ስፖርት እና የወጣቱ ሥነ-ምግባር
ዓርብ፣ ጥቅምት 8 2006የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ባለፈው እሁድ የተካሄደውን ጨዋታ ከአንጋፋው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ጋ በራሳቸው ሀገር እና ስታዲዮም መመልከት መቻላቸው ትልቅ ኩራት እና ስሜት ፈጥሯል። የዛኑ ያህል በሳላዲን ሰይድ አማካኝነት የገባው ግብ ሲሻር፤ በደጋፊዎች ዘንድ ከብስጭት ያለፈ የሥነ ስርዓት ጉድለት ተስተውሏል። ጨዋታውን ለመከታተል እሁድ ማለዳ ወደ አዲስ አበባ ስታዲዮም ያመራው -አብነት ገላን ከነበረው ድባብ ጀምሮ የታዘበውን ገልፆልናል። አብዛኛዉ ወጣት ወደ ስታዲዮሙ ለመግባት ፍላጎት ስለነበረውም ግፊያና ግርግር ከቦታው አልጠፋም። በቲኬት አቆራረጥ ላይ መሻሻል ሊደረግ ቢቻል ለችግሩ መፍትሄ ሊሆን ይችላል ባይነዉ አብነት።
የእግር ኳስ አፍቃሪ የሆነዉ ወጣት እስከዛሬ የሌላ ሀገር የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊ ነበር። ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማለፉ እና ለዓለም ዋንጫ ፉክክር ወደ ብራዚል ለመጓዝ መቃረብ፤ በወጣቱ ዘንድ ያሳደረዉ ስሜት ከፍተኛ ነዉ። ወጣት ፀጋ በርኪሳ የእግር ኳስ አፍቃሪ ብትሆንም ጨዋታውን ከቤቷ ሆና ነው የተመለከተችው። ለምን? ነግራናለች።
ለእሁዱ ጨዋታ በማልያ ሽያጭ እረፍት አጥቶ የነበረው ወጣት ነጋዴ -መሀመድ ሙሳ ደግሞ ሽያጩ ከግጥሚያውም በኋላ እንደቀጠለ ነው ይላል። ከስታዲዮም እና የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሌላ ብዙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ማልያ የለበሱ የእግር ኳስ ደጋፊዎች የተስተዋሉበት ስፍራ የሚሊየም አዳራሽ ነው። ወጣት ሚሊዮን ብስራት ጨዋታውን በዚህ አዳራሽ ነው ለመከታተል የወሰነው።
እንደ ሚሊዮን ገለፃ፤በአዳራሹ ብዙም ሰው ቢገኝም በአጠቃላይ የእግር ኳስ አፍቃሪዎቹ መልካም ሥነ ምግባር ባለው መልኩ ጨዋታውን ተከታትለዋል።
ብዙአየሁ ዋጋው የኢንተር ስፖርት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነው። ወጣቱ ጋዜጠኛ ግጥሚያውን ሊመለከት ብቻ ሳይሆን ስለጨዋታው ሊዘግብም በስታዲዮሙ ተገኝቷል። እሱም የታዘበውን አጫውቶናል። በስፖርት በተለይም በእግር ኳስ ጨዋታ አፍቃሪዎች ዘንድ የታየዉን የሥነ ምግባር ሁኔታ የቃኘንበት የወጣቶች ዓለም ዝግጅት የድምፅ ዘገባን ከዚህ በታች ያገኙታል።
ልደት አበበ
አርያም ተክሌ