ስፖርት፤ ነሐሴ 27 ቀን፣ 2011 ዓ.ም
ሰኞ፣ ነሐሴ 27 2011በደርሶ መልስ ግጥሚያ ደቡብ አፍሪቃን ያንኮታኮተው የሌሶቶ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የፊታችን ረቡዕ ባሕር ዳር ስታዲየም ውስጥ ለዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ይገጥማል። ለየሀገሮቻቸው ቡድኖች ተሰልፈው የሚጫወቱ ተጨዋቾችን ብቻ በሚያሳትፈው የአፍሪቃ ሃገራት አሸናፊዎች (ቻን) ቅድመ ማጣሪያ ግጥሚያ ሁለቱም ቡድኖች ወደቀጣዩ ዙር ያለፉ ናቸው። በቻን የደርሶ መልስ የማጣሪያ ግጥሚያ ጅቡቲን በትግል አሸንፎ ለቀጣዩ ዙር የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተፎካካሪው አንጻር አቋሙ ምን ይመስላል? ትንታኔ ይኖረናል። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ጨዋታዎች ላይም ዳሰሳ እናደርጋለን።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ረቡዕ ነሐሴ 29 ቀን፣ 2011 ዓ.ም ባሕር ዳር ስታዲየም ውስጥ የሌሴቶ ቡድንን ለመግጠም ቀጠሮ ተይዞለታል። ልምምዱንም ሰሞኑን እዛው ባሕር ዳር ውስጥ ጀምሯል። ኳታር በምታዘጋጀው የ2022 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ውስጥ ለመግባት የቅድመ ማጣሪያ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የተጋጣሚው ሌሴቶ ቡድን አቋም ምን ይመስላል? የእግር ኳስ ስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመከላከል ላይ ተመስርቶ ግብ እንዳይቆጠርበት ጥረት ማድረግ እንዳለበት ገልጧል።
በዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች አሸናፊ የኾኑ 14 ቡድኖች ለዋናው የማጣሪያ ጨዋታ ከተመደቡት 26 ቡድኖች ጋር ተቀላልቀለው ይጋጠማሉ። እነዚህ የ40 ሃገራት ቡድኖች እያንዳንዳቸው አራት ቡድኖችን በያዙ 10 ምድቦች ተደልድለው ይጋጠሙና የየቡድኖቹ አላፊ 10 ቡድኖች የመጨረሻውን ማጣሪያ ያከናውናሉ። ከ10 ቡድኖች አሸናፊ የሚኾኑት አምስቱ የ2022 የኳታር የዓለም ዋንጫ ላይ አፍሪቃን ወክለው የሚሳተፉ ይኾናሉ።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እንደ ባለፈው የጨዋታ ዘመን ሁሉ ሊቨርፑል በመጀመሪያዎቹ የግጥሚያ ሳምንታት ቀዳሚነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ያለፈው ዙር የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ ባለድል ማንቸስተር ሲቲም በቅርብ ርቀት በመከተል ላይ ይገኛል። ማንቸስተር ሲቲ በሳምንቱ መጨረሻ ቅዳሜ ብራይተንን 4 ለ0 ድል አድጎ በ10 ነጥብ ሊቨርፑልን ይከተላል።
እስካሁን የተደረጉ አራት ግጥሚያዎችን በአጠቃላይ በድል ያጠናቀቀው መሪው ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት በርንሌይን 3 ለ0 በማሸነፍ ሙሉ 12 ነጥብ በመሰብሰብ ቀዳሚነቱን አስጠብቋል። ባለፈው ሐሙስ የአውሮጳ እግር ኳስ የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች ክብርን የተጎናጸፈው የሊቨርፑሉ ተከላካይ ቪርጂል ቫንዳይክ ጨዋታው በተጀመረ አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከባድ ስህተት ፈጽሞ ነበር። ከሎተን በርቀት የተላከችው ኳስ ለበርንሌዩ 9 ቁጥር ውድ ስትደርስ ቪርጂል ቫንዳይክ ኳሷን መቆጣጠር አልቻለም ነበር። በሪቨልፑሉ ግብ ጠባቂ ጥረት ግን ኳሷ ግብ ሳትሆን ቀርታለች። ቪርጂል ቫንዳይክ ከባርሴሎናው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ እና ከጁቬንቱሱ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር የፊፋ ምርጥ ተጨዋቾች ክብርን ለመቀዳጀት ዕድል እንዳለው ዛሬ ይፋ ኾኗል።
ለሊቨርፑል ያስቆጠሩት ሮቤርቶ ፊርሚኖ፤ ሞ ሳላህ እና ሳዲዮ ማኔ ናቸው። ሳዶ ማኔ ተቀይሮ ሲወጣ ጥቂት ቀደም ብሎ ሞ ሳላህ ነጻ ሆኖ ኳስ ስላላቀበለው በመበሳጨት እጁን ዘርግቶ በመበሳጨት ተቃውሞውን በማሳየቱ የበርካታ መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ኾኗል። ጀርመናዊው አሰልጣን ዬርገን ክሎፕ በድርጊቱ ፈገግ ብለው ሳዶ ማኔ ስሜቱን መደበቅ የማይችል መኾኑን እና ንዴቱን እንደሚረዱለትም ተናግረዋል።
ትናንት ከቶትንሀም ጋር 2 እኩል የተለያየው አርሰናል ዳግም ነጥብ ጥሏል። ቸልሲ ከትናንት በስትያ ከሼፊልድ ዩናይትድ ጋር በተመሳሳይ 2 እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። እንደ ቸልሲ አምስት ነጥብ ያለው ማንቸስተር ዩናይትድ ከሳውዝሀምፕተን ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። በ73ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ተጨዋቹን የቀይ ካርድ ሰለባ አድርጎ በ10 ተጨዋች ለተጋጠመው ሳውዝሀምተን አቻ መለያየቱ የድል ያኽል ነበር። ላይስተር ሲቲ ቦርመስን 3 ለ1 ድል አድርጎ በደመረው 8 ነጥቡ ከክሪስታል ፓላስ፤ አርሰናል፣ ኤቨርተን እና ዌስትሀም ዩናይትድ በአንድ ነጥብ ከፍ፤ ከማንቸስተር ሲቲ በ2 ነጥብ ዝቅ ብሎ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ ከኃያሉ ባየር ሙይንሽን ቀጥሎ ብርቱ ቡድን በመኾን የሚታወቀው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከታች ባደገው ዩኒየን ቤርሊን ቡድን የ3 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። የዶርትሙንድ ሽንፈት ደጋፊዎቹን እጅግ አስደንግጧል። ባየር ሙይንሽን በአንጻሩ ቅዳሜ ዕለት ማይንትስን 6 ለ1 አንኮታኩቶ ዳግም ኃያልነቱን አስመስክሯል።
የባየር ሙይንሽኑ አጥቂ ጄሮም ቦአቴንግ ወደ ጁቬንቱስ እንደማያቀና ዛሬ ይፋ ኾኗል። ቀደም ሲል በጀርመንኛ ቋንቋ የሚታተመው «ቢልድ» ጋዜጣ እና »ስካይ» የባየር ሙይንሽኑ ተከላካይ ወደ ጣልያኑ ጁቬንቱስ ሊያቀና እንደኾነ ዘግበው ነበር። በርካታ የባየር ሙይንሽን ደጋፊዎች የቡድናቸው እና የብሔራዊ ቡድኑ ተከላካይ ከባየር ሙይንሽን እንዳይሄድ መማጸናቸውም ተሰምቶ ነበር። ጄሮም ቦአቴንግ ከባየር ሙይንሽን ጋር የገባው ውል ሊጠናቀቅ ከ21 ወራት በላይ ይቀሩታል።
አትሌቲክስ
ሞሮኮ ራባት ከተማ ውስጥ በተከናወነው የመላው አፍሪቃ ጨዋታዎች ተሳታፊ የኾነው የኢትዮጵያ ቡድን ትናንት ወደ ሀገር ቤት ሲገባ አቀባበል ተደርጎለታል። ቡድኑ በ12ኛ የመላ አፍሪቃ ጨዋታ ኢትዮጵያን በ13 የስፖርት አይነቶች ወክሎ የተወዳደረ ሲኾን፤ በአጠቃላይ 6 ወርቅ፣ 5 ብር፣ 12 ነሐስ፣ በድምሩ 23 ሜዳልያ በማስመዝገብ የ9ኛ ደረጃ ይዞ ተመልሷል። ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን፣ 2011 ዓ. ም ማለዳ ላይ በአዲስ አበባ ስቴድዮም ደማቅ አቀባበል እንደተደረገለት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሩ ዘግቧል።
በሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ የዓለማችን ምርጡ ተወዳዳሪ ኖቫክ ጄኮቪች በደረሰበት ጉዳት ከዩናይትድ ስቴትስ ውድድር ማቋረጡ ተዘግቧል። ሠርቢያዊው የሜዳ ቴንስ ዕውቅ ተጨዋች ጉዳት የደረሰበት ከስዊትዘርላንዳዊው ስታን ዋውሪንካ ጋር ባደረገው አራተኛ ዙር ግጥሚያ ነበር። በሴቶች የሜዳ ቴኒስ ውድድር የ37 ዓመቷ አሜሬካዊት ሴሬና ዊሊያምስ ፔትራ ማርቲችን 6-3 እና 6-4 በኾነ ውጤት አሸንፋ ለሩብ ፍጻሜ ደርሳለች። ሴሬና በደረሰባት ጉዳት ሕክምና አግኝታ በመጋጠም ነበር ያሸነፈችው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ