1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ጥር 09 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

ሰኞ፣ ጥር 9 2008

በስፔን ላሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያ ሪያል ማድሪድ በአዲሱ አሠልጣኝ ዚነዲን ዚዳን መመራት ከጀመረ ወዲህ በተከታታይ 5 ግቦችን ማስቆጠሩን ትናንትም ደግሞታል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታ ፍልሚያ፦ ሊቨርፑል በሜዳው እጅ ሰጥቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በቻን 2016 አፍሪቃ ዋንጫ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተሸንፏል።

https://p.dw.com/p/1HfcL
WM 2014 Achtelfinale USA Belgien Tor
ምስል Reuters

ስፖርት፤ ጥር 09 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

ማንቸስተር ዩናይትዶች ትናንት በድንቅ ግብ ጠባቂያቸው ዴቪድ ዴ ጊያ ሳይተማመኑ አልቀሩም። ግብ ጠባቂው ኹለት ያለቀላቸውን ኳሶች ባማዳን በእርግጥም ድንቅ መኾኑን አስመስክሮ ነበር። በስተመጨረሻም ዋይኔ ሩኒ ባገኛት ግብ ሊቨርፑልን 1 ለባዶ ሸኝተዋል። አርሰናል ከስቶክ ሲቲ ጋር ትናንት ተገናኝቶ ያለምንም ግብ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። እናም በጥቂት ሰአታት ልዩነት በግብ ልዩነት መሪው ላይስተር ሲቲን በልጦ በደረጃ ሠንጠረዡ አንደኛ ሆኖ ጉብ ብሏል። አርሰናል እና ሌስተር ሲቲ ተመሳሳይ 44 ነጥብ ሲኖራቸው፤ የሚለያዩት በግብ ክፍያ ብቻ ነው። ሌስተር ሲቲ ቅዳሜ ዕለት ከአስቶን ቪላ ጋር አንድ እኩል መውጣቱ ይታወሳል።

ማንቸስተር ሲቲ አንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ በሦስተኛ ደረጃውን ተቆናጧል። አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ከመሪዎቹ ጋር ያለውን ነጥብ በ7 ነጥብ ማጥበብ ችሏል። ገና 16 ጨዋታዎች ይቀራሉ። የፕሪሚየር ሊጉ ግብግብ ከምንጊዜውም የበለጠ ዘንድሮ የተጠናከረ ይመስላል። ስምንት ጨዋታዎችን ሳያሸንፍ ተጉዞ ለነበረው ማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ቫን ጋል የስጋት ጊዜው ሰከን ያለ ይመስላል። አሠልጣኝ ቫን ጋል «ተፎካካሪዎቻችን ነጥብ ጥለዋል» ሲሉ ቡድናቸውን ለማጽናናት ሞክረዋል። «ልዩነቱ እንደዚህ ሲሆን፤ ማለትም ሰባት ነጥብ፤ ያኔ ልትወጣው ትችላለህ። 2016ን በጥሩ ኹኔታ ነው የጀመርነው፤ በተደጋጋሚ በማሸነፍ እና ነጥብ በመጋራት፤ አንድ ጊዜም አልተሸነፍንም።» ብለዋል አሠልጣኝ ቫን ጋል።

ከቶትንሐም በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ ለሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ዘንድሮ በአራተኛ ደረጃ አጠናቆ ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ መብቃት ዝቅተኛው ግብ መኾኑ ከቡድኑ ተገልጧል። እናም ታዲያ ዋይኔ ሩኒ ግብ ወደ ማስቆጠር ልማዱ በመመለሱ ለ20 ጊዜያት ባለድሉ ማንቸስተር ዩናይትድ የወደፊቱ ጉዞ ተስፋ የተሞላበት ይመስላል። የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አምበሉ ዋይኔ ሩኒ በ2016 በአራት ግጥሚያዎች አምስት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ለእዚህም ይመስላል ማንቸስተር ዩናይትድ ቢያንስ ቢያንስ ሻምፒዮንስ ሊግ አናጣም ማለት የጀመረው።

ሊቨርፑል በትናንቱ ጨዋታ በለስ ሳይቀናው ቀርቷል። ከሊቨርፑል 19 የግብ ሙከራዎች ውስጥ በቀጥታ ወደ ግብ የተላኩት ኳሶች አራት ብቻ ነበሩ። ይኽ በእርግጥም የሊቨርፑል አጥቂ ክፍልን ጥያቄ ውስጥ ሳይከተው አይቀርም። በደረጃ ሠንጠረዡ 9ኛ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል እንደ ማንቸስተር ዩናይትድ ዕቅድ ቢያንስ አራተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ለሻምፒዮንስ ሊግ ለመብቃት መከራ የሚገጥመው ይመስላል። በፕሬሚየር ሊጉ 39 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቶትናም ሆትስፐር በ8 ነጥብ ዝቅ ብሎ ነው የሚገኘው። እንዲያም ሆኖ ግን አሉ የሊቨርፑል አሠልጣኝ ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕ፦«ዛሬ ያደረግናቸው በርካታ ነገሮች ጥሩ ነበሩ። አጨራረሳችን ግን ጥሩ አልለበረም» ሲሉ ተደምጠዋል ከትናንቱ ሽንፈት በኋላ።

በፕሬሚየር ሊጉ 15 ግቦችን በማስቆጠር የኤቨርተኑ ሮሜሉ ሉካካ በኮከብ ግብ አግቢነት አንደኛ ነው። የላይስተር ሲቲው ጃሚ ቫርዲም በተመሳሳይ ግብ አንደኛነቱን ተጋርቷል። የላይስተር ሲቲው ሌላኛው ተጨዋች ሪያድ ማኅሬዝ እና የዋትፎርዱ ኦዲዮን ኢጋሎ 13 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ በጋራ ሁለተኛ ኮከብ ግብ አግቢ ናቸው። የአርሰናሉ ኦሊቨር ጂሮድ እና የቶትንሐም ሆትስፐሩ ሐሪ ኬን እያንዳንዳቸው 12 ግቦችን በማስቆጠር ይከተላሉ።

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ቀጥሎ ዛሬ ወራጅ ቀጣና ውስጥ የሚዋዥቀው ስዋንሲ ሲቲ ከዋትፎርድ ጋር ይጋጠማል። ስዋንሲ ከወራጅ ቃጣናው ለመውጣት ዛሬ የግድ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

በስፔን ላሊጋ ኃያላኑ ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ተጋጣሚዎቻቸውን ድባቅ መትተዋል። የዓለም ምርጡ ሊዮኔል ሜሲን ይዞ ትናንት ወደ ሜዳ የገባው ባርሴሎና አትሌቲኮ ቢልባዎን 6 ለ ባዶ በሆነ ከባድ ምት አደባይቶታል። በትናንቱ ጨዋታ ለባርሴሎና ቀዳሚዋን ግብ በ7ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ትንግርተኛው ሊዮኔል ሜሲ ነው። ከዛም በ31ኛው ደቂቃ ላይ ኔይማር ሁለተኛዋን ግብ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። በ47ኛው፣ 69ኛው እና 82ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሉዊስ ሱዋሬዝ ሦስት ግቦችን አከታትሎ በማግባት ሄትትሪክ ሠርቷል። በትናንቱ ሦስት ግብም ሉዊስ ሱዋሬዝ እስከ ዛሬ ከመረብ ያሳረፋቸው ግቦችን 18 በማድረስ የላሊጋው ኮከብ ግብ አግቢነቱን ተቆናጧል። ኔይማር በ16 ይከተለዋል። ኢቫን ራኪቲች በ62ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ግብ ከመረብ አሣርፏል።

በስፔን ላሊጋ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ባርሴሎና አትሌቲኮ ቢልባዎን ከነገ በስተያ በድጋሚ ለአምስተኛ ጊዜ ያገኘዋል። ሁለቱ ቡድኖች ረቡዕ ዳግም ሜዳ ላይ ሲገናኙ በአራት ቀናት ልዩነት ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። አትሌቲኮ ቢልባዎ ትናንት ከካምፕ ኑ ስታዲየም የሽንፈት ማቁን ተከናንቦ ሲወጣ በዕለቱ ዳኝነት እያማረረ ነበር። ሆኖም ግብ ጠባቂው ጎራክ ኢራይዞዝ ከአምስት ደቂቃ በኋላ ከሜዳ የተሰናበተው ሉዊስ ሱዋሬዝን ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ጠልፎ በመጣሉ ነው። የተገኘችውን ፍጹም ቅጣት ምት ከመረብ ያሳረፈው ሊዮኔል ሜሲ በሁለተኛው አጋማሽ በቱርክ ብሔራዊ ቡድን አማካዩ አርዳ ቱራን ተቀይሮ ወጥቷል። ባርሴሎና ዛሬ እንዳስታወቀው በትናንቱ ጨዋታ ሊዮኔል ሜሲ የጡንቻ መሸማቀቅ ደርሶበታል። እናም አሠልጣኙ ሉዊስ ኤንሪኬ አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲን ትናንት በሁለተኛው አጋማሽ መቀየራቸው ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ዛሬ ተናግረዋል።

የዓለም ምርጡ ሊዮኔል ሜሲ
የዓለም ምርጡ ሊዮኔል ሜሲምስል picture-alliance/dpa/A. Wiegmann
የኤቨርተኑ ሮሜሉ ሉካካ
የኤቨርተኑ ሮሜሉ ሉካካምስል picture alliance/dpa
አሠልጣኝ ቫን ጋል
አሠልጣኝ ቫን ጋልምስል picture-alliance/dpa/N. Roddis

በስፔን ላሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያ ታሪክ በተደጋጋሚ ዋንጫውን በእጃቸው በማስገባት ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ቢልባዎ ከጥቂቶቹ ውስጥ ይመደባሉ። ባርሴሎና ለ27 ጊዜያት እንዲሁም አትሌቲኮ ቢልባዎ ለ23 ጊዜያት የዋንጫው ባለቤት ለመሆን የቻሉ ጠንካራ ቡድኖች ናቸው። በእርግጥ አትሌቲኮ ቢልባዎ ዘንድሮ ከባርሴሎና በ17 ነጥብ ተበልጦ 28 ነጥብ በመያዝ በደረጃ ሠንጠረዡ 9ኛ ላይ ነው የሚገኘው። ባርሴሎናዎች ባስኮቹን የአትሌቲኮ ቢልባዎ ተጨዋቾች እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2009፣ 2012 እና 2015 ለፍፃሜ አግኝተው ድል ነስተዋቸዋል። አትሌቲኮ ቢልባዎ ለመጨረሻ ጊዜ ባርሴሎናን ያሸነፈው ከዛሬ 32 ዓመት በፊት በ1984 ነው።

ሌላኛው የላሊጋው ኃያል ሪያል ማድሪድም ልክ እንደ ባርሴሎና በግብ ተንበሽብሾ ነው ያመሸው። በደረጃ ሰንጠረዡ ከባርሴሎና ዝቅ ብሎ በያዘው 43 ነጥብ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሪያል ማድሪድ፦ስፖርቲንግ ዢዮንን 5 ለ 1 አሸንፏል። ለሪያል ማድሪድ ግቦቹን ያስቆጠሩት፦ በ7ኛው ደቂቃ ጋሬት ባሌ፣ በ9ኛው እና 18ኛው ደቂቃ ላይ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ እንዲሁም በ12ኛው እና 41ኛው ደቂቃ ካሪም ቤንዜማ ናቸው። ስፖርቲንግ ዢዮን ከባዶ ከመሸነፍ ያዳነችውን ግብ በ62ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ኢስማ ሎፔዝ ነው።

ሪያል ማድሪድ በአዲሱ አሠልጣኝ ዚነዲን ዚዳን መመራት ከጀመረ ወዲህ በተከታታይ አምስት ግቦችን በማስቆጠር ትናንት ሲያሸንፍ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። የትናንቱ ድል ግን የአሠልጣኝ ዚነዲን ዚዳን ሁለት ተጨዋቾችን ለጉዳት ዳርጓል። በላሊጋው 13 ግቦችን በማስቆጠር ከነ ኔይማር እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ዝቅ ብሎ የሚገኘው ጋሬት ባሌ እና፤ ከእነ ሮናልዶ ጋር እኩል 16 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈው ካሪም ቤንዜማ በትናንቱ ጨዋታ ተጎድተዋል።
ስፖርቲንግ ዢዮን ከሌቫንቴ በአንድ ነጥብ ከፍ ብሎ በያዘው 15 ነጥብ በደረጃ ሠንጠረዡ 19ኛ ላይ ይገኛል። የደረጃ ሠንጠረዡን አትሌቲኮ ማድሪድ በ47 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ባርሴሎና በ45 ነጥብ ሁለተኛ ነው። ትናንት ቫሌንሺያ እና ራዮ ቫሌካኖ ሁለት እኩል ተለያይተዋል። ጌታፌ ኤስፓኞላን 3 ለ1 ረትቷል። ዛሬ ማታ አይበር ከግራናዳ ይጋጠማሉ።

የ27 ዓመቱ ጀርመናዊ የእግር ኳስ ተጨዋች ሜሱት ኦትሲል የጀርመን ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን የዓመቱ ምርጥ ተብሎ ዘንድሮም ለአራተኛ ጊዜ ተመርጧል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ለአርሰናል ተሰልፎ የሚጫወተው የቱርክ ዝርያ ያለው ሜሱት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2011፣ 2012 እና በ2013 በተከታታይ የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች መባሉ ይታወሳል። በ2014 የጀርመን የዓመቱ ምርጥ ተብሎ የተመረጠው ቶኒ ክሮስ ነበር። ዘንድሮ ግን ሜሱት ኦትሲል 45,0 ከመቶ ድምጽ በማግኘት የዓመቱ ኮከብ ተጨዋችነቱን አስመልሷል። በብሔራዊ ቡድን እና በቡድን ጨዋታዎች በተገኘው አጋጣሚ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር የሚታወቀው ቶማስ ሙይለር 15,9 ከመቶ በማግኘት ሁለተኛ የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች ተብሏል። የኮለኑ ዮናስ ሔክቶር በ13,6 ከመቶ ድምጽ ሦስተኛ ወጥቷል። ለምርጫ የቀረቡት በአጠቃላይ 13 ተጨዋቾች ነበሩ።

የዓለም የሜዳ ቴኒስ ስፖርት የሙስና ቅሌት እንዳጠላበት ዛሬ ይፋ ኾኗል። የስፖርት ባለሥልጣናት የተጨዋቾች የግጥሚያ ድልድል ሲወጣ በግጥሚያ እንዲገናኙ የሚፈልጓቸውን ተጨዋቾች በሙስና እንዲገናኙ በማድረግ ሙስና ሲፈፀም የስፖርቱ ባለሥልጣናት ችላ ብለዋል የሚል ወቀሳ ቀርቦባቸዋል። ታዋቂው እና ዝነኛው የሜዳ ቴኒስ ባለድል ኖቫክ ጄኮቪች በበኩሉ በቀጥታ ባይኾንም እኔን በሚቀርቡኝ ሰዎች በኩል የተጨዋቾች ድልድል ላይ እነሱ በሚፈልጉት መንገድ እንድስማማ ተጠይቄ ነበር ብሏል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለቻን 2016 አፍሪካ ዋንጫ ትናንት ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ባከናወነው ጨዋታ የ3 ለባዶ ሽንፈት ገጥሞታል። ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሦስቱን ግቦች ያስቆጠሩት ሉሳዲሱ በ45ኛው፣ ሉቩምቡ በ46ኛው እንዲሁም ሜስቻክ በ58ኛው ደቂቃ ላይ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Symbolbild Tennis ATP World Tour
ምስል picture-alliance/dpa/J.C. Hidalgo

አዜብ ታደሰ