1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ኅዳር 10 ቀን፣ 2011ዓ.ም

ሰኞ፣ ኅዳር 10 2011

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ የማለፍ እድሉን በትናንትናው ዕለት አጨናግፏል። ቡድኑ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ሲሸነፍ ቀዳሚ ግብ የተቆጠረበት ጨዋታው በተጀመረ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ደቂቃዎች ነበር። በሜዳ ቴኒስ ውድድር ዝነኛው ኖቫክ ጄኮቪች በወጣቱ ጀርመናዊ ሽንፈት ገጥሞታል።

https://p.dw.com/p/38XkS
ATP World Tour Finals in London | Finale Alexander Zverev vs. Novak Djokovic
ምስል Action Images via Reuters

ስፖርት፤ ኅዳር 10 ቀን፣ 2010 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ትናንት በሜዳው እና በደጋፊው ፊት 2 ለ0 በመሸነፍ የማለፍ ዕድሉን አጨልሟል። ብሔራዊ ቡድኑን ለሽንፈት የዳረጉት ሁለቱም ግቦች የተቆጠሩት በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ነበር። የመጀመሪያዋ ግብ ጨዋታው በተጀመረ ከሦስት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ መቆጠር ደግሞ ብዙዎችን አስደንግጣለች። ለቢቢሲ እና ለአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ድረገጾች ዘገባ አቅራቢው ኦምና ታደለን ስለጨዋታው በስልክ አነጋግሬዋለሁ።

በቻይና ሻንጋይ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያኑ ድል ሲቀዳጁ በሴቶች ፉክክር ክብር ወሰን በመስበር ነበር። 38,000 ሯጮች በታደሙበት የትናንቱ የሻንጋይ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት የብርጓል መለሰ አራጌ የማራቶን ሩጫዋን በማጠናቀቅ ወደ ሻንጋይ ስታዲየም የገባችው 2:20:37 በመሮጥ ነው። በዚህ ሰአቷም ቀደም ሲል በሀገሯ ልጅ ትዕግስት ቱፋ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 ዓ.ም ተይዞ የነበረውን የ2:21:52 ክብር ወሰን ሰብራለች። 

በተመሳሳይ የወንዶች ፉክክር ኢትዮጵያዊው ሠይፉ ቱራ አብዲዋቅ 2:09:20 ሮጦ በመግባት ድል ተቀዳጅቷል። በሻንጋዩ ውድድር በ42 ኪሎ ሜትር ማራቶን የተወዳደሩት ሯጮች 25,000 ሲኾኑ፤ ቀሪዎቹ  6,000 ሯጮች በ10 ሺህ  7,000ው ደግሞ በ5.5 ኪሎ ሜትር ተሳትፈዋል።

Symbolbild Selbstläufer
ምስል Colourbox

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የአውሮጳ ሃገራት በሚያከናውኑት የኔሽን ሊግ ግጥሚያ ዛሬ ምሽት ከኔዘርላንድ ጋር ይጋጠማል። ኔዘርላንድ ዓርብ እለት ፈረንሳይን በማሸነፏ የጀርመን ቡድን ወደ ደረጃ ቢ ዝቅ ብሏል። የጀርመን ቡድን ጌልዘንኪርሸን ቬልቲንስ አሬና ውስጥ ዛሬ የሚያከናውነው ጨዋታ የመጨረሻው ሲኾን፤ ለኔዘርላንድ ግን የመጨረሻዎቹ አራቱ አሸናፊዎች ተርታ ሊያስገባው ይችላል።

የሜዳ ቴኒስ

የ31 ዓመቱ ሠርቢያዊ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ኖቫክ ጄኮቪች በ21 ዓመቱ ወጣት ጀርመናዊ አሌክሳንደር ዝቬሬቭ ሽንፈት ገጥሞታል። ድሉ ለጀርመናዊው ወጣት በሜዳ ቴኒስ የውድድር ዘመኑ ኹሉ ታላቁ ተብሎ ተመዝግቦለታል። በቴኒስ ፕሮፌሽናሎች ማኅበር (ATP) ውድድር ለስድስት ጊዜያት ባለድል የነበረው ሠርቢያዊ በጀርመናዊው የተሸነፈው ሰፊ በሚባል ልዩነት 6-4 እና 6-3 በኾነ ውጤት ነው። አሌክሳንደር ዝቬሬቭ «ከሚታመነው በላይ ተደስቻለሁ። ይኽ መቼም ቢኾን ካሸነፍኳቸው ድሎች ትልቁ መኾኑ ግልጽ ነው» ብሏል። ጀርመናዊው የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች በትናንትና ድሉ 2 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ሀገሩ ይዞ ገብቷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ