ስፖርት፤ ታኅሣሥ 6 ቀን፣ 2012 ዓ.ም
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 6 2012የሻምፒዮንስ ሊግ እና የአውሮጳ ሊግ የእግር ኳስ ቡድኖች ግጥሚያ ድልድል እጣ ዛሬ ከሰአት ላይ ወጥቷል። ጠንካራ ቡድኖች ጠንካራ ተፎካካሪዎች ደርሷቸዋል። ዝርዝር ይኖረናል። የማራቶን ሯጩ ኬኒያዊው አትሌት ኤሊውድ ቺፕቾጌ ቢቢሲ ባካሄደው የድረ-ገጽ ድምጽ አሰጣጥ የዓለም ምርጥ የዓመቱ ኮከብ ስፖርተኛ ተሰኝቷል። የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ዛሬ ባከናወነው ጉባኤው በተሽከርካሪ ወንበር ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ስፖርትን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማጠናከር ወስኗል። ለስፖርቱ ተገቢ ትኩረት እና ድጋፍ እንዲደረግለትም ጥሪ ተላልፏል።
እግር ኳስ
የአውሮጳ ኅብረት እግር ኳስ ማኅበር (UEFA) ዋና ጽሕፈት ቤት ከሚገኝበት ስዊዘርላንድ ኒዮን ማዘጋጃ ይፋ በኾነው የሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ውድድር የእጣ ድልድል የጀርመን ቡድኖች ከጠንካራ ተፎካካሪዎች ጋር ተመድበዋል። በቡንደስ ሊጋው ቅዳሜ ዕለት ማይንትስን አራት ለዜሮ ድል ያደረገው ቦሩስያ ዶርትሙንድ የቀድሞው አሰልጣኙ ተፎካካሪው ኾነው ብቅ ብለዋል። የቀድሞው የቦሩስያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ ቶማስ ቱሁል የፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንጄርሜን ቡድንን ይዘው ነው ከሁለት ወራት በኋላ ለሻምፒዮንስ ሊጉ ዋንጫ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር የሚፋለሙት። ዶርትሙንድ በቡንደስሊጋው 29 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።
ሌላኛው የጀርመን ቡድን ላይፕሲሽ የእንግሊዙ ቶትንሀም ሆትስፐርን ይገጥማል። ላይፕሲሽ በቡንደስሊጋው በ33 ነጥብ የመሪነቱን ደረጃ ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ተረክቧል። ከአውሮጳ ሊግ የምድብ ውድድር ለተሰናበተው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በቡንደስሊጋውም መሪነቱን በ2 ነጥብ ተበልጦ ማስረከቡ ለቡድኑ ደጋፊዎች የሚያበሳጭ ነው። በቡንደስሊጋው ቅዳሜ ዕለት ላይፕሲሽ ጠንካራ ያልኾነውን ፎርቱን ዱይስልዶርፍ ቡድን ገጥሞ 3 ለ0 አሸንፏል። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ደግሞ በትናንትናው ዕለት 2 ለ1 የተረታው በቮልፍስቡርግ ነው። ቮልፍስቡርግ በአውሮጳ ሊግም ድል ቀንቶታል።
በሻምፒዮንስ ሊጉ የዛሬ የእጣ ድልልድል መሰረት ባየር ሙይንሽን የደረሰው የእንግሊዙ ቸልሲ ነው። ባየር ሙይንሽን በጀርመን ቡንደስሊጋ ቅዳሜ ዕለት ቬርደር ብሬመንን 6 ለ1 ሲያንኮታኩት፤ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቼልሲ ዝቅተኛ በሚባለውና ከታችኛው ዲቪዚዮን ባደገው ቦርሞስ ቡድን ቅዳሜ ዕለት 1 ለ0 ተሸንፏል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዘንድሮ እንደቀድሞው ጠንከር ብሎ ያልታየው ቸልሲ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2102 ዓም የጀርመኑን ኃያል በፍጻሜው ገጥሞ ዋንጫውን መውሰዱ ይታወሳል። በእርግጥ ግን ለባየር ሙይንሽኑ ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር ለንደን ልዩ ትዝታ ጥላበት ነው ያለፈችው። በዚህች ከተማ የዌምብሌይ ስታዲየም ቡድኑ ባየር ሙይንሽን በ2013 የፍጻሜ ግጥሚያ የገዛ ሀገሩ ተፎካካሪ ቡድን ዶርትሙንድን ገጥሞ ዋንጫውን ወስደዋል።
በሻምፒዮንስ ሊጉ ድልድል አታላንታ የገጠመው ቫለንሺያን ነው። ሊዮን ከጁቬንቱስ፤ ናፖሊ ከስፔኑ ኃያል ባርሴሎና፤ ሌላኛው የስፔን ብርቱ ሪያል ማድሪድ ከማንቸስተር ሲቲ የሚጋጠመው፤ ሲኾን በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ከተከታዩ በ10 ነጥብ ርቆ ለዋንጫ እየገሰገሰ የሚገኘው ሊቨርፑል ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ተደልድሏል። ሊቨርፑል ባለፈው የሻምፒዮንስ ሊጉ ዋንጫን ወዳነሳበት ከተማ ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም አቅንቶም ነው ዘንድሮ አትሌቲኮ ማድሪድን የሚገጥመው።
በዛሬው እለት 32ቱ የአውሮጳ ሊግ ቡድኖች ግጥሚያ እጣ ድልድልም ወጥቷል። የአውሮጳ ሊግ ውድድር በአውሮጳ የእግር ኳስ ግጥሚያ ደርጃ ከሻንፒዮንስ ሊግ ቀጥሎ በኹለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው። ልክ እንደ ሻምፒዮንስ ሊግ ኹሉ የአውሮጳ እግር ኳስ ሊጎች በምድብ ተደልድለው በጥሎ ማለፍ ወደ ዋንጫ ግስጋሴ የሚያመሩበት ነው። በከፍተኛ ደረጃ የመገናኛ ብዙኃን የሚከታተሉት መጠነ ሰፊ የማስታወቂያ ገቢ የሚገኝበትም ግጥሚያ ነው። የአውሮጳ ሊግ በ48 የአውሮጳ ቡድኖች መካከል የሚደረግ የእግር ኳስ ግጥሚያም ነው።
እስካሁን ድረስ የስፔኑ ሴቪላ ለ5 ጊዜያት የአውሮጳ ዋንጫውን ማሸነፍ ችሏል። ለሦስት ጊዜያት ዋንጫውን በመውሰድ በ2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ቡድኖች አትሌቲኮ ማድሪድ፤ ኢንተር ሚላን ጁቬንቱስ እና ሊቨርፑል ናቸው።
የጀርመኑ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ አስቀድሞ ከውድድሩ የወጣው በቱርኩ ኢስታንቡል ባዛክሴሒር ባለቀ ሰአት 2 ለ1 ተሸንፎ ነበር። በአውሮጳ ደረጃ ካለፉት ከ7ቱ የጀርመን ቡድኖች ከምድብ ውድድር ማለፍ ያልቻለው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባህ ነው። ከምድብ ጄ ውስጥ ባለቀ ሰአት ወደ ስሦስተኛ የወረደ እድለቢስ ቡድን ነው ማለት ይቻላል።
ከ40 ሺህ በላይ ታዳሚዎች በነበሩበት ስታዲየም የመጀመሪያዋን ግብ በ33ኛ ደቂቃ ላይ ያስቆጠወው ማርኩስ ቱርማን ነበር። በ44ኛው ደቂቃ ላይ ግን ኢፍራን ቻን ካህቬቺ ለኢስታንቡል አስቆጥሮ አቻ ኾኑ። ያም ኾኖ ሞይንሽንግላድባህኅ ማለፍ ይችል ነበር። ኾኖም ድንቅ የነበረው ግብ ጠባቂ ያን ዞመር በ90ኛው ደቂቃ ላይ ሊይዘው የሚገባውን ኳስ መቆጣጠር አቅቶት ከመርብ አርፋለች።
ባለፈው ሳምንት ባየር ሙይንሽንን ጉድ ያደረገው እና እስካለፈው ሳምንት ድረስ የቡንደስሊጋ የዘንድሮ መሪ የነበረውን ቡድን ማሰናበትና ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ለኢስታንቡል የማይረሳ ታሪክ ኾኖ አልፏል። የሞይንሽንግላድባኅ አሰልጣኝ ማርኮ ሮይስ
ዛሬ በቀጥታ ሥርጭት ይፋ በኾነው የ32 ቡድኖች የእጣ ድልድሉ በሁለት ሳህኖች ውስጥ ነው የተቀየጠው። የመጀመሪያው ሰሀን ላይ ከምድቡ አሸናፊ የኾኑ 12 ቡድኖች እና 4 ተጨማሪ ቡድኖች እጣ ወጥቶላቸዋል። የሚጋጠሙትም በኹለት ዙር ደርሶ መልስ ነው። በሌላኛው ሰሐን ለእጣ የየደለደሉት 16 ቡድኖች ግን አንዴ ለጥሎ ማለፍ ይጋጠማሉ። ከኹለት ወራት በኋላ የደርሶ መልስ ግጥሚያዎቹ ይከናወናሉ።
ቮልፍስቡርግ የፈረንሳዩ ሴይንት ኤቲኔን በመልስ ጨዋታ 1 ለ 0 አሽንፎ አልፏል። በመጀመሪያው ጨዋታ ያለግብ ነበር የተለያዩት። በአውሮጳ ሊግ የእጣ ድልድል ደግሞ የስዊድኑ ማልሜዮን ይገጥማል። ይኽ የደቡብ ስዊድን ቡድን ለ20 ጊዜያት የስዊድን የሊግ ዋንጫ ማሸነፍ የቻለ ቡድን ነበር።
አይንትራህኅት ፍራንክፉርት በፖርቹጋሉ ቪቶሪያ ጉዊማሬስ 3 ለ2 ተሸንፏል። ኾኖም ከምድቡ አርሰናል በቤልጂየም ሊግ አምስተኛ ደረጃ ላይ ከነበረው ሉይቲች ጋር ተጋጥሞ ነጥብ በመጋራቱ ፍራንክፉርት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችሏል። በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ፍራንክፉርት 2 ለ1 አሸንፎ ነበር። በእጣው መሠረት የሚገጥመው በኦስትሪያ ሊግ በተደጋጋሚ አሸናፊ የኾነው ዛልስቡርግን ይኾናል። ከሻምፒዮንስ ሊጉ ዝቅ ያለው ባየር ሌቨርኩሰን በአውሮጳ ሊግ የፖርቹጋሉ ፖርቶን ለመግጠም ተደልድሏል።
አትሌቲክስ
የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ሰኞ፤ ታኅሣስ 6 ቀን፣ 2012 ዓ.ም በፍል ውኃ ሆቴል መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲያከናውን በዋናነት የተሽከርካሪ ወንበር (የዊልቼር) ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንን ለማጠናከር ወሰነ። የኮሚቴው ሥራ አስፈፃሚ አባላት፣ የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን እና የክልል ፓራሊምፒክ ቢሮ ተወካዮች እና ማኅበራት በጉባዔው ተገኝተዋል።
በያዝነው የበጀት ዓመት በስልጠና እና ውድድሮች ላይ በበቂ ሁኔታ ለመሳተፍ ውሳኔ ያሳለፈው ጠቅላላ ጉባዔው በተሽከርካሪ ወንበር (የዊልቼር) ቅርጫት ኳስ ማኅበር እና የአዕምሮ እድገት ውስንነት ስፖርት ፌዴሬሽን መቋቋም እና መመስረትን እንደ አዎንታዊ ጎን ማንሳቱን በጉባዔው ታድሞ የነበረው የእግር ኳስ ስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ ለዶይቸ ቬለ (DW)በላከው አጠር ያለ ዘገባ ገልጧል።
በወቅታዊ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምክንያት ፓራሎምፒክ ኮሚቴው አምና በእቅዱ መሰረት በቂ የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት ተሞክሮ እንዳልተሳካ የፓራሎምፒክ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ስጦታው ለዶይቼ ቬሌ (DW)ተናግረዋል።
«እስከ 15 ሚሊዮን የሚደርስ ሰነድ» በማዘጋጀት የገቢ ማስገኛ ድጋፍ ለማሰባሰብ ወደ ሥራ ለመግባት በሒደት ላይ የነበረ ቢኾንም የሀገሪቱ የጸጥታ ኹኔታ ድጋፉን ለማስፈጸም እንዳላስቻላቸው ተናግረዋል።
ኮሚቴው በያዝነው ዓመት በበቂ መልኩ ዝግጅት ተደርጎ በአፍሪቃ ፓራሊምፒክ እና ጃፓን በሚስተናገደው የዓለም ፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎቱ እንዳለው ገልጧል። በውድድሩ ላይም ጥሩ ውጤት ለማምጣት በሚያስችል መልኩ ወደ ዝግጅት እንዲገባ አስፈላጊውን የፋይናንስ ትብብር ከድጋፍ ሰጪዎች ለማግኘት ማሰቡን ዐሳውቋል።
«የዊልቼር ቅርጫት ኳስን» ለማጠናከር ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ዐስታውቋል። አዲሱ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ማኅበር ሲቋቋም «አመራሩ ላይ ጥያቄ እንዳይነሳ» የአመራረጡ ግልጽነት ላይ ጥንቃቄ መደረጉን ኮሚቴው አክሎ ገልጧል።
የኮሚቴው ፕሬዝደንት አቶ ዓለም ገብረመስቀል እና ምክትል ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታደለች ዳለቾ በመሩት ጉባዔ ላይ የ15ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ቃለ-ጉባዔን ማፅደቅ፣ የ2011 የሥራ አፈፃፀም፣ የፋይናንስ፣ ኦዲት ሪፖርቶች እንዲሁም የ2012 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይቶች ተደርገዋል።
ማራቶን
የማራቶን ባለድሉ ኬኒያዊው አትሌት ኤሊውድ ኪፕቾጌ ቢቢሲ በድረ ገጽ ባከናወነው የድምፅ መስጠት ውድድር የዓመቱ ምርጥ ስፖርተኛነትን አሸንፏል። ኬንያዊው የዓለማችን የማራቶን ክብር ወሰን ባለቤት ኤሊውድ ኪፕቾጌ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ በኦስትሪያ ልዩ የማራቶን ሩጫ ከ2 ሰአት በታች በመግባት አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ የቻለ ነው። ኪፕቾጌ የማራቶን ሩጫውን በ1 ሰአት ከ59 ደቂቃ ከ40,2 ሰከንድ ነበር ያጠናቀቀው። በሪዮ ኦሎምፒክ ላይም ለንደን ውስጥ የነበረውን የራሱን ክብረ-ወሰን በመስበር የወርቅ ሜዳሊያም ባለቤት መኾን የቻለ አትሌት ነው። ኤሊውድ ኪፕቾጌ በዋና ዋና የማራቶን ሩጫ ውድድሮቹ ካስመዘገባቸው ድሎቹ መካከል የለንደን ማራቶንን ለአራት ጊዜያት ማሸነፍም የቻለ ብርቱ አትሌትነቱ ይጠቀሳል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ