የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ኅዳር 5 2009የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ቅዳሜ እለት ጀምሮ እሁድም ተከናውኗል። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተኪያሄዱት ጨዋታዎች አዲስ አበባ ከተማ ሐዋሳን፤ ወላይታ ዲቻ መከላከያን 2 ለ0 አሸንፈዋል። ሲዳማ ቡና ፋሲል ከነማን፣ አዳማ ድሬዳዋ ከተማን እንዲሁም ወልዲያ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 1 ለ0 ማሸነፍ ችለዋል። ጅማ አባቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። ትናንት ደደቢት ኢትዮጵያ ቡናን አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ 3 ለ0 አሸንፏል።
ጨዋታውን ስታዲየም ተገኝቶ የተከታተለው የሐትሪክ ጋዜጣ ባለቤት እና ዋና አዘጋጅ ይሳቅ በላይ ውጤቱ ያልተጠበቀ ነበር ብሏል። «ጨዋታውን በርካታ ቁጥር ያለው ተመልካች በስታዲየሙ ተገኝቶ ተከታትሎታል። ያልተጠበቀ ውጤት ነው የተመዘገበው» ያለው ይሳቅ «በጌታነህ ከበደ ሦስት ተከታታይ ግብ» ማለትም ሔትሪክ የኢትዮጵያ ቡና መሸነፉን ገልጧል።
የስፖርት ጋዜጠኛው ይሳቅ በላይ በስታዲየም ውስጥ ተመልካቾች ቡድናቸውን ሲደግፉም ኾነ ተጨዋቾች በሜዳ ውስጥ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ለስፖርታዊ ጨዋነት መደፍረስ በማይዳርግ መልኩ መኾን እንዳለበት ጠቁሟል።
የቅዳሜውን የመክፈቻ ጨዋታ እንደተከታተለ የገለጠው ሌላኛው የስፖርት ጋዜጠኛ መርሻ ወልዴ በኤፍ ኤም 96.3 ፕላኔት ስፖርት የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባ ምንጭን 3 ለ0 ያሸነፈበት ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለተመልካች ሳቢ እንዳልነበረ ጠቅሷል።
ቅዱስ ጊዮርጊስም ኾነ አርባ ምንጭ የፕሬሚየር ሊግ መክፈቻ ጨዋታ ከማድረጋቸው በፊት በደቡብ እና በአዲስ አበባ የከተማ ዋንጫ ውድድሮች ተሳትፎ አድርገው ተሸናፊ እንደነበሩ ጋዜጠኛ መርሻ ወልዴ ገልጧል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮ ኤሌክትሪክ እንዲሁም አርባ ምንጭ ከተማ ደግሞ በሲዳማ ቡና ነበር የተሸነፉት። በፕሬሚየር ሊጉ መክፈቻ ግን አርባ ምንጭ ዳግም ሽንፈት ሲገጥመው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀንቶታል። በዕለቱ ጨዋታ ዓለም አቀፍ ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው ጨዋታውን በሚገባ ተቆጣጥረው እንደዳኙ ጨዋታውን በስታዲየም የተከታተለው የስፖርት ጋዜጠኛው መርሻ ተናግሯል።
በሳምንቱ ማሳረጊያ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሪችሞንድ ማራቶን ሩጫ በወንድም በሴትም አሸናፊ መኾናቸው ተዘግቧል። በ39ኛው የሪችሞንድ ማራቶን ሩጫ በወንዶች አንደኛ የወጣው ዳዲ በየነ ውድድሩን ያጠናቀቀበት ጊዜ 2 ሰአት ከ19 ደቂቃ ከ36 ሰከንድ ነው። ብዙወርቅ ጌታነህ 2 ሰአት ከ37 ደቂቃ ከ51 ሰከንድ በማጠናቀቅ በሴቶች ፉክክር ድሉን በእጇ አስገብታለች። የግማሽ ማራቶን የወንዶች ውድድርንም ያሸነፈው ኢትዮጵያዊው ግርማ ገብሬ ነው። በተመሳሳይ ርቀት የሴቶች ውድድር አሸናፊዋ ኬኒያዊቷ ዮዋና አያባይ ናት። በውድድሩ ላይ ወደ 17,000 ያህል ሰው እንደተሳተፈ ተገምቷል።
ትናንት ብራዚል ውስጥ በተከናወነው የመኪና ሽቅድምድም የዘንድሮ ውድድር ፍጻሜ ባለድል ይኾናል ተብሎ የተገመተው ጀርመናዊ አሽከርካሪ ሳይቀናው ቀርቷል። ከሁለት ሳምንት በፊት የሚኪያሄደው የአቡዳቢ ፉክክር ድሉ ለጀመርናዊው አለያም ለብሪታንያው ተወዳዳሪ መኾኑ ይለይለታል።
ኒኮ ሮዝበርግ በብራዚሉ ሽቅድምድም 12 ነጥብ ያገኘሲኾን ዋነኛ ተፎካካሪው ሌዊስ ሐሚልተን ለአንደ ደረጃ የሚሰጠውን 25 ነጥብ ሰብስቧል። እንዲያም ኾኖ ግን በአጠቃላይ ነጥብ ኒኮ ሮዝበርግ ከሌዊስ ሐሚልተን በ12 ይበልጣል።
የዛሬ አስራ አምስት ቀን አቡዳቢ ውስጥ በሚከናወነው ውድድር ኒኮ ሮዝበርግ የዘንድሮ የፍጻሜ ባለድል ለመኾን ሦስተኛ መውጣት ብቻ ነው የሚጠበቅበት። የብሪታንያው ሌዊስ ሐሚልተን በአንደኛነት እንኳን ቢጨርስ የዘንድሮ አጠቃላይ አሸናፊ ለመኾን የመርሴዲስ አሽከርካሪው የቡድኑ አባል አራተኛ እና ከዛ በታች እንዲወጣ መጸለይ ይኖርበታል። ምናልባት የተሽከርካሪ ቴክኒክ ብልሽት ኒኮ ሮዝበርግ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር ከኾነ እድል ፊቷን ወደ ሌዊስ ሐሚልተን ታዞር ይኾናል። እንደ ኒኮ ሮዝበርግ አያያዝ ግን ያ የሚኾን አይመስልም።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ