1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

​​​​​​​ስፖርት፤ የካቲት 12 ቀን፣ 2010 ዓ.ም.

ሰኞ፣ የካቲት 12 2010

በነገው ዕለት ለንደን ስታምፎርድ ብሪጅ ውስጥ በግርማ ሞገስ ከሚንጎማለለው የዓለማችን ዕውቁ የኳስ ጠቢብ ሊዮኔል ሜሲ በርካቶች ብዙ ይጠብቃሉ። በ619 ግጥሚያዎች ለባርሴሎና 534 ኳሶችን ከመረብ ያሳረፈው አርጀንቲናዊ አጥቂን ግን በስታምፎርድ ብሪጅ የሚጠብቀው የእነሴስ ፋብሬጋስ ቸልሲ ነው።  

https://p.dw.com/p/2swaZ
Pyeongchang Olympia Snowboard Big Air Reira Iwabuchi
ምስል Getty Images/M. Hangst

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በነገው ዕለት ለንደን ስታምፎርድ ብሪጅ ውስጥ በግርማ ሞገስ ከሚንጎማለለው የዓለማችን ዕውቁ የኳስ ጠቢብ ሊዮኔል ሜሲ በርካቶች ብዙ ይጠብቃሉ። በ619 ግጥሚያዎች ለባርሴሎና 534 ኳሶችን ከመረብ ያሳረፈው አርጀንቲናዊ አጥቂን ግን በስታምፎርድ ብሪጅ  የሚጠብቀው የእነሴስ ፋብሬጋስ ቸልሲ ነው።  ቸልሲ ከባርሴሎና ጋር ለሻምፒዮንስ ሊግ የሚያደርገው የነገው ማታ ግጥሚያ በጉጉት ይጠበቃል። በሩዋንዳው የአፍሪቃ የብስክሌት ውድድር ኢትዮጵያ የሁለተኛ ደረጃን አግንታለች፤ በሜዳሊያ ብዛት ቀዳሚ ኾና የአጠቃላይ ውድድሩ አሸናፊ የኾነችው ኤርትራ ናት። አዘጋጇ ሀገር የሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች። 

ሻምፒዮንስ ሊግ

ነገ ማታ በተመሳሳይ ሰአት የሻምፒዮንስ ሊግ ሁለት ጨዋታዎች ይኖራሉ። የጀርመኑ ባየር ሙይንሽን ከቱርኩ ቤሺክታስ ኢስታንቡል ጋር በሚጫወትበት ሰአት የስፔኑ ኃያል ባርሴሎና የእንግሊዙን ቸልሲ ይገጥማል።  ታዲያ አንድ አስገራሚ ነገር አለ። ባርሴሎና እና ቸልሲ ባደረጉት ስምንት ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈው ሊዮኔል ሜሲ አንድም ጊዜ ቸልሲ ላይ ግብ አስቆጥሮ ዐያውቅም። 

በእርግጥ ከባርሴሎና ጋር ባደረገው ጉዞው በ619 ግጥሚያዎች 534 ኳሶችን ከመረብ ማሳረፍ የቻለ ይኽ አስደናቂ የእግር ኳስ ተጨዋች ሰማያዊዎቹ ላይ ሲኾን አንዳችም ግብ ማስቆጠር ምነው ተሳነው? ባርሴሎና ከሌሎች ተቀናቃኞቹ ጋር ካደረጋቸው ግጥሚያዎች ሁሉ እንደ ቸልሲ የፈተነው የለም። የስፔን ኃያሉ ባርሴሎና ከቸልሲ ጋር ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች አንዱንም ማሸነፍ አልቻለም። ለአምስት ጊዜያት ሁለቱ ቡድኖች አቻ የወጡ ሲኾን፤ ለሁለት ጊዜያት ቸልሲ በሜዳው ባርሴሎናን 1 ለ0 አሸንፏል። እናስ በነገው ጨዋታ ባርሴሎና ለዓመታት ከለመደው የተለየ ያደርግ ይኾን? ነገ ማታ የምናየው ይኾናል።

Lionel Messi
ምስል picture-alliance/AP Photo/F. Seco

በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ 2 ሰአት ከ45 ደቂቂቃ የሚጀምረው የባየር ሙሽይንሽን እና የቤሺክታሽ ኢስታንቡል ግጥሚያ ብዙዎች ለ20 ዓመታት ወደ ኋላ በምናብ እንዲነጉዱ አድርጓል። ግጥሚያው በተለይ ለቱርካውያን በልዩ ዐይን የሚመለከቱት ነው።

የዛሬ 20 ዓመት ብዙዎች የማይረሱት ክስተት «የአልዲ ቅሌት» ተብሎ ዛሬም ይታወሳል። አልዲ ጀርመን ውስጥ ርካሽ ዕለታዊ ሸቀጦች እና የምግብ ውጤቶች የሚሸጡበት ግዙፍ የሸቀጥ መደብር ነው።

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር መስከረም ወር 1997 ነው። በወቅቱ በነበረው ባየር ሙይንሽ እና ቤሺክታሽ ኢስታንቡል ለአውሮጳ ዋንጫ የዙር ጨዋታ ያደረጉት ብቸኛ ግጥሚያ ጀርመን እና ቱርክን ዲፕሎማሲያዊ አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ አንዳች ነገር አስከትሏል።

ክስተቱ የሚከተለው ነበር። የባየር ሙይንሽን የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች አንድ ሚሊዮን የቴሌቪዥን ተመልካቾች ፊት ኦሎምፒያ ስታዲየም ውስጥ ታድመዋል። ለቱርኩ ቡድን ያደረጉት አቀባበል ግን ደስ የማይል ነበር። ደጋፊዎቹ ርካሽ ዋጋ ያላቸው የአልዲ የላስቲክ ከረጢቶችን ከፍ አድርገው በመያዝ ታይቷል።

ደጋፊዎቹ ያዘጋጁት ተለቅ ያለ የጽሑፍ ማስታወቂያም «አልዲ ለደምበኞቹ ሠላምታ ያቀርባል» ሲል ይነበባል። ደጋፊዎቹ ያን ያደረጉት ጀርመን ውስጥ የሚኖሩ የቱርክ ዜጎች ርካሽ ዋጋ ያላቸውን ሸቀጦች ከአልዲ ይገዛሉ ሲሉ በዘረኝነት መንፈስ ለመሳለቅ ነበር። በዚያ ላይ አንዳንድ ደጋፊዎች «ወደ አልዲ ማቅናት ትችላላችሁ» እያሉ ሲዘምሩም ተደምጠዋል። ይኽ ደስ የማይል አቀባበል ለቀናት የመወያያ ርእስ ኾኖ መቆየቱ አጠያያቂ አልነበረም። 

Fußball FC Bayern München - Besiktas Istanbul
ምስል picture-alliance/dpa/F. Leonhardt

ኹሪዬት የተሰኘው ከፍተኛ ተነባቢነት ያለው የቱርኩ ትልቊ ጋዜጣ፦ «ዘረኝነት ከመድረኩ»ሲል ኪከር የተባለው የጀርመን የስፖርት ጋዜጣ በበኩሉ፦ «በወንጀል የተዋጠ ደነዝነት» ሲል ኹኔታውን ገልጦታል።

ፖለቲከኞችም የሰላ ትችታቸውን ሠንዝረዋል። በወቅቱ የምክር ቤት አባል የነበሩት፤ የቱርክ ዝርያ ያላቸው ጀርመናዊው የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ፖለቲከኛ ቼም ኦይትስዴሚር ቊጣቸውን በይፋ ከገለጹት ውስጥ ይገኛሉ። «እዚህ ያሉ ሁለት ሚሊዮን ቱርካውያን በዓለም ፊት ተሰድበዋል፤ እናም ይኽ በጀርመን የሚኖሩ ቱርካውያን ላይ በመላ ያነጣጠረ ነው» ሲሉ በርሊነር ሳይቱንግ በተባለው ጋዜጣ ላይ አጥብቀው ተችተዋል።

በያኔው ጨዋታ ቤሺክታስን 2 ለ0 ያሸነፈው ባየር ሙይንሽን ቡድን አኹን በብዙ መልኩ ተቀይሯል። እንደውም ባየር ሙይንሽን በጸረ ዘረኝነት እና መጤ ጠል ጥላቻን በመታገል ላደረገው ጠንካራ ዘመቻው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 ዩሊዩስ ሒርሽ የተሰኘውን የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ሽልማት አሸንፏል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ባየር ሙይንሽን ቢያንስ ለሩብ ፍጻሜ መድረስ ችሏል። ባለፈው ዓመት ግን በደርሶ መልስ የ6 ለ ለ3 ውጤት ከሩብ ፍጻሜው የተሰናበተው በሪያል ማድሪድ ነበር። 

ለዚሁ የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ከነገ በስትያ የእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድ እና የስፔኑ ሴቪላ ተቀጣጥረዋል። የጣሊያኑ ሮማ እና የዩክሬኑ ሻካታር ዶኒዬትስክም ረቡዕ በተመሳሳይ ሰአት ከምሽቱ 2 ሰአት ከ45 ደቂቂቃ ላይ ይጋጠማሉ።

ለእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲ ከዊጋን ጋር ዛሬ ምሽት ይጋጠማል።  ቶትንሐም ትናንት ከሮሽዳሌ ጋር ተጫውቶ ሁለት እኩል ተለያይቷል። ቅዳሜ ዕለት ማንቸስተር ዩናይትድ ሑደርስፌልድን 2 ለ0 ሲረታ፤ ኮንቬንትሪ በብሪንግቶን 3 ለ1 ተሸንፏል።

5. Bildergalerie Sportfoto des Monats Januar 2018
ምስል Reuters/V. West

በጀርመን ቡንደስሊጋ እግር ኳስ ዛሬ ማታ ላይፕሲሽ ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር ይጋጠማል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትናንት ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን  1 ለ0 ድል አድርጓል። አውስቡርግ በሽቱትጋርት 1 ለ0 ተሸንፏል። ሻልከ ሆፈንሀይምን እንዲሁም ባየር ሌቨርኩሰን ሐምቡርግን በተመሳሳይ 2 ለ1 አሸንፈዋል። ኮሎኝ ከሐኖቨር ጋር አንድ እኩል አቻ የወጣበት የዳኛ ውሳኔ አወዛግቧል። ክላውዲዮ ፒዛሮ ያስቆጠረው ሁለተኛ ግብ የቪዲዮ መረጃ ከታየ በኋላ ተሽሯል። 14 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ መጨረሻ 18ኛ ለኾነው የኮሎኝ ቡድን በባከነ ሰአት የተገኘችው ግብ መሰረዟ ደጋፊዎቹን አስቆጥቷል፤ ግቡ ከመሻር ግን አልተረፈም።

በስፔን ላሊጋ ዛሬ ምሽቱን ሴልታቪጎ ከጌታፌ ጋር ይጋጠማል። ትናንት ምሽት ኃያሉ ሪያል ማድሪድ ሪያል ቤቲስን 5 ለ3 አንኮታኩቷል። ለሪያል ማድሪድ ማርኮ አሴንሲዮ ሁለት ግቦችን፣ ሠርጂዮ ራሞዝ፣ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ፣ እና ካሪም ቤንዜማ አንድ አንድ ግብ አስቆጥረዋል። የካሪም ቤንዜማ ግብ የተቆጠረችው 90 ደቂቃ ሙሉ የጨዋታው ጊዜ ተጠናቆ በተጨመው 2 ደቂቃ ላይ ነበር።

ብስክሌት

ኪጋሊ ሩዋንዳ ውስጥ በተከናወነው የአፍሪቃ አኅጉር የብስክሌት ሽቅድምድም የኤርትራ ብስክሌት ቡድን በአንደኛነት አጠናቀቀ። የኤርትራ ቡድን፦ 10 የወርቅ፣ 5 የብር እና  5 የነሐስ በድምሩ 20 ሜዳሊያ በመሰብሰብ ነው በአንደኛነት ያጠናቀቀው።  ኢትዮጵያን ወክለው የተሰለፉ ብስክሌተኞች በበኩላቸው 3 የወርቅ፣ 7 የብር እና  3 የነሐስ በድምሩ 13 ሜዳሊያ በማግኘት በቡንድ ሁለተኛ ሲወጡ፤ የአዘጋጇ ሩዋንዳ ቡድን 3 የወርቅ 3 የነሐስ እና 4 የብር በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሦስተኛ ወጥተዋል። 23 የአፍሪቃ ሃገራት ተወዳዳሪዎቻቸውን ባሳተፉበት የኪጋሊው የብስክሌት ሽቅድምድም፥ አልጀሪያ 2 የነሐስ፣ ብሩንዲ 1 የብር እንዲሁም ናሚቢያ 1 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ያለውን ቦታ ይዘዋል።   

ከዚሁ ከብስክሌት ሽቅድምድም ሳንወጣ፦ የቱር ደ ፍሯንስ ውድድርን ለአራት ጊዜያት ያሸነፈው፣ የዓለማችን ዕውቁ ብስክሌተኛ ክሪስ ፎሜ የስፔን ሩታ ዴል ሶል ውድድር ላይ በ10ኛነት ማጠናቀቁ መነጋገሪያ ኾኗል። ክሪስ ፎሜ ከሦስት ዓመት በፊት የተከናወነውን ተመሳሳይ ውድድር በአንደኛነት ማጠናቀቁ ይታወቃል። ኾኖም ለአስም ኅመም ማስታገሻ የሚሰጠውን ሣልቡታሞል መድኃኒት ተጠቅመሀል ተብሎ ባለፈው በስፔን ቩዌልታ ሽቅድምድም ላይ ምርመራ ተደርጎበት ነበር።

Pyeongchang 2018 Olympische Winterspiele | Aerials
ምስል Getty Images/C. Spencer

የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች

ደቡብ ኮሪያ ፕዮንግቻንግ ውስጥ ዐሥረኛ ቀኑን ባስቆጠረው 23ኛው የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች በሜዳሊያ መሪ የነበረችው ጀርመን ቦታውን ለኖርዌይ አስረክባለች። 5,2 ሚሊዮን ነዋሪ ብቻ ያላት ኖርዌይ 82,6 ሚሊዮን ነዋሪ ያላትን ጀርመን በሜዳልያ ልቃለች። ኖርዌይ እስካሁን 28 ሜዳሊያዎችን ስትሰበስብ ጀርመን በ20 ትከተላለች። ካናዳ በሜዳሊያ ብዛት ሦስተኛ ናት። 17 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች። ዩናይትድ ስቴትስ በ10 ሜዳሊያ ከኔዘርላንድ በታች ናት። ውድድሩ እየተኪያሄደ በመኾኑ የሜዳሊያ ብዛቱ ሊቀያየር ይችላል።

ደቡብ ኮሪያ ፕዮንግቻንግ ውስጥ ዐሥረኛ ቀኑን ባስቆጠረው 23ኛው የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ኖርዌይ በሜዳሊያ ብዛት እየመራች ትገኛለች። ጀርመን በሁለተኛነት ስትከተል፤ ጎረቤት ኔዘርላንድ ሦስተኛ ደረጃን ይዛለች።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ