ስፖርት፣ ግንቦት 1 ቀን፣ 2008 ዓ.ም
ሰኞ፣ ግንቦት 1 2008
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአምስት ወራት ቆይታ ስልጠና እንዲሰጡለት ከቀድሞው የብሔራዊ ቡድን አጥቂ እና የመከላከያ እግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ገብረ-መድኅን ኃይሌ ጋር ንግግር መጀመሩ ተገልጧል። ለአንድ ዓመት ያኽል በብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝነት ተሹመው የነበሩት አቶ ዮሐንስ ሣኅሌ መሰናበታቸውን ተከትሎ ነው አዲስ አሠልጣኝ ለመመደብ ንግግሩ የተጀመረው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩን በስልክ አነጋግረናቸዋል፤ አሠልጣኙ ለምን እንደተነሱ በማብራራት ይጀምራሉ።
የቀድሞው አሠልጣኝ አቶ ዮሐንስ ሣኅሌ አስተያየታቸውን እንዲያካፍሉን ደውለንላቸው ስብሰባ ላይ እንደሆኑ ገልጠውልን ነበር። ቆየት ብለን ደጋግመን ስልካቸው ላይ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም። ለአምስት ወራት ስልጠና ብሔራዊ ቡድኑን እንዲይዙት የተጠየቁት አሠልጣኝ ገብረ-መድኅን ኃይሌን ግን አነጋግረናቸዋል። «ስምምነቱ ገና ተጀመረ እንጂ አላለቀም» ያሉን አሠልጣኝ ዝርዝር ጉዳዮች በሒደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እግር ኳስ
ሊጠናቀቅ አንድ አንድ ዙር ብቻ በቀረው የጀርመን ቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ውድድር አስቀድሞ ዋንጫውን መውሰዱን ያረጋገጠው ኃያሉ ባየር ሙይንሽን የፊታችን ቅዳሜ ከሰአት በኋላ ከኮሎኝ ጋር የመጨረሻውን ጨዋታ ያከናውናል። ከሁለቱ ጨዋታ ይልቅ ግን በእለቱ በተመሳሳሳይ ሰአት ቬርደር ብሬመን ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት፣ ሽቱትጋርት ከቮልፍስቡርግ፣ ማይንትስ ከሔርታ በርሊን እንዲሁም ሻልከ ከሆፈንሀይም ጋር የሚያከናውኑት ጨዋታዎች እጅግ በጉጉት ይጠበቃሉ።
ቡንደስሊጋ
በቡንደስሊጋው 25 ነጥብ ይዞ 18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውሐኖቨር ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ወራጅ መሆኑ ተረጋግጧል። 16ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቬርደር ብሬመን 15ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው አይንትራኅት ፍራንክፉርት በአንድ ነጥብ ይበለጣል፤ ነጥቡ 35 ነው። ሁለቱ በሚያደርጉት የሞት ሽረት ፍልሚያ አይንትራኅት ፍራንክፉርትካሸነፈ 39 ነጥብ ይዞ ከወራጅ ቃጣናው ስጋት ሙሉ ለሙሉ ይላቀቃል። ከተሸነፈ ግን በቡንደስሊጋው የመቆየት ኅልውናው የሚወሰነው ከታችኛው ዲቪዚዮን ሦስተኛ ከወጣ ቡድን ጋር ተጋጥሞ በሚኖረው ውጤት ይሆናል። ተጋጣሚው ቬርደር ብሬመን ካሸነፈ 38 ነጥብ ይዞ ወደታችኛው ዲቪዚዮን ከመውረድ ይተርፋል ማለት ነው። ወራጅ ቃጣና ውስጥ 17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሽቱትጋርት 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቮልፍስቡርግን ካሸነፈ ነጥቡን 36 በማድረስ ከመውረድ ሊተርፍ የሚችለው ብቬርደር ብሬመን ከተሸነፈለት ብቻ ነው። ያም ቢሆን በቡንደስ ሊጋው ለመቆየት ከታችኛው ከሚመጣው 3ኛ ቡድን ጋር ተጋጥሞ ማሸነፍ ይኖርበታል። ይኽ በመሆኑም የቅዳሜው የቡንደስ ሊጋ የመጨረሻ ግጥሚያ እጅግ በጉጉት ይጠበቃል።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫውን በእጁ ያስገባው ሌስተር ሲቲ አሠልጣኝ ጣሊያናዊው ክላውዲዮ ራኒየሪ ተጨዋቾቻቸው በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ቡድኑን ጥለው እንዳይሄዱ መክረዋል። ወደ ሌላ ቡድን መሄድ የሚፈልግ ካለ ግን ተጨዋቹን ለማሰናበት ምንም እንደማያንገራግሩ ገልጠዋል።
ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ሊቨርፑል ትናንት ዋትፎርድን 2 ለo በማሸነፉ የሚቀጥለው ዙር የአውሮጳ ሊግ ማጣሪያ ውስጥ ለመግባት ዕድሉን አመቻችቷል። በእርግጥ የአውሮጳ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታውን ካሸነፈ በቀጥታ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ መግባቱ አይቀርም። አርሰናል ከማንቸስተር ሲቲ ጋር 2 ለ2 መውጣቱ በቀጥታ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ የማለፍ ዕድሉን ጥያቄ ውስጥ አስገብቷል። ቀጣዩን ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲ ካሸነፈ እና አርሰናል ከተሸነፈ ማንቸስተር ሲቲ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ በቀጥታ ያልፋል። አርሰናል ለሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ይገባል። ውጤቱ ከተገላበጠ ዕድሉም በዛው መልኩ ይቀየርና አርሰናል በቀጥታ ለሻምፒዮንስ ሊግ ማለፍ ይችላል። ዋንጫውን በሌስተር ሲቲ በመነጠቁ እና በሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን በማረጋገጡ ቶትንሀም ትናንት በሳውዝሀምፕተን2 ለ1 መሸነፉ ብዙም የሚያስቆጨው አይደለም።
ላሊጋ
በስፔን ላሊጋ ትናንት ኤስፓኞላን 5 ለ0 ያንኮታኮተው ባርሴሎና በ88 ነጥብ ዋንጫውን ለመውሰድ ጫፍ ቢደርስም ትናንት ቫሌንሺያን 3 ለ2 ያሸነፈው እና 87 ነጥብ ይዞ የሚከተለው ሪያል ማድሪድ የዋንጫ ዕድል አለው። በላሊጋው ከሁለቱ በተጨማሪ አትሌቲኮ ማድሪድም ለሻምፒዮንስ ሊግ ማለፋን አረጋግጧል። ስፖርቲንግ ጂone፣ራዮ ቫሌካኖ እና ሌቫንቴ ወራጅ ቃጣና ውስጥ ይገኛሉ።
የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ፕሬዚዳንት ሚሼል ፕላቲኒ ከያዙት የአመራርነት ሥልጣን እንደሚነሱ ተገለጠ። የ60 ዓመቱ ሚሼል ፕላቲኒ ከፕሬዚዳንትነት እንደሚነሱ የተናገሩት ከእግር ኳሱ ዓለም ለስድስት ዓመታት መታገዳቸውን የስፖርት ጉዳዮች ውሳኔ ሰጪ ፍርድ ቤት ዛሬ ወደ አራት ዝቅ ማድረጉን በገለጠበት ወቅት ነው። ሚሼል ፕላቲኒ እና የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽን በእንግሊዘኛ ምኅጻሩ (FIFA) የቀድሞው ፕሬዚዳንት የ79 ዓመቱ ሴፕ ብላተር 2 ሚሊዮን የስዊስ ፍራንክ «ታማኝ ባልሆነ መልኩ በመክፈል» በሚል የሙስና ድርጊት ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸው መገለጡ ይታወሳል።
አትሌቲክስ
በቃታር ዶሃ በተከናወነው የዳያመንድ ሊግ የ3000 ሜትር የሩጫ ውድድር አሸናፊ የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አልማዝ አያና 88 ቀናት በቀሩት የሪዮ ኦሎምፒክ ውድድር ተስፋ ከሚጣልባቸው አትሌቶች አንዷ ናት። የአምስት እና የዐሥር ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድሮችን ለመካፈል ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች።
ሜዳ ቴኒስ
ከዓለማችን በሜዳ ቴኒስ ውድድር በ3ኛ ደረጃ ዕውቅ ተጨዋች የሆነው እንግሊዛዊው አንዲ ሙራይ ለሁለት ዓመታት ካሰለጠኑት አሜሊ ሙሬስሞ ጋር መለያየቱ ተገለጠ። «ከአሜሊ ማውሬስሞ ብዙ ቀስሜያለሁ» ያለው የ28 ዓመቱ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ «በጋራ ተስማምተናል» ሲል አክሏል። የ36 ዓመቷ ፈረንሳዊት አሠልጣኝ በበኩላቸው «ከአንዲ ጋር የሠራሁበት ያለፉት ሁለት ዓመታት ለእኔ እጅግ የሚደንቅ ልምድ ያካበትኩበት ነው» ብለዋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ