የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ኅዳር 12 2009በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቸልሲ የአንደኛነት ደረጃውን ቅዳሜ ዕለት ነጥብ ከጣለው ሊቨርፑል ተረክቧል። ማንቸስተር ሲቲም በተመሳሳይ ነጥብ እና የግብ ክፍያ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ፍራንክፉርት ባለቀ ሰአት ብሬመንን አሸንፏል። አዲስ አበባ ላይ በተከናወኑ ጨዋታዎች ቅዳሜ እለት ኢትዮጵያ ቡና ከመከላከያ ጋር ተጋጥሞ 2 ለ2 ተለያይቷል።
ትናንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደደቢትን 2 ለ0 አሸንፏል። ይኽ ጨዋታ በብዙዎች ዘንድ የተጠበቀ ነበር። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች ምክንያት ብዙ ተመልካች ወደ ስታዲየም ላይገባ ይችላል ተብሎ ቢገመትም ስታዲየሙ ግን ሞልቶ እንደነበር የሶከር ኢትዮጵያ የስፖርት ድረ-ገጽ ዋና ኤዲተር ኦምና ታደለ ተናግሯል። ጋዜጠኛ ኦምና ታደለ ከሶከር ኢትዮጵያ ድረገጽ በተጨማሪ ለአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF)የኢትዮጵያ ዘጋቢም በመኾን ያገለግላል።
አሁን የምንሻገረው ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች አጠር ያለ ዳሰሳ ነው። በፕሬሚየር ሊጉ ፍልሚያ ቸልሲዎች እየገሰገሱ ነው። ስድስተኛ ተከታታይ ድላቸውን ትናንትና ተጎናጽፈዋል። የትናንቱን ብቸኛ ግብ የሚድልስቦሮው መረብ ላይ ያሳረፈው የቸልሲው አጥቂ ዲዬጎ ኮስታ ነው። ይኽች ግብ የጨዋታ ዘመኑ ከተጀመረ አንስቶ ለዲዬጎ ኮስታ 10ኛዋ ኾና ተመዝግባለች። ቸልሲንም በደረጃ ሰንጠረዡ ቁንጮ ላይ እንዲቀመጥ አስችላለች።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች 10 ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ሊቨርፑል ከትናንት በስትያ ሳውዝ ሐምፕተን ላይ ግብ ማስቆጠር ተስኖት ነጥብ ተጋርቷል። የሳውዝ ሐምፕተኑ ግብ ጠባቂ ፍሬዘር ፎርስተር ጀርመናዊው የርገን ክሎፕ ለሚያሰለጥኑት ሊቨርፑል አልተበገረም። በ28ኛው ደቂቃ ላይ የቀድሞ ቡድኑ አባል የነበረው ማኔ ወደ ግብ የላካትን ኳስ ፍሬዘር በድንቅ ሁኔታ ግብ ከመሆን አጨናግፏታል።
ሊቨርፑል በፊሊፕ ኮቲንሆ እና ሮቤርቶ ፊርሚኖ አማካኝነት ግብ የማስቆጠር ዕድል አግኝቶም ኳሶቹን አምክኗል። ሊቨርፑል ባየለበት የሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታም ሮቤርቶ ፊርሚኖ ሁለት ጊዜ የግብ ዕድሎች አግኝቶ ነበር። ተፎካካሪው ሳውዝ ሐምፕተንም ለሁለት ጊዜያት በቻርሊ አውስቲን በኩል ያደረጋቸው ሙከራዎች የሚጠቀሱ ናቸው።
ማንቸስተር ዩናይትድ ከአርሰናል እንዲሁም ኤቨርተን ከስዋንሲ ሲቲ ጋር 1 ለ1 ተለያይተዋል። ማንቸስተር ሲቲ ክሪስታል ፓላስን 2 ለ1 አሸንፏል። ዋትፎርድ ላይስተር ሲቲን 2 ለ1 ረትቷል። ሰንደርላንድ ከሁልሲቲ 3 ለ0፣ ቶትንሀም ዌስትሐምን 3 ለ2 እንዲሁም በርመስ ስቶክ ሲቲን 1 ለምንም አሸንፈዋል። ዌስት ብሮሚች ከበርንሌይ ዛሬ ማታ ይጫወታሉ።
በጀመርን ቡንደስ ሊጋ ጨዋታዎች ትናንት ሆፈንሀይም ከሐምቡርግ ጋር 2 ለ2 አቻ ወጥተዋል። አይንትራኅት ፍራንክፉርት ቬርደር ብሬመንን ባለቀ ሰአት 2 ለ1 ድል አድርጓል። ቅዳሜ እለት ባየር ሙይንሽን በቦሩሲያ ዶርትሙንድ 1 ለ0 ተሸንፏል። ኮሎኝ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 2 ለ1 አሸንፏል።
በዚህም መሰረት ዐርብ ዕለት ሌቨርኩሰንን 3 ለ2 ያሸነፈው ላይፕሲግ የደረጃ ሰንጠረዡን በ27 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ባየር ሙይንሽንበ24 ነጥብ ይከተላል። ኮሎኝ 21 ነጥብ አለው ሦስተኛ ነው።
እሁድ ዕለት ሕንድ ውስጥ በተከናወነው የግማሽ ማራቶን ሩጫ የሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ ወርቅነሽ ደገፋ በመግባት አንደኛ ወጥታለች። በወንዶች ውድድር ያሸነፈው በኦሎምፒክ የማራቶን ባለድሉ ኬንያዊው ኤሊዩድ ኪፕቾጌ ነው። ሁለቱም አሸናፊዎች 27,000 ዶላር ተሸላሚ ኾነዋል።
ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ሴት ተጨዋቾች በሚሳተፉበት የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽን (FIFA) ጨዋታ የጀርመን ቡድን የኮሪያ ሪፐብሊክ ተጋጣሚውን ዛሬ 2 ለ0 አሸንፏል። ጀርመን ሜክሲኮን እንዲሁም ኮሪያ ሪፐብሊክ ቬኒዙዌላን 3 ለ0 አሸንፈው ነበር ዛሬ ምድብ መ ላይ የተገናኙት።
ምድቡን ጀርመን በ9 ነጥብ ይመራል። ሜክሲኮ በ6 ይከተላል። ኮሪያ ሪፐብሊክ 3 አለው። ከምድቡ ያለምንም ነጥብ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቬኒዙዌላ ቡድን ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ