1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ታኅሣሥ 8 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2011

ጠዋት ላይ ወደ ሐዋሳ በመመለስ ላይ የነበረው የሐዋሳ ቡድን ከሰአት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተጋጥሞ አቻ ተለያይቷል።  ከረዥም ጉዞ መልስ ነጥብ የተጋሩት የሐዋሳ ተጨዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል ሲያቀኑ ያሸነፉ ያኽል ሲጨፍሩ እንደነበር ተገልጧል። በላሊጋው ሐት ትሪክ የሠራው ሊዮኔል ሜሲ ኃያልነቱን አስመስክሯል።

https://p.dw.com/p/3AH5c
Bundesliga: Leipzig-Mainz
ምስል Getty Images/AFP/R. Michael

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታ ጠዋት ላይ ወደ ሐዋሳ በመመለስ ላይ የነበረው የሐዋሳ ቡድን ከሰአት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቅዱስ ጊዮርጊስ  ጋር ተጋጥሞ  አቻ ተለያይቷል።  ከረዥም ጉዞ መልስ ነጥብ የተጋሩት የሐዋሳ ተጨዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል ሲያቀኑ ያሸነፉ ያኽል ሲጨፍሩ እንደነበር ተገልጧል።   ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መገባደጃ ላይ በተለያዩ ክፍላተ ዓለም ድል ቀንቷቸዋል። በፕሬሚየር ሊጉ ሊቨርፑል የአንደጃ ደረጃውን ሲያስመልስ፤ በድል ጎዳና ሲገሰግስ የነበረው አርሰናል በሳውዝሀምተን ሽንፈት ቀምሷል። በቡንደስሊጋው ቦሩስያ ዶርትሙንድ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። በላሊጋው ሐት ትሪክ የሠራው ሊዮኔል ሜሲ ኃያልነቱን አስመስክሯል።

በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ጨዋታ በነውጠኛ ደጋፊዎች የተነሳ ስፖርታዊ ጨዋነት በተደጋጋሚ ሲደፈርስ መመልከቱ የተለመደ ይመስላል። ትናንት አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ ሊከናወን ታቅዶ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የሐዋሳ እግር ኳስ ግጥሚያ የተስተጓጎለው በዚሁ የደጋፊዎች ስፖርታዊ ጨዋነት እጦት የፈጠረው ግጭት የተነሳ ነበር። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ትናንት ሊከናወን ባለመቻሉ ዛሬ ከሰአት ዘጠኝ ሰአት ላይ ደጋፊዎች በሌሉበት በዝግ ስታዲየም ተከናውኗል። ጋዜጠኞች ግን ጨዋታውን እንዲከታተሉ ተድርጓል። የእግር ኳስ ስፖርት ጋዜጠኛ ኦምና ታደለ ጨዋታውን ከስፍራው ተከታትሏል። በስልክ አነጋግሬዋለው።

Symbolbild Selbstläufer
ምስል Colourbox

ወደ አውሮጳ እግር ኳስ ጨዋታዎች ከመሻገራችን በፊት የአትሌቲክስ ውጤቶችን በአጭሩ እናሰማችሁ። የ30 ኪ ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ትናንት  በቢሾፍቱ ደብረዘይት ለ5ኛ ጊዜ ተከናውኗል። ውድድሩን የኢትዮጵያ  አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ በስፍራው ተገኝታ ማስጀመሯን ፌዴሬሽኑ ገልጧል። ውድድሩ በወንዶች እና በሴቶች እንዲሁም በአንጋፋ አትሌቶች መካከል ነበር የተከናወነው። በሴቶች 1ኛ የወጣችው ሮዛ ደረጄ ከፌዴራል ማረሚያ ስትኾን የገባችበት ሰአትም 1:46.33 ነበር። በወንዶች የ1ኛ ደረጃውን ያገኘው ከኢት/ኤሌክትሪክ አትሌት  ፅዳት አበጀ መኾኑን ፌዴሬሽኑ በድረ ገጹ ዐሳውቋል፤ ውድድሩን ያጠናቀቀበት ሰአትም  1:31.56 ነው። ከ50 አመት በላይ በኾኑ አንጋፋ አትሌቶች በተደረገው ውድድር አትሌት አያሌው እንዳለ፤ ከ50 አመት በታች ደግሞ  አትሌት ገዛኸኝ ገብሬ 1ኛ ወጥተዋል።

በሳምንቱ መገባደጃ ላይ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተከናወኑ የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን ድል ቀንቷቸዋል። ቅዳሜ እና ኡሁድ በነበሩ ፉክክሮች ቁጥራቸው «ከ26 በላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የአለም ሃገራት በማራቶን እና አገር አቋራጭ የአትሌቲክስ ውድድሮች ውጤታማ» መኾናቸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገልጧል። በሸንዜን ማራቶን - ቻይና ሙሉ ሰቦቃ በ 2፡27.12 1ኛ ስትወጣ፤ አሹ ቃሲም 2፡38.35 በመሮጥ 3ኛ ደረጃ አግኝታለች። በተመሳሳይ የወንዶች ውድድር  በቀለ ሙሉነህ በ2፡11.19 ሰከንድ 2ኛ  ወጥቷል።  ቱርክ ውስጥ በተከናወነው የመርሲን ማራቶን ቆንጂት ጥላሁን  በ1ኛነት  አሸንፋለች። የገባችበት 2፡33.18 ነው። 2፡35.44  በመሮጥ 2ኛ የወጣችው ጫልቱ ዲዳ ናት።

በህንድ ኮልካታ 25 ኪሜ ሩጫ በወንድም በሴትም ድል ተመዝግቧል። በሴቶች ፉክክር 1ኛ ድባቤ ኩማ፤ 2ኛ ፍታው ዘርዓይ ወጥተዋል። በወንዶች ፉክክር ደግሞ 1ኛ ብርሃኑ ለገሰ ሲወጣ 2ኛ ደረጃ ያገኘው ባየልኝ ይግዛው ነው። ስፔን ውስጥ በተከናወነ የ7.6 ኪሜ የሴቶች ውድድር 1ኛ ለተሰንበት ግደይ 27፡22 እንዲሁም ሃዊ ፈይሳ በ27፡40 ሰከንድ ወጥተዋል።  በክሮስ ፌስታስ ዲላ ቨርጂን የክላ - ስፔን የ8 ኪሜ ሩጫ ደግሞ የአንደኛ ደረጃውን ኢትዮጵያዊቷ  ፀሐይ ገመቹ ይዛለች ።

እግር ኳስ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ለሊቨርፑል ተቀይሮ የገባው ሼርዳን ሻቂሪ ቡድኑ በደረጃው አናት ላይ ዳግም ጉብ እንዲል አስችሏል። በተለያዩ 22 ግጥሚያዎች አይበገሬ የነበረው አርሰናል እሁድ እለት ለሳውዝሀምፕተን እጅ ሰጥቷል።  መደበኛ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃ እስኪቀረው ድረስ አቻ የነበረው አርሰናልን በ85ኛው ደቂቃ ላይ በጭንቅላቱ ገጭቶ በማግባት 3 ለ2 ጉድ ያደረገው  ቻርሊ  አውስቲን ነው።  የየርገን ክሎፕ ቡድን ሊቨርፑል ትናንት ማንቸስተር ዩናይትድን 3 ለ1 ድል ያደረገበትን ጨምሮ ላለፉት ስድስት ተከታታይ ግጥሚያዎች አይበገሬነቱን አስመስክሯል። በሊቨርፑል ጉድ የኾኑት የማንቸስተር ዩናይትዱ አሠልጣኝ ኾዜ ሞሪኞ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።

Champions League FC Liverpool - SSC Neapel Klopp
ምስል Action Images via Reuters

በቡንደስ ሊጋው ቬርደር ብሬመንን ከትናንት በስትያ 2 ለ1 ያሸነፈው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በደረጃ ሰንጠረዡ መሪነቱን እንደጨበጠ ነው። ያለፉት ስድስት የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎቹን ያሸነፈው ባየር ሙይንሽን ባልተለመደ መልኩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ላይ በነጥብ ለመድረስ እየታገለ ነው። በቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በግብ ክፍያ ተበልጦ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባየር ሙይንሽን ከመሪው ከቦሩስያ ዶርትሙንድ በ9 ነጥብ ዝቅ ብሏል።

ባርሴሎና ሌቫንቴን 5 ለ0 ባደባየበት የላሊጋው ግጥሚያ ሊዮኔል ሜሲ ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሀት ትሪክ ሠርቷል። ያም ብቻ አይደለም ሌሎቹን ኹለት ግቦችም በማመቻቸት የምሽቱ ኮከብ ኾኖ ደምቋል። በ10 ተጨዋቾች ተጫውቶ ያለምንም ግብ የተንኮታኮተው ሌቫንቴ በ22 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የሻምፒዮንስ ሊግ 16 ቡድኖች ድልድል ዛሬ የወጣ ሲኾን፤ የእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድ የፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንጄርሜንን ይገጥማል። የጣሊያኑ ሮም ከፖርቹጋሉ ፖርቶ ጋር ተደልድሏል። የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከእንግሊዙ ቶትንሀም ሲመደብ የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ከኔዘርላንዱ አያክስ ጋር ይጋጠማል።  የስፔኑ ባርሴሎና ከፈረንሳዩ ሊዮን፤ የጣሊያኑ ጁቬንቱስ ከስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ተደልድለዋል። እጅግ አጓጊው ጨዋታ፦ የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ከጀርመኑ ሻልከ እንዲሁም ሌላኛው የጀርመኑ ባየር ሙይንሽን ከእምግሊዙ ሊቨርፑል ጋር የሚያደርጉት ግጥሚያ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ