1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ የካቲት 28 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.

ሰኞ፣ የካቲት 28 2008

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጥላ አጥልቶበታል። 3 አትሌቶቹ ኃይል ሰጪ መድኃኒት መጠቀማቸው ይፋ ኾኗል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ 4 ተከታታይ ጨዋታዎችን ያሸነፈው ማንቸስተር ዩናይትድ 11ኛ ደረጃ ላይ ለሚገኝ ቡድን እጅ ሰጥቷል። ሊቨርፑል በካፒታል ዋንዋንጫ የነጠቀውን ማንቸስተር ሲቲን 3 ለ0 ተበቅሎ፤ ክሪስታል ፓላስንም ድል አድርጓል።

https://p.dw.com/p/1I8p7
Spanien Cristiano Ronaldo und Leo Messi
ምስል picture-alliance /NurPhoto/J. Valls

ስፖርት፤ የካቲት 28 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ኃያላኑ ባየር ሙይንሽን እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ ተገናኝተው ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድ ሴልታቪጎን 7 ለ1 ጉድ ባደረገበት ጨዋታ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በላሊጋው ታሪክ ሠርቷል።

በአውሮፓ ሊግ ቀደም ሲል ያከናወኗቸውን የምድብ ጨዋታዎች አሸንፈው ለመጀመሪያው ዙር ጨዋታ የደረሱት ዐሥራ ስድስቱም ቡድኖች የፊታችን ሐሙስ ይገናኛሉ።

በፕሪሚየር ሊጉ ሽንፈት የገጠመው ማንቸስተር ዩናይትድ ከሊቨርፑል ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል። ዋይኔ ሩኒ እና ሽቫይንሽታይገርን ጨምሮ ዘጠኝ ተጨዋቾች የተጎዱበት ማንቸስተር ዩናይትድ ሊቨርፑልን ለ195ኛ ጊዜ ኾኖም በአውሮጳ ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመፋለም ሐሙስ ወደ አንፊልድ ያቀናል። ሊቨርፑል በአንፃሩ አራት ተጨዋቾች ብቻ ናቸው የተጎዱበት።

ሁለቱ ቡድኖች በእንግሊዝ የሊግ ጨዋታዎች ለ166 ጊዜያት ተገናኝተው ማንቸስተር ዩናይትድ 67 ጊዜ ሲያሸንፍ፤ ሊቨርፑል 55 ጊዜ አሸንፎዋል። እንግሊዝ ውስጥ በተከናወኑ 18 የዋንጫ ጨዋታዎች ሁለቱ ቡድኖች ተፋልመዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ 11 ጊዜ ሊቨርፑልን ሲረታ፤ ሊቨርፑል ማንቸስተር ዩናይትድን ለ7 ጊዜያት አሸንፎታል። ማንቸስተር ዩናይትድ ከሊቨርፑል ጋር ያከናወናቸውን ያለፉትን አራት የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሙሉ አሸንፏል። ኾኖም ግን ሊቨርፑል ዘንድሮ ባከናወናቸው የአውሮጳ ሊግ ስምንት ጨዋታዎች በአንዱም አልተሸነፈም። ማንቸስተር ዩናይትድ የአውሮጳ ሊግ ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጪ ዘንድሮ አንዴም አላሸነፈም።

በፕሬሚየር ሊጉ አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን ያሸነፈው ማንቸስተር ዩናይትድ የኋዋን ማታ በጊዜ ከሜዳ መሰናበትን ተከትሎ ትናንት በዌስት ብሮሚች 1 ለ0 ተሸንፏል። ጄምስ ሚልነርን በቀይ ካርድ ያጣው ሊቨርፑል በቆራጥነት ተፋልሞ ክሪስታል ፓላስን 2 ለ1 የረታው በክርስቲያን ቤንቴኬ የፍጹም ቅጣት ምት ግብ ነው። ሊቨርፑል በፕሪሚየር ሊጉ ያሳየው እልህ፤ የሐሙሱ የአውሮፓ ሊግ ጨዋታ በሜዳው በአንፊልድ ከመሆኑ ጋር ተደምሮ ለማንቸስተር ዩናይትድ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

በእርግጥ ማንቸስተር ዩናይትድም ኾነ ሊቨርፑል በእንግሊዝ የእግር ኳስ ታሪክ እጅግ ስኬታማ የሚባሉ ናቸው። እናስ የሐሙሱን ጨዋታ ማን ያሸንፍ ይኾን? ሊቨርፑል ወይንስ ማንቸስተር ዩናይትድ?

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በነጥብ ሦስተኛ የሆነው ቶትንሀም ሆትስፐርም በአውሮፓ ሊግ ጨዋታ ሐሙስ ከባድ ተፋላሚ ነው የሚጠብቀው። ከሰሜን ለንደን ተቀናቃኙ አርሰናል ጋር 2 እኩል የተለያየው ቶትንሀም በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ የደረጃ ሠንጠረዥ ሁለተኛ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድን በሜዳው ሊገጥም ነው የሚያቀናው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ የደረጃ ሠንጠረዡን በ63 ነጥብ በአንደኛነት ከሚመራው ባየር ሙይንሽን ጋር ቅዳሜ ዕለት ተገናኝቶ ያለምንም ግብ ተለያይቷል።

በስፔን ላሊጋ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው እና ቅዳሜ ዕለት በላፓልማ አንድ ለባዶ የተሸነፈው ቪላሪያል ከጀርመኑ ባየር ሌቨርኩሰን ጋር ስፔን ውስጥ ይጋጠማል። አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሴቪላ ደግሞ ከጌታፌ ጋር አንድ እኩል አቻ ወጥቷል፤ የአውሮጳ ሊግ ዕድሉን ለመሞከር ሐሙስ ወደ ባዝል ስዊዘርላንድ ያቀናል። በቅዱስ ያዕቆብ አጸድ የእግር ኳስ ሜዳም ከባዝል ጋር ይጋጠማል። ትናንት በአትሌቲኮ ማድሪድ 3 ለ1 የተረታው ቫሌንሺያ ስፖርቲንግ ጂዎንን 2 ለ0 ካሰናበተው አትሌቲክ ቢልባዎ ጋር ሐሙስ ለአውሮፓ ሊግ በቢልባዎ ሣን ማሜ ሜዳ ላይ ይፋለማል። የጣሊያኑ ላትሲዮ ከስፓርታ ፕራሃ ጋር ቼክ ሪፐብሊክ መዲና ፕራህ ውስጥ በሚገኘው ጄኔራሊ አሬና ስታዲየም ለሐሙስ ተቀጣጥሯል። የቤልጂጉ አንደርሌሽት ቡድን የዩክሬን መዲና ኪዬቭ ውስጥ ከሻካታር ዶኔትስክ ጋር የሚጫወተው ሐሙስ ዕለት ነው። የፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ብራጋ ከቱርኩ ፌኔርባኅቼ ጋርም በዚሁ ዕለት ይጫወታል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የትናንቱ ጨዋታ፤ የዌስት ብሮሚች አልቢኖው ሳሎሞን ሮንዶን በ67ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ በዐሥር ተጨዋቾች የተወሰነው ማንቸስተር ዩናይትድ ተሸንፎ ወጥቷል። ሳሎሞን ሮንዶን ትናንት ያገባት ኳስ በ6 ጨዋታዎች አራተኛ ግቡ ነበረች። በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ስፔናዊው ዃን ማታ በሁለት ቢጫ ካርድ በቀይ ከሜዳ መሰናበቱ ማንቸስተር ዩናይትድን ጎድቶታል። በቀይ መሰናበቱን «እጅግ አናዳጅ» ሲል የገለጠው ስፔናዊው ከጥፋቱ ወደፊት እንደሚማር ተናግሯል። ዃን ማታ በመጀመሪያው አጋማሽ በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ሁለት ቢጫ በማግኘቱ ነው የተሰናበተው። በግል አምደመረቡ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍም፦ «ሁለቱም ውሳኔዎች በጣም አናዳጅ ናቸው። ብዙውን ጊዜ እጅግ የከፉ ጥፋቶች ተፈጽመው ቅጣት ሲሰጥ አላየንም። ያም ሆኖ ግን ጥፋቶቹን እንዳይከሰቱ ማድረግ እችል ነበር። ኃላፊነቱን እወስዳለሁ» ብሎዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ከአንድ ሰአት በላይ በ10 ተጨዋቾች ለመወሰን ተገዷል። መጨረሻውም በ1 ለ0 ተደምድሟል።

የእንግሊዙ ቸልሲ ለሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ረቡዕ ዕለት በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ የፈረንሣዩ ፓሪስ ሳንጀርሜይንን ይገጥማል። ፓሪስ ሳንጀርሜይንን ከነጌ በስተያ ወደ ለንደን የሚያቀናው ቀደም ሲል ፓሪስ ውስጥ በ2 ለ1 ድሉ ያሰፋውን ዕድል ይዞ ነው። ጆን ኦቢ ሚኬል ከሜዳ ውጪ ያስቆጠራት ግብ ቸልሲ በሜዳው የተሻለ ሊሠራ እንደሚችል ተስፋ ሰጥቶታል። ቸልሲዎች ባለፈው ታኅሣስ ወር አሠልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆን ካሰናበቱ ወዲህ ባከናወኗቸው 16 ግጥሚያዎች አንድ ጊዜ ብቻ ነው የተሸነፉት። ቸልሲ ቅዳሜ ዕለት ከስቶክ ሲ ጋር አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። በፕሬሚየር ሊጉ እንደምንም በአራተኛነት ጨርሶ ወደፊት በሻምፒዮንስ ሊግ የመሳተፍ ዕድሉ ግን ጨልሟል።

በአንፃሩ ያለፉት አራት ጨዋታዎቹን ያልተሸነፈው ሊቨርፑል የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ዕድሉን እያለመለመ ነው። 60 ነጥብ ካለው ከመሪው ላይስተር ሲቲ በ16 ነጥብ ልዩነት 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። እንደ ማንቸስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። ኤቨርተን እና ኒውካስል ዩናይትድም ተስተካካይ ጨዋታ ይቀራቸዋል። ባለፈው ሳምንት በስዋንሲ ሲቲ የተሸነፈው አርሰናል ቅዳሜ ዕለት ከቶትንሀም ሆትስፐር ጋር አቻ ሁለት እኩል ወጥቷል። በዚህም አስቶን ቪላን 4 ለ0 ያደባየው ማንቸስተር ሲቲ ነጥቡን 50 አድርሶ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናልን ተጠግቶታል። አርሰናል ማንቸስተር ሲቲን በ2 ነጥብ ብቻ ነው የሚበልጠው፤ ሁለተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው በቶትንሀም ግን በ3 ነጥብ ይበለጣል። መሪው ላይስተር ሲቲ ዋትፎርድን አንድ ለባዶ አሸንፏል።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ አንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባየር ሙይንሽን ከተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር ዜሮ ለዜሮ በመውጣት ነጥብ ተጋርተዋል። የባየር ሙይንሽኑ አጥቂ ቶማስ ሙይለር ቡድናቸው ባያሸንፍም ጠንካራ እንደነበር ተናግሯል።

«0 ለ0 የተጠናቀቀ ኃይለና ጨዋታ ነበር። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ዕድሎች አጋጥሟቸዋል። ቡድናችን በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ኃያል ኾኖ አይቼዋለሁ። በእውነቱ ጨዋታውን በደንብ ነው የተቆጣጠርነው። ከምርጥ ተጨዋቾች ጋር ስትጫወት እንግዲህ እንደዛ ነው። የሚገርም 0 ለ0 ነው። አስጨናቂ ጨዋታ ነበር ግን በተወሰነ መልኩ ደስተኞች ነን።»

የሊቨርሉ አሠልጣኝ፤ ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕ
የሊቨርሉ አሠልጣኝ፤ ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕምስል Reuters/C. Recine
የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ
የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታምስል picture-alliance/dpa/Y. Valat
የአውሮጳ ሊግ ጨዋታ
የአውሮጳ ሊግ ጨዋታምስል Getty Images/AFP/P. Stollarz

ኦበርሜያንግ በቀኝ በኩል እየገፋ ሄዶ ወደግብ የሞከራትን ኳስ የባየር ሙይንሽኑ ግብ ጠባቂ ማኑኤል ኖዬር ግብ እንዳትሆን ገችቶ አውጥቷታል። ኮስታ በ27ኛው ደቂቃ ላይ ከቦሩስያ ዶርትሙንዱ ግብ ጠባቂ ቡርኪ ጋር ተገናኝቶ የመታት ኳስ በግብ ጠባቂው እግር ተጨናግፋለች። 64 ከማዕዘን የመጣችውን ኳስ ቪዳል ወደ ግቡ ልኳት የግቡን አግዳሚ ገጭታ ወጥታለች። 88ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ኦበርሜያንግ ከበስተቀኝ ማዕዘን አቅጣጫ የላካትን ኳስ ተቀይሮ የገባው ራሞስ በችጭንቅላት ገጭቶ ስቷል።

ትናንት ማይንትስ ከዳርምሽታድት ባዶ ለባዶ ሲወጣ፤ ሐምቡርግ ሔርታን 2 ለ0 አሰናብቷል። ቡንደስ ሊጋውን ባየር ሙይንሽን በ63 ነጥብ ይመራል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ58 ይከተላል። 42 ነጥብ የያዘው ሔርታ ሦስተና ደረጃ ላይ ይገኛል።

በስፔን ላሊጋ የሣምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች የሪያል ማድሪድ የ7 ለ1 ድል ከፍተኛው ኾኖ ተመዝግቧል። ማድሪድ ቅዳሜ ዕለት ሴልታቪጎን የግብ ጎተራ ሲያደርገው በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ አራቱን ግቦች ያስቆጠረው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነው። የመጀመሪያዋን በ7ኛው ደቂቃ ላይ ፔፔ በግንባሩ ገጭቶ በግሩም ኹኔታ አስቆጥሯል። ቀሪዎቹን ሁለት ግቦች ከመረብ ያሳረፉት ጄሴ እና ባሌ በ77 እና 80ኛው ደቂቃ ላይ ነው። ስፔናዊው አጥቂ ኢያጎ አስፓስ ለሴልታ ቪጎ 61ኛው ደቂቃ ላይ በማስቆጠር ቡድኑን በባዶ ከመሸነፍ አድኖታል።

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ባስቆጠራቸው አራት ግቦች በስፔን ላሊጋ በግብ ብዛት ቀዳሚ ኾኗል።እስካሁን 27 ኳሶችን ከመረብ አሳርፏል። የባርሴሎናዎቹ ሉዊስ ሱዋሬዝ እና ሊዮኔል ሜሲ በ26 እና 21 ግቦች ይከተሉታል። በላሊጋው ታሪክ ግን እስካሁን በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ሊዮኔል ሜሲን የሚስተካከል አልተገኘም። ሮናልዶ 252 ኳሶችን በላሊጋው ለማስመዝገብ ችሏል። ሊዮኔል ሜሲ 305 ግቦችን አስቆጥሮ ብዙ የማግባት ክብር ወሰኑን ተቆጣጥሯል። ባርሴሎና አይበርን ትናንት 4 ለዜሮ ድል አድርጓል። በ72 ነጥብ ላሊጋውን ይመራል። አትሌቲኮ ማድሪድ እና ሪያል ማድሪድ በ64 እና 60 ነጥቦች ይከተሉታል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኃይል ሰጪ መድኃኒት በመጠቀም ከተጠረጠሩት 9 አትሌቶች ሦስቱን ጥፋኞች በሚል አግዷል። አትሌቶቹ እነማን እንደሆኑ ግን ፌዴሬሽኑ በይፋ አልተናገረም። 9ኙ አትሌቶች በእርግጥም ጥፋተኛ ከሆኑ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ላይ ከባድ ጥላ ማጥላቱ እንደማይቀር በፌስቡክ ገጻችን ላይ ባሰፈርነው የመወያያ ርእስ ላይ ተሳታፊዎች ገልጠዋል።

የተወሰኑትን የፌስ ቡክ ተሳታፊዎች ለማቅረብ ያኽል፦ አብይ ግርማ የተባሉ ተሳታፊ «ኢትዮጵያ ዶፒንግ ተገኘባት ማለት በዓለም አትሌቲክስ ስፖርት ወድቃ አከተመለት እንደማለት ነው። አረንጓዴ ጎርፍ ወደ ኤልኒኖ ተቀየረ ማለት ነው። ከአላባ » ብለዋል። « በጣም ቅሌት ቆይ እነማን ናቸዉ?» ሲሉ ያጠየቁት ደግሞ ጌታቸው ሰቦቃ ናቸው። ጌታቸው ሞሐመድ ደግሞ በእንግሊዝኛ በሰጡት አስተያየት «ያሳዝናል፤ ይኽ ግን እውነት ነው? ለመሆኑ እነማን ናቸው?» ብለዋል። አስተያየቶቹን ለማንበብም ሆነ በአስተያየት ለመሳተፍ የፌስ ቡክ ገጻችንን እንድትጎበኙ እንጋብዛለን።

ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ
ክሪስቲያኖ ሮናልዶምስል picture-alliance/AP Photo/M. Meissner
ፒዬር ኦበርሜያንግ
ፒዬር ኦበርሜያንግምስል picture-alliance/dpa/E. Silva