሴ በዎልቭስ የ3 ለ1 ሽንፈት ተሰናክሏል።  ማንቸስተር ዩናይትድ በኦሌ ጉነር ሶልስክያር ጊዜያዊ አሰልጣኝነት ስር ከተያዘ ጀምሮ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎችን አሸንፏል። ማንቸስተር ዩናይትድ ከበርመስ ጋር ባከናወነው የትናንቱ  ጨዋታ ሁለት ግቦችን ከመረብ ያሳረፈው ፖል ፖግባ ገኖ ወጥቷል።  ለማንቸስተር ዩናይትድ በመጨረሻው 20 ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ሮሜሉ ሉካኩ እና ማርኩስ ራሽፎርድም ግብ አስቆጥረዋል።  ራሽፎርድ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማመቻቸትም ብቃቱን አስመስክሯል። ሉካኩ ተቀይሮ እንደገባ በ72ኛው ደቂቃ ላይ ወዲያው ግብ በማስቆጠር እኔም አለሁ ብሏል። የማንቸስተር ዩናይትድን በር አላስደፍር ያለው ኤሪክ ቤርትራንድ ባይሌይ በ7ኛው ደቂቃ ላይ በፈጸመው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል፤ እንዲያም ኾኖ ጨዋታው 4 ለ1 ተጠናቋል።

Russland WM 2018 Frankreich gegen Kroatien
ምስል Reuters/M. Shemetov

ሌላው በሳምንቱ መጨረሻ ጎልቶ የወጣው ሊቨርፑል አርሰናልን 5  ለ1 በኾነ ሰፊ የግብ ልዩነት እንደማይኾን አድርጎ ድባቅ የመታበት ጨዋታ ነው። በቅዳሜው ጨዋታ ግብ አዳኙ ሮቤርቶ ፊርሚኖ ለሊቨርፑል ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትሪክ ሠርቷል። ሳዲዮ ማኔ በ32ኛው ደቂቃ እንዲሁም ግብጻዊው ሞሐመድ ሳላህ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመረው ሁለተኛ ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል። ለአርሰናል ቀዳሚዋን እና ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው አይንስሌይ ማይትላንድ ኒለስ  ነው። ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ቡድናቸውን በተረከቡበት ወቅት ሊቨርፑልን ወደ ቀድሞ ዝናው ለመመለስ ጥቂት ዓመታት እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረው ነበር። ምናልባት ዘንድሮ ይሳካላቸው ይኾን? አካሄዳቸው ግን ሊቨርፑል ከ29 ዓመታት ወዲህ ዋንጫውን እንዲያነሳ ለማስቻል የቆረጡ ይመስላሉ። ሊቨርፑል ከ15 ቀናት በኋላ ወደ ማንቸስተር ሲቲ ተጉዞ የሚያደርገው

ቡድንደስ ሊጋ

ቡንደስሊጋውን በነጥብ እየመራ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዐርብ እለት ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 2 ለ1 አሸንፎ ባገኘው ነጥቡ ተከታዩ ባየር ሙይንሽንን  በስድስት ነጥብ ርቆታል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ 42 ነጥብ አለው።  ባየርሙይንሽን  ቅዳሜ ዕለት አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 3 ለ0  አሸንፎ ነው ከቦሩስያ ዶርትሙንድ በ6 ነጥብ መከተል የቻለው።  በዕለቱ ግቦቹን ያስቆጠሩት ፍራንክ ሪቤሪ 2 እንዲሁም ራፊና ናቸው። በእለቱ ግብ ያልቀናው የባየር ሙይንሽኑ አጥቂ  ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ የእግር ኳስ ዘመኑን ማጠናቀቅ የሚሻው በባየር ሙይንሽን እንደኾነ ተናግሯል። የ30 ዓመቱ ፖላንዳዊ አጥቂ ላይ የስፔኑ ሪያል ማድሪድ እና የእንግሊዙ ቸልሲ ዐይናቸውን ጥለውበታል ተብሎ ነበር።

England, London: Roger Federer beim Match gegen Dominic Thiem
ምስል Getty Images/N. Baker

የሜዳ ቴኒስ

በሆፕማን የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ስዊዘርላንዳውያኑ ሮጀር ፌዴሬር እና ቤሊንዳ ቤንቺክ የታላቋ ብሪታንያ ተፋላሚዎች ካሜሩን ኖሪ እና ኬቲ በትለርን 3 ለ0 አሸነፉ። የዓለማችን ቁጥር ሦስት ምርጥ የሜዳ ተጨዋቹ ሮጀር ፌዴሬር በጣምራ ግጥሚያ ከማሸነፉ በፊት ካሜሩን ኖሪን 6-1 እና 6-1  በኾነ ውጤት አሸንፏል። በሴቶቹ ዘርፍ ደግሞ ቤሊንዳ ቤንቺች ያሸነፈችው 6-2 እና 7-6 በድምሩ (7-0) ነው። በጋራ ውድድሩም ስዊዘርላንዳውያኑ 4-3 (4-0) 4-1 አሸንፈዋል። የሆፕማን ዋንጫ እያንዳንዳቸው ኹለት ተፎካካሪዎች ባሉበት የአራት ሃገራት ቡድኖች መካከል የሚከናወን ሲኾን፤ የፍጻሜው ፍልሚያ የፊታችን ቅዳሜ ይከናወናል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ