1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ የካቲት 18 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ የካቲት 18 2011

በእንግሊዝ ፕሬሚየ ርሊግ ሊቨርፑል ትናንት ኦልትራፎርድ ውስጥ የማሸነፍ እድሉን አምክኗል። ኾኖም ግን በድጋሚ መሪነቱን ተቆናጧል። የተጋጣሚው ማንቸስተር ዩናይትድ የአደራ ጊዜ አሰልጣኝ አይበገሬነታቸውን አስመስክረዋል። «የኢትዮ ቡና ስፖርት  መፍትኄ አፈላላጊ ኮሚቴ» ዛሬ በመግለጫው ከእንግዲህ ተግባሩን ማቋረጡን ይፋ አድርጓል

https://p.dw.com/p/3E4s3
Premier League | Crystal Palace vs. Tottenham Hotspur
ምስል picture-alliance/empics/Craig Mercer/Sportimage

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየ ርሊግ ሊቨርፑል ትናንት ኦልትራፎርድ ውስጥ የማሸነፍ እድሉን አምክኗል። ኾኖም ግን በድጋሚ መሪነቱን ተቆናጧል። የተጋጣሚው ማንቸስተር ዩናይትድ የአደራ ጊዜ አሰልጣኝ አይበገሬነታቸውን አስመስክረዋል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን እና መሪው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በነጥብ እጅግ ተቀራርበዋል። የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር በተለያዩ የቡንደስሊጋው ተጨዋቾች ላይ እገዳ መጣሉን ዛሬ ይፋ አድርጓል። በአትሌቲክሱ ዘርፍ «ለደኅንነታችን እንሩጥ» በሚል መርኅ ቃል ትናንት በአዲስ አበባ የሩጫ ውድድር ተከናውኗል። «የኢትዮ ቡና ስፖርት  መፍትኄ አፈላላጊ ኮሚቴ» ዛሬ በመግለጫው ከእንግዲህ ተግባሩን ማቋረጡን ይፋ አድርጓል። 

የኢትዮ ቡና ስፖርት ቡድን በተለያዩ ችግሮች ተተብትቧል። ቡድኑ አንዳች መፍትኄ ካልተፈለገለት ለውድቀት ይዳረጋል የሚሉ ተበራክተዋል። ሰሞኑን ፈረንሳዊ አሰልጣኙ ዲዲዬ ጎሜዝን ያሰናበተው ኢትዮ ቡና ቡድን በቦርዱ እና በመፍትኄ አፈላላጊ ቡድኑ መካከል ልዩነቱ ጫፍ ደርሷል። «የኢትዮ ቡና ስፖርት መፍትኄ አፈላላጊ ኮሚቴ» ዛሬ ከሰአት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንቅሳቃሴውን በይፋ ማቋረጡን ዐሳውቋል።  መግለጫውን ከሂልተን ሆቴል ለተከታተለው የኢትዮ ኤፍ ኤም 107,8 ኢትዮ ስፖርት ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰን ስብሰባው እንደተጠናቀቀ ቃለ መጠይቅ አድርገንለት ነበር። መፍትኄ አፈላላጊ ኮሚቴው፦ «ከተቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ ምን ምን ሥራዎችን ሲያከናውኑ እንደነበር፤ ያንን ጥርት ባለ ኹኔታ ለቡድኑ ቦርድ፤ ያቀረቡትን ነገር ለማሳወቅ እና ጨርሰናል፤ ከዚህ በኋላ ከእኛ የሚጠበቀውን ሥራ ስላጠናቀቅን እዚህ ላይ ማቆማችንን» ኹሉም እንዲያውቀው ማለቱን ምስጋናው ገልጧል። 

Jürgen Klopp
ምስል picture-alliance/PA Wire/R. Sellers

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በሳምንቱ መጨረሻ የተከናወነው የሊቨርፑል እና የማንቸስተር ዩናይትድ የእግር ኳስ ግጥሚያ የበርካቶችን ቀልብ የሳበ ነበር። በእለቱ ግጥሚያ ሊቨርፑል በጨዋታ ብልጫ አሳይቶ የነበር ቢኾንም፤ ማንቸስተር ዩናይትድ በተደጋጋሚ አስደንጋጭ ሙከራዎችን አድርጓል። የሊቨርፑል አሰልጣኝ ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕ፦ «የዚህ ቡድን የልብ ትርታ የቡድኑ ፍቅር ነው። ረቡዕ ማታ ከዋትፎርድ ጋር የምናደርገው ጨዋታ ሌላ ዕድል ነው። ከዚያ ደግሞ ከኤቨርተን ጋር የምናደርገው ደርቢ አለ። እሱ ሁልጊዜም በስሜት እና በልዩ ፍቅር የሚከናወን ግጥሚያ ነው» በማለት የቡድናቸው ዕድል ሰፊ መኾኑን ጠቁመዋል። ኾኖም ከወሳኝ ተጨዋቾቻቸው መካከል በትናንቱ ጨዋታ በቁርጭምጭሚት ጉዳት የተነሳ ተቀይሮ የወጣው ሮቤርቶ ፊርሚኖ በረቡዕ ግጥሚያ መሰለፍ ይችል እንደኾን ማጠራጠሩ በቡድኑ ስጋት ፈጥሯል። ፊርሚኖ ምናልባትም ለሻምፒዮንስ ሊጉ የባየር ሙይንሽን ግጥሚያ ላያገግምም ይችላል። ሌሎቹ አጥቂዎች ሞሐመድ ሳላኅ እና ሳዲዮ ማኔ በትናንቱ ጨዋታ የተጠበቀባቸውን ያኽል አለመፈጸማቸው፤ አሰልጣኙ  የሻምፒዮንስ ሊጉን የበለጠ እንዲጨነቁበት አድርጓል።

የተጋጣሚያቸው ማንቸስተር ዩናይትድ የአደራ ጊዜ አሰልጣኝ ኦሌ ጉነር ሶልስካዬር እስካሁን ቡድኑን ከተረከቡ ጊዜ ጀምሮ ድንቅ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ናቸው። ኾኖም የፊታችን ረቡዕ ጠንከር ያለ ፈተና ሳይገጥማቸው አይቀርም። ምክንያቱም አንቶኒ ማርሺያል እና ኔማንያ ማቲች ለልምምድ መድረስ አልቻሉም። ትናንት ከሊቨርፑል እና ማንቸስተር ዩናይትድ ግጥሚያ ባሻገር በነበረው ፍልሚያ አርሰናል ሳውዝሐምፕተንን 2 ለ0 አሸንፏል።

Fußball UK Premier League | Manchester United v Burnley | Trainer Ole Gunnar Solskjaer
ምስል picture-alliance/empics/S. Bellis

የጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለያዩ ተጨዋቾች ላይ ዛሬ ቅጣት አስተላልፏል። ቅዳሜ ዕለት ከባየር ሙይንሽን ጋር በነበረው ግጥሚያ በቀይ ካርድ የተሰናበተው የሔርታ ቤርሊኑ ተከላካይ ካሪም ሬኪክ አንድ ተጨማሪ ጨዋታ ተቀጥቷል። ከሮበርት ሌቫንዶብስኪ ጋር ግጭት በመፍጠሩ ከእገዳው በተጨማሪ የ17 ሺህ ዩሮ ቅጣት ተላልፎበታል። የሌቫንዶቭስኪ ቡድን ባየር ሙይንሽን 51 ነጥብ ይዞ መሪው ቦሩስያ ዶርትሙንድን ደረስኩብህ ብሎታል። ልዩነታቸው 3 ነጥብ ብቻ ኾኗል።

የኑረንበርግ የክንፍ ተጨዋች ማቲያስ ፔሪዬራም በጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሦስት ጨዋታዎችን ታግዷል። የ22 ዓመቱ ብራዚሊያዊ ቅዳሜ ዕለት ባሳየው ያልተገባ ድርጊት በሚል 11 ሺህ ዩሮ በተጨማሪ ተቀጥቷል።

ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበርና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጋራ ያዘጋጁት  4ኛው የ5 ኪ.ሜ የጎዳና ሩጫ ውድድር ተከናውኗል። በአዲስ አበባ መገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ ከማለዳው 3:00 ሰዓት ላይ በተከናወነው የሩጫ ፉክክር፦ በወንዶች፣ የመከላከያው ተስፋሁን አካልነው 1ኛ ወጥቷል። የገባበት ሰአትም  14:37.61 ነው።  2ኛ ብርሃን ወንድሙ ከኢትዮ/ኤሌክትሪክ እንዲሁም 3ኛ ጅራታ ሌሊሣ ከቢሾፍቱ ከተማ አጠናቀዋል።  በሴቶች፣ 1ኛ ዳባሽ ከልሌ ከሱር ኮንስትራክሽን፤ የገባችበት ሰአት 16:54.42 ነው።  2ኛ የወጣችው አበራሽ ምንስዎ ከሱር ኮንስትራክሽን እንዲሁም 3ኛ ደረጃ ያገኘችው መድኀን ገ/ስላሴ ከኢትዮ/ን/ባንክ ናት።

ማንተጋፍቶት ስለሺ