1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት ከእግር ኳስ እስከ ቴኒስ

ሰኞ፣ መጋቢት 10 2004

የአውሮፓ እግር ኳስ አንድም የቦልተን ወንደረርስ የመሃል ሜዳ ተጫዋች የፋብሪስ ሙዋምባ በልብ ድካም ተዝለፍልፎ መውደቅ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለፓናቴናኢኮስና ለኦሊምፒያኮስ ፒሬውስ ግጥሚያ መቋረጥ ምክንያት በሆነ ከባድ የተመልካች ዓመጽ ሳቢያ አስከፊ ሰንበት ነው ያሳለፈው።

https://p.dw.com/p/14MvU
ምስል Reuters

የአውሮፓ እግር ኳስ አንድም የቦልተን ወንደረርስ የመሃል ሜዳ ተጫዋች የፋብሪስ ሙዋምባ በልብ ድካም ተዝለፍልፎ መውደቅ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለፓናቴናኢኮስና ለኦሊምፒያኮስ ፒሬውስ ግጥሚያ መቋረጥ ምክንያት በሆነ ከባድ የተመልካች ዓመጽ ሳቢያ አስከፊ ሰንበት ነው ያሳለፈው። ቢሆንም ከእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እስከ ፖርቱጋል ሻምፒዮና ውድድሩ በሙሉ ተካሂዷል።

በፋብሪስ ሙዋምባ ልብ ድካም በድንጋጤና በሃዘን በተዋጠው በእንግሊዝ ፕሬሞየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ዎልቨርሃምፕተን ወንደረርስን 5-0 አሸንፎ አመራሩን ወደ አራት ነጥቦች ማስፋቱ ተሳክቶለታል። ለማኒዩ ከአምሥት ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረው ሜክሢካዊ አጥቂው ሃቪዬር ሄርናንዴስ ነበር። በእንግሊዝ ፌደሬሺን ዋንጫ FA ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ በተካሄዱት ግጥሚያዎች ደግሞ ቼልሢይ ላይሴስተር ሲቲይን 5—2 ሲረታ ሊቨርፑል ስቶክ ሲቲይን 2-1 አሸንፏል። ኤቨርተንና ሰንደርላንድ ደግሞ 1-1 ተለያይተዋል።

አራተኛው የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ በቦልተን ወንደረርስና በቶተንሃም ሆትስፐር መካከል ሊካሄድ የታቀደው ነበር። ይሁንና በቦልተኑ የመሃል ሜዳ ተጫዋች በፋብሪስ ሙዋምባ በልብ ድካም መውደቅ የተነሣ ገና በመጀመሪያ አጋማሹ ነበር የተቋረጠው። የ 23 ዓመቱ ወጣት በሜዳ ውስጥ የሃኪሞች ዕርዳታ ተደርጎለት ወደ ሆስፒታል በመወሰድ ላይ እንዳለ መልሶ መተንፍስ ቢጀምርም የክለቡ አሰልጣኝ ኦወን ኮይል እንደገለጸው አሁንም ገና በአደገኛ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው።

«የፋብሪስ ሕመም በጣም አሳሳቢ ነው። የሚቀጥሉት 24 ሰዓታት ወሣኝ የሚሆኑ ይመስለኛል። በሃሣባችንና በጸሎታችን ከርሱ ጋር ነን። እንደ ሌሎች ብዙዎች ሁሉ እንዲያገግም የምንመኝ ሲሆን እግዜር በበጎ እንዲያሳልፍለት ነው ጸሎታችን»

የእንግሊዝ ከ 21 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች የነበረው ሙዋምባ በወቅቱ በለንደን የልብ ሕክምና ሆስፒታል የቅርብ ክትትል እየተደረገለት ሲሆን ሰንበቱን በርካታ የፕሬሚየር ሊጉ ተጫዋቾችና ክለቦች የድጋፍ መልዕክት አስተላልፈውለታል። በነገራችን ላይ ሙዋምባ በትውልዱ የዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ ሰው ነው። በፕሬሚየር ሊጉ ውድድር ማንቼስተር ዩናይትድ አሁን ሊጋውን በ 70 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ማንቼስትር ሲቲያ አንድ ጨዋታ ጎሎት በ 66 ነጥቦች ሁለተኛ ነው። በጎል አግቢነት የአርሰናሉ ሮቢን-ፋን-ፕርሲ 26 አስቆጥሮ ይመራል።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ቀደምቱ ሬያል ማድሪድ ለዚያውም በቤርናቤው ስታዲዮሙ ከማላጋ በ 1-1 ውጤት በመወሰኑ አመራሩ ከአሥር ወደ ስምንት ሊያቆለቁል በቅቷል። ሬያል ካሪም ቤንዜማ በ 35ኛዋ ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ጎል ሲመራ ከቆየ በኋላ ሣንቲ ካዛሮላ ለማላጋ ውጤቱን ያስተካከለው በመጨረሻዋ ደቂቃ ላይ ነበር። ሁለተኛው ባርሤሎና ሴቪያን 2-0 ሲያሸንፍ ሬያልን ቀረብ ማለቱ ሆኖለታል። በጎል አግቢነት የሁለቱ ክለቦች ከዋክብት ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በ 32፤ እንዲሁም ሊዮኔል ሜሢ በ 31 ተከታትለው ይመራሉ።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቀደምቱ ክለቦች በሙሉ ሰንበቱን በማሸነፍ ሲያሳልፉ ቦሩሢያ ዶርትሙንድ በአምሥት ነጥቦች ብልጫ መምራቱን እንደቀጠለ ነው። ዶርትሙንድ ብሬመንን 1-0 ሲረታ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረውም ጃፓናዊ አጥቂው ሺንጂ ካጋዋ ነበር። ክለቡ ያለፉትን ሃያ ግጥሚያዎቹን ያላንዳች ሽንፈት ሲያሳልፍ አሰልጣኙ ዩርገን ክሎፕ እንዳለው በሰንበቱ ጨዋታ ብዙ ጎሎችን ማግባት በተቻለውም ነበር።

«እጅግ ትግል የተመላው ጨዋታ ነበር። ከነበረን በዙ የጎል ዕድል የተወሰነውን ተጠቅመን ቢሆን ጨዋታው ቀድሞ በለየለት ነበር። ግን አልሆነም፤ ብሬመን ዕድሉን ይዞ ሊቆይ ችሏል። በበኩላችን ጥሩ ተጫውተን ግሩም ጎል አስቆጥረናል። ግን አንዲት ጎል ብቻ!እናም እስከ መጨረሻው ድረስ ብሬመንም ጎል ለማግባት እንደሚችል ማሰብ ነበረብን»

ለማንኛውም ሁለተኛው ባየርን ሙንሺን በበኩሉ ግጥሚያ በርሊንን 6-0 ሲረታ ጠንካራው የዶርትሙንድ ተፎካካሪ እንደሆነ ይቀጥላል። ክለቡ ባለፉት ሶሥት ግጥሚያዎቹ ብቻ ሃያ ጎሎችን ማስቆጠሩ ነው። ከዚሁ ሌላ ግላድባህ ሌቨርኩዝንን 2-1 አሸንፎ ሶሥተኛ ሲሆን ሻልከም ካይዘርስላውተርንን 4-1 በመርታት አራተኛ ነው። በጎል አግቢነት የባየርኑ ማሪዮ ጎሜስ 22 አስቆጥሮ ይመራል።

የቡንደስሊጋው ውድድር ይዞታ ከሞላ-ጎደል ይህን የመሰለ ሲሆን በዚህ ሣምንት አጋማሽ ደግሞ የፌደሬሺኑ ዋንጫ ግምሽ ፍጻሜ ግጥሚያዎች በታላቅ ጉጉት ይጠበቃሉ። በውድድሩ ከቀሩት ከመጨረሻዎቹ አራት ቡድኖች ሶሥቱ ቀደምቱ የቡንደስሊጋ ክለቦች ሲሆኑ አንዱ የሁለተኛው ዲቪዚዮን ቁንጪ ግሮይተር ፉርት ነው። ያሄው ፉርት በነገው ምሽት ከሊጋው ሻምፒዮን ከዶርትሙንድ ጋር የሚጋጠም ሲሆን የማለፍ ዕድል ይኖረዋል ብለው የሚገምቱት ጥቂቶች ናቸው። ሆኖም በፌደሬሺኑ ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ውድድር ትንሹ ትልቁን ማንበርከክ መቻሉ የተለመደ መሆኑም መዘንጋት የለበትም።

Bundesliga 26. Spieltag Borussia Dortmund Werder Bremen
ምስል AP

ከባዱ ግጥሚያ እርግጥ በማግሥቱ ረቡዕ በባየርን ሙንሺንና በግላድባህ መካከል የሚካሄደው ነው። ግላድባህ በወቅቱ የቡንደስሊጋ ውድድር ሁለቴ ባየርንን ሲያሸንፍ ድሉን ሊደግመው ነው የሚመኘው። ለማስታወስ ያህል ባየርንን እስካሁን በአንድ የውድድር ወቅት ውስጥ ሶሥቴ ያሸነፈ ክለብ ለነገሩ የለም። እናም ግላድባህ ተሳክቶለት ከፍጻሜ ከደረሰ ከ 17 ዓመታት ወዲህ ትልቅ ዕርምጃው ይሆናል።

በኢጣሊያ ሶሪያ-አ ኤሲ ሚላንና ጁቬንቱስ በአራት ነጥቦች ልዩነት ተከታትለው መምራታቸውን ሲቀጥሉ በፈረንሣይም ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ቀደምቱ እንደሆነ ነው። በተረፈ በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶ፤ በኔዘርላንድም አልክማር ይመራሉ። ሰንበቱ እርግጥ በግሪክ ሻምፒዮና ከስፖርት መንፍስ የራቀ ዓመጽ የሰፈነበት ሆኖም ነበር ያለፈው። የታላላቆቹ ክለቦች የፓናቴናኢኮስና የኦሊምፒያኮስ ፒሬውስ ግጥሚያ በተመልካቾች ዓመጽ ሁለቴ ከተቋረጥ በኋላ የኋላ ኋላ መሰረዙ ግድ ሆኗል።

የፓናቴናኢኮስ ደጋፊዎች የእሳት ቃጠሎዎችን ሲያስነሱ ይህንኑ ለማጥፋት የእሣት አደጋ መከላከያ ሃይል እንዲጠራ አስገድዶ ነበር። ከዚሁ ሌላ ተመልካቾች በፖሊሶች ላይ ፍንጂ በመወርወር ዓመጹን ሲያባብሱ ዕለቱ ለግሪክ ስፖርት የሃፍረት ሆኖ ነው ያለፈው።

አትሌቲክስ

Die olympischen Ringe
ምስል picture-alliance/Sven Simon

በትናንቱ ሰንበት በዓለም ዙሪያ የማራቶን ሩጫ ውድድሮች ሲካሄዱ እነዚህም እንደተለመደው የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ሃያል ሆነው የታዩባቸው ነበሩ። በሮማ ማራቶን በወንዶች ኬንያዊው ሉካ-ሎኮቤ-ካንዳ በሁለት ሰዓት ከስምንት ደቂቃ አራት ሴኮንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሌላው ኬንያዊ ሳምሶን ኪፕሮኖ ሁለተኛ ወጥቷል። ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመው የኢትዮጵያው ተወዳዳሪ ደምሰው አበበ ነበር። በሴቶችም ድሉ የኬንያዊቱ የሄለን ኪሙታይ ሲሆን ኢትዮጵያዊቱ አሸቴ ዲዶ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ሩሢያዊቱ ማሪና ኮቫልዮቫ ሶሥተኛ ውጥታለች።

በሶውል ማራቶንም በወንዶች አምሥት ኬንያውያን ግንባር-ቀደም ሲሆኑ ማንም ያልጠበቀው ዊልሰን ኤሩፔ በሁለት ሰዓት ከአምሥት ደቂቃ 37 ሶኮንድ ጊዜ በማሸነፍ ታዛቢዎችን አስደንቋል። ሩጫውን በሁለተኝነት የፈጸመው ጀምስ-ኪፕሳንግ-ኩዋምባይ ነበር። በሴቶች ኢትዮጵያዊቱ ፈይሴ-ቦሩ-ታደሰ ስታሸንፍ አስካለ መገርሣም ሁለተኛ ወጥታለች።

ከዚሁ ሌላ በሎስ አንጀለስ የሴቶች ማራቶን የኢትዮጵያ ተወዳዳሪ ፋጡማ ሳዶ ስታሸንፍ በወንዶች የኬንያ አትሌቶች ሲሞን እንጆሮጌና ዌልደን ኪሩዊ በመከታተል ለድል በቅተዋል። ባለፈው አርብ የኢየሩሣሌም ማራቶን ደግሞ በውንዶች ኬንያዊው ዴቪድ ቶኒዮክ ጉደታ ቢራቱን አስከትሎ ሲያሸንፍ በሴቶች ምሕረት አናሞ የኢትዮጵያን ድል አረጋግጣለች። በኢየሩሣሌሙ ማራቶን 15 ሺህ ሯጮች ሲሳተፉ 1,500 የውጭ ተወዳዳሪዎች የተካፈሉበትም ነበር።

የአውቶሞቢል እሽቅድድም

Formel 1 GP Großer Preis von Australien 2012 Button
ምስል Reuters

የዘንድሮው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል ውድድር ትናንት አውስትራሊያ ውስጥ በተካሄደ እሽቅድድም ተጀምሯል። በአውስትራሊያው ግራንድ-ፕሪ የብሪታኒያው ጄንሰን ባተን አሸናፊ ሲሆን ያለፈው ዓመት ሻምፒዮን ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል ሁለተኛ ወጥቷል። ሌላው የብሪታኒያ ተወዳዳሪ ሉዊስ ሃሚልተን ደግሞ ሶሥተኛ ሲሆን ማርክ ዌበር ግን በአገሩ አሸናፊ ለመሆን ያደረገው 11ኛ ሙከራም አልሰመረለትም። በአራተናኝነት ተውስኗል። በተቀረ የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ አምሥተኛ ሲወጣ ጃፓናዊው ካሙኢ ኮባያሺም ስድሥተኛ ሆኗል።

ቴኒስ

Sport Tennis Victoria Azarenka und Maria Sharapova Australian Open
ምስል AP

በኢንዲያን ዌልስ-ካሊፎርኒያ ሲካሄድ የሰነበተው ታላቅ የቴኒስ ውድድር ትናንት እጅግ በደመቁ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ተጠናቋል። በውንዶች የስዊሱ ተወላጅ ሮጀር ፌደረር አሜሪካዊ ተጋጣሚውን ጆን ኢስነርን ፍጹም ስክነት በታየበት በለየለት ሁኔታ 7-6,6-3 በማሸነፍ ባልድል ሆኗል። በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ሶሥተኛ የሆነው ፌደረር ለፍጻሜ የደረሰው በግማሽ ፍጻሜው ሁለተኛውን ራፋኤል ናዳልን ረትቶ ሲሆን የትናንቱን ግጥሚያ በድል ለመፈጸም አንድ ሰዓት ከ 21 ደቂቃ ከሆነ ጊዜ በላይ አላስፈለገውም። ጆን ኢስነርም የዓለም አንደኛውን ሰርቢያዊ ኖቫክ ጆኮቪችን በግማሽ ፍጻሜው ሲያሰናብት በፍጻሜው ስኬት እንደሚያገኝ በዙዎች ገምተው ነበር። ለማንኛውም ለፌደረር የትናንቱ ድል በስምንት ውድድሮች ስድሥተኛው መሆኑ ነው።

በሴቶች በዓለም የማዕረግ ተዋርድ ላይ አንደኛ በሆነችው በቤላሩሷ በቪክቶሪያ አዛሬንካና በሁለተኛዋ በሩሲያዊቱ በማሪያ ሻራፖቫ መካከል የተካሄደው ፍጻሜ ግጥሚያም በፊተኛዋ አሸናፊነት ተፈጽሟል። አዛሬንካ በቀላሉ 6-2,6-3 በሆነ ውጤት ስታሸንፍ ይህም በዚህ ዓመት አራተኛ የውድድር ድሏ መሆኑ ነው። የ 22 ዓመቷ አዛሬንካ ባለፈው ጥር በአውስትሬሊያን-ኦፕን ለመጀመሪያ ግራንድ-ስላም ድሏ የበቃችውም ሻራፖቫን በማሸነፍ እንደነበር ይታውሳል። በወንዶች ጥንድ ማርክ ሎፔዝና ራፋኤል ናዳል ከስፓኝ የአሜሪካ ተጋጣሚዎቻቸውን ጆን ኢስነርንና ሳም ኩዌሪያን በሁለት ምድብ ጨዋታ አሸንፈዋል።

በቢስክሌት እሽቅድድም ለማጠቃለል ባለፈው ቅዳሜ ኢጣሊያ ውስጥ ተሃሂዶ በነበረው ከሚላኖ ሣን ሬሞ 103ኛ ውድድር የአውስትራሊያው ተወዳዳሪ ሳይመን ጌራንስ አሸናፊ ሆኗል። ጌራንስ 298 ኪሎሜትሩን ርቀት በሰባት ሰዓት ያህል ጊዜ ከኋላው አስቀርቶ ለድል የበቃው በመጨረሻ የስዊሱን ፋቢያን ካንቼሬላን ቀድሞ መግቢያውን መስመር ካቋረጠ በኋላ ነው። ጌራንስ በዚሁ ያለፈውን ሻምፒዮን የአገሩን ልጅ የማት ጎስን ቦታ ለመያዝ በቅቷል። ለአውስትራሊያዊው ቢስክሌተኛ ይሄው ታላቁ የአንድ ቀን እሽቅድድም ድሉ መሆኑ ነው።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ