ስፖርት፤ ታኅሣስ 27 ቀን፣ 2012 ዓ.ም
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 27 2012ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በቻይና ዢያሜን ማራቶን የሩጫ ፉክክር በወንድም በሴትም ትናንት ድል ተቀዳጅተዋል። የማራቶን ውድድሩን የቻይናው ዢኑዋ የዜና ምንጭ በድረገጹ ላይ የዓመቱ በወርቅ ደረጃ የተከናወነ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ሲል ጠቅሶታል። በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃ በመያዝ ድል አድርገዋል።
አትሌቲክስ
በወንዶች ፉክክር የ25 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ሯጭ ብርሃን ነበበው 2:08:16 በመሮጥ አንደኛ ወጥቷል። ብርሃን እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ባለፈው ዓመት ፖርቹጋል ሊዛቦን ውስጥ በተከናወነው የማራቶን ሩጫ አሸናፊ ነበር። በዕለቱ ውድድር ኬኒያዊው ሯጭ ሮይበን ኪፕሮ ኬሪዮ 2:08:46 በመሮጥ የኹለተኛ ደረጃን አግኝቷል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ግርማይ ብርሃኑ ከኬንያዊው በ6 ሰከንዶች ብቻ ለጥቂት ተበልጦ ሦስተኛ ወጥቷል። አብዲሳ ተሾመ እና ደጀኔ ደበላም አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃን ይዘው ነው ያጠናቀቁት።
በሴቶች ተመሳሳይ የሩጫ ፉክክር ደምቀው የወጡት ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ናቸው። አትሌት መዲና ደሜ በአንደኛነት ያጠናቀቀችው 2:26:12 በመሮጥ ነበር። መሠራ ሑሴን፣ አፈራ ጉድፋይ፣ ሕይወት አያሌው፣ የብርጓል መለሠ፣ ብርሃን ምኅረቱ፣ ፀሐይ ገብሬ እና ዝናሽ ደበበ በተከታታይ እስከ ስምንተኛ ያለውን ደረጃ ተቆጣጥረውታል። በውድድሩ ከ41 ሃገራት የተውጣጡ 35,071 ሯጮች ተካፋይ መኾናቸው ተጠቅሷል።
ቱርክ ውስጥ በተከናወነውም የግማሽ ማራቶን ሩጫ ፉክክር በወንዶችም በሴቶችም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ ኾነዋል። በሴቶች ፉክክር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡት፦ አታለል አንሙት፣ አገሬ በላቸው እና ዘውዲቱ አሸናፊ ናቸው። በወንዶቹ ደግሞ ጌታዬ ፍስሃ እና ፈጠነ ዓለሙ የአንደኛ እና የኹለተኛ ደረጃ አግኝተዋል። በሜክሲኮ የትናንትና የማራቶን ሩጫ በወንዶች ገዛኸኝ ኹንዴ አሸናፊ ኾኗል። በስፔን አገር አቋራጭ የዐሥር ሺህ ሰባት መቶ ሜርትር ፉክክር እንየው መኮንን አንደኛ ሲወጣ፤ በሴቶች የስምንት ሺህ ሰባት መቶ ሜርትር ፉክክር ደግሞ ጽጌ አብርሃ በአንደኛነት ማጠናቀቋን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በፌስቡክ ገጹ አትቷል።
እግር ኳስ
በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት ዌስትሀም ዩናይትድ ጊሊንግሃምን 2 ለ0 ሲያሸንፍ፤ ሊቨርፑል በወጣት እና ታዳጊ ተጨዋቾቹ ኤቨርተንን 1 ለ0 ጉድ አድርጎታል። በተለይ የአሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ወጣት ተጨዋቾች ብቃታቸውን ያሳዩበት ጨዋታ ነበር። ግብ ጠባቂው አድሪያን ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አምክኗል። አድሪያን ከረፍት በፊት ብቻ ዶሚኒክ፣ ማሶን እና ሪቻርሊሰን የሞከሯቸውን ድንቅ ሙከራዎች በብቃት ግብ ከመኾን አጨናግፏል።
ለሊቨርፑል ማሸነፊያ የኾነችውን ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው የ18 ዓመቱ ኩርቲስ ጆናስ ነው። ልምድ ካለው የሊቨርፑል አጥቂ ኦሪጊ ከግቡ በስተቀኝ የፍጹም ቅጣት ክልል አቅራቢያ በኩል የተላከለትን ኳስ በሚደንቅ ኹኔታ ከመረብ አሳርፏል። ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ በትናንቱ ጨዋታ ዘጠኝ ተጨዋቾችን ቀይረው ያስገቡ ሲኾን፤ ከዘጠኙ አራቱ በዐሥራዎቹ ዕድሜያቸው ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ለሻምፒዮንስ ሊግ እና ለፕሬሚየር ሊግ ዋንጫዎች ትኩረቱን ላደረገው ሊቨርፑል ወጣት ቡድኖቹም ተስፋ የሚጣልባቸው መኾኑን ያስመሰከረበት ጨዋታ ነበር።
በሌላ የኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ ባርንስሌይ ክሪው አሌክሳንድራን 3 ለ1፣ ደርቢ ኮንቲ ክሪስታል ፓላንስ 1 ለ0 አሸንፈዋል። ብሪስቶል ሮቨርስ እና ኮቨንትሪ 2 እኩል አቻ ወጥተዋል። ሼፊልድ ዩናይትድ ኤኤፍ ሲ ፎይልድን 2 ለ1 ሲያሸንፍ፣ ቶትንሀም ከሚድልስቦሮው ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። ዌስት ብሮሚች ቻርልተንን 1 ለ0፤ እንዲሁም ቸልሲ ኖቲንግሀምን 2 ለ0 ድል አድርገዋል። ኪው ፒ አር ስዋንሲ ሲቲን 5 ለ1 የግብ ጎተራ አድርጎታል።
ኤፍ ኤ ካፕ
ሦስተኛ ዙር የኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያዎች በብዛት የተከናወኑት ቅዳሜ እለት ሲኾን፤ ሦስት ቡድኖች እያንዳንዳቸው አራት አራት ግቦችን በተጋጣሚያቸው ላይ ማስቆጠር ችለዋል። ማንቸስተር ሲቲ ፖርት ቫሌን 4 ለ1፤ በርመስ ሉቶን ታውንን 4 ለ0 ድል አድርገዋል። ኖርዊች ፕሬስቶን ኖርዝ ኢንድን እንዲሁም በርንሌይ ፔተርቦሮውን በተመሳሳይ 4 ለ2 አሸንፈዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ ከዎልቨርሀምፕተን ጋር ያለምንም ግብ ሲለያይ፤ ላይስተር ሲቲ ዊጋንን 2 ለ0 ድል አድርጓል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በርካታ ግጥሚያዎች የተከናወኑ ሲኾን፤ አርሰናል ዛሬ ማታ ሊድስን ይገጥማል።
በአውሮጳ የእግር ኳስ ቡድኖች የተጨዋቾች ዝውውር ከመጠናቀቁ በፊት አንዳንድ ቡድኖች ተጨዋቾችን እያስፈረሙ ነው። የጀርመኑ ኃያል ባየር ሙይንሽን ባለፈው ቅዳሜ የሻልከውን ግብ ጠባቂ አሌክሳንደር ኖይብልን ለአምስት ዓመት ውል ለማስፈረም መስማማቱን ይፋ አድርጓል። ግብ ጠባቂው በቀጣዩ ዙር የቡንደስሊጋ ግጥሚያ ለባየር ሙይንሽን እንደሚሰለፍ ቡድኑ ዐስታውቋል። የስፔኑ ሪያል ማድሪድ በበኩሉ ብራዚላዊ ታዳጊን ለማስመጣት ጫፍ መድረሱ ተገልጧል። በቅርቡ ወጣቶቹ ቪንሺየስ ጁኒየር እና ሮድሪጎን ካስፈረመ ወዲህ የ17 ዓመቱን ራይነር ከብራዚሉ ፍላሚንጎ ቡድን ለማስፈረም ጫፍ መድረሱ ተገልጧል። ራይነር ወደ ማድሪድ የሚመጣው በ35 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ መኾኑም ተዘግቧል። የእግር ኳስ ተጨዋቾች ዝውውር የመጨረሻ ቀነ ገደብ ስፔን፤ ጀርመን እና ጣሊያን ውስጥ የሚያበቃው ከ25 ቀናት በኋላ ጃንዋሪ 31 ላይ ነው።
በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ትናንት መቀለ 70 እንደርታን 2 ለ1 አሸንፏል። በርካታ ደጋፊዎች በታደሙበት ግጥሚያ ቅዳሜ ዕለት ፋሲል ከነማ እና ባህርዳር ከተማ ባደረጉት ግጥሚያ ፋሲል ከነማ 3 ለ0 አሸንፏል። ስታዲየሙ ከመሙላቱ የተነሳ ደጋፊዎች በተራራማ ስፍራዎች ላይ ኾነው ጨዋታውን ሲከታተሉ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች በስፋት ተሰራጭተዋል። ኢትዮጵያ ቡና ሀዲያ ሆሳዕናን ያሸነፈበት ግጥሚያ በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት ኾኖ ተመዝግቧል። ኢትዮጵያ ቡንና ተጋጣሚው ላይ 5 ግቦችን አስቆጥሮ ነው ያሸነፈው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ