ስፖርት፤ ጥር 14 ቀን፣ 2010 ዓ.ም.
ሰኞ፣ ጥር 14 2010ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በሙምባይ ማራቶን በወንድም በሴትም ድል ተቀዳጅተዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ሊቨርፑል ዛሬ ማታ ተስተካካይ ጨዋታውን ያደርጋል። ማንቸስተር ሲቲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ቸልሲ፣ ቶትንሀም እና አርሰናል በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ድል ቀንቷቸዋል። የቦን ከተማ ተጎራባቹ ኮሎኝ ቡድን ቅዳሜ እለት ባደረገው ግጥሚያ በቡንደስ ሊጋ የመቆየት እድሉን ከማጨለም ተርፏል። በስፔን ላሊጋ በግብ የተንበሸበሸው ሪያል ማድሪድ የማታ ማታ አጥቂው ክሪስቲያኖ ሮናልዶን ለጉዳት ዳርጓል። በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ጀርመናዊቷ አንጄሊካ ኬርበር እና ስዊትዘርላንዳዊው ሮጀር ፌዴሬርስ በቀላሉ ወደ ሩብ ፍጻሜ አልፈዋል። ሌላኛው የዓለማችን ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ኖቫክ ጆኮቪች ግን አልተሳካለትም።
አትሌቲክስ
ሕንድ ሙምባይ ከተማ ውስጥ ትናንት በተከናወነው 15ኛው የታታ ሙምባይ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢታዮጵያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም አሸናፊ ኾነዋል። ከፍተኛ ፉክክር በታየበት የወንዶች የማራቶን ሩጫ ፉክክር አንደኛ የወጣው ሰለሞን ደቂሳ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ 2:09:34 ነው። አፍታም ሳይቆይ በ26 ሰከንዶች ልዩነት ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ሹመት አካልነው ሁለተኛ ወጥቷል። ከሹመት በ30 ሰከንድ ልዩነት ያጠናቀቀው ጆሹዋ ኪፕኮሪር የተሰኘው የኬንያ ሯጭ የሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል። ሹሚ ደቻሳ በአራተኛነት አጠናቋል።
በሴቶች የሙምባይ ማራቶን የሩጫ ፉክክር አንዲት ኬንያዊት ጣልቃ ከመግባቷ በስተቀር ከአንደኛ እስከ 5ኛ ደረጃ የኢትዮጵያውያቱ ኾኗል። ኢትዮጵያዊቷ አማኔ ጎበና 2:25:49 ሮጣ በአንደኛነት በአሸነፈችበት ውድድር ኬንያዊቷ ቦርኔስ ኪቱር ሁለተኛ ወጥታለች። ኬንያዊቷ ከአማኔ 3 ደቂቃ ዘግይታ በመግባት ነው ሁለተኛ የወጣችው። ኢትዮጵያውያቱ ሹኮ ጌኔሞ፣ ብርቄ ደበላ እና ኩፍቱ ታሂር እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ተቆጣጥረውታል።
ከዛው ከማራቶን የሩጫ ውድድር ዜና ሳንወጣ፦ የሦስት ጊዜያት የኦሎምፒክ ባለድሉ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በለንደኑ ማራቶን ሞ ፋራህን እንደሚገጥም ተዘግቧል። የለንደን ማራቶን ውድድር ከሦስት ወራት በኋላ ሚያዝያ 14 ነው የሚካሄደው። የ5,000 እና 10,000 ሜትር ርቀት ውድድር የዓለም ክብር ወሰን ባለቤት አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ኬንያዊው ዳንኤል ዋንጂሩ ባሸነፈበት የባለፈው ዓመት የለንደን ማራቶን ፉክክር በሁለተኛነት ነበር ያጠናቀቀው። ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ። ከኬንያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ እና ከብሪታንያዊው ሰር ሞ ፋራህ ጋር ተሰልፎ የሚሮጠው አትሌት ቀነኒሳ ሚያዝያ ወር ላይ ጠንካራ ፉክክር ይገጥመዋል።
እግር ኳስ
አፍሪቃ ውስጥ የሚገኙ ተጨዋቾች ብቻ በሚሳተፉበት የአፍሪቃ ዋንጫ ግጥሚያ ዛሬም ቀጥሎ በሚደረግ ግጥሚያ ምሽት ላይ አራት ጨዋታዎች ይከናወናሉ። አይቮሪኮስት ከኡጋንዳ፣ ናይጀሪያ ከኢኳቶሪያል ጊኒ ፤ ዛምቢያ ከናሚቢያ እና ሩዋንዳ ከሊቢያ ምሽቱን ይፋለማሉ። አዘጋጇ ሞሮኮ ትናንት ከሱዳን ጋር ያለምንም ግብ ተለያይታለች። ጊኒ ሞሪታንያን 1 ለ0 አሸንፋለች። የዋንጫ ውድድሩ የሚከናወነው ከ11 ቀን በኋላ እሁድ ጥር 25 ቀን ነው። በውድድሩ ማለፍ ያልቻለችው ኢትዮጵያ ፌዴሬሽኗ አሁንም በመወዛገብ ላይ ይገኛል።
ፕሬዚዳንት እና ሥራ አስፈጻሚዎችን ለመመረጥ የተቸገረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሦስተኛ ጊዜ ያራዘመውን የምርጫ ሒደት ለማከናወን የገባው ቀጠሮ አንድ ወር ግድም ይቀረዋል። ውዝግቡን ሲከታተል የነበረው ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን (FIFA)ባደረገው ግፊት የምርጫ ሒደቱ ለሦስተኛ ጊዜ ከተራዘመ በኋላ ኹኔታዎች ምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ? የሶከር ኢትዮጵያ ድረ-ገጽ መራኄ አርታኢ ኦምና ታደለ ለፌዴሬሽኑ ምርጫ የቀረቡ ዕጩዎች «ክፍፍልን አስከትሏል» ብሏል።
አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል ዛሬ ማታ ወሳኝ ጨዋታውን ከስዋንሲ ሲቲ ጋር ያደርጋል። ሊቨርፑል የዛሬውን ግጥሚያ ከ3 ግብ በላይ ካሸነፈ የቸልሲን 3ኛ ደረጃ ይረከባል። በሊቨርፑል ዘንድሮ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ባለፈው ውድድር የቀመሰው መሪው ማንቸስተር ሲቲ ከትናንት በስትያ ኒውካስትልን 3 ለ1 ሸኝቶ ነጥቡን 65 አድርሷል። በእለቱ 24ኛ ግጥሚያውን አከናውኖ በርንሌይን አንድ ለባዶ ያሸነፈው ማንቸስተር ዩናይትድ በ53 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 42 ነጥብ ይዞ 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ቅዳሜ እለት ክሪስታል ፓላስን 4 ለ1 አንኮታኩቷል፤ ከቶትንሀም በ3 ነጥብ ይበለጣል። ትናንት ከሳውዝሀምፕተን ጋር አንድ እኩል አቻ የተለያየው ቶትንሀም 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በደረጃ ሰንጠረዡ ዝቅ ብሎ 16ኛ ላይ የሚገኘው ብሪንግቶንን ቅዳሜ እለት 4 ለ0 ያደባየው ቸልሲ ረቡእ እለት ከበርመስ ጋር ይጋጠማል።
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ግጥሚያ በቬርደር ብሬመን እየተመራ የነበረው መሪው ባየር ሙይንሽን ትናንት 4 ለ2 አሸንፏል። ሻልከ ከሀኖቨር 1 ለ1 አቻ ተለያይቷል። 31 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባየር ሌቨርኩሰንን በ16 ነጥብ ርቆ ሄዷል። ከባየር ሌቨርኩሰን እኩል 31 ነጥብ ያላቸው፦ ሻልከ፤ ላይፕሲሽ እና ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በተከታታይ ከ3ኛ እስከ 4ኛ ደረጃ ተቆናጠዋል። የባየር ሙይንሽን የበርካታ ጊዜያት ተፎካካሪ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዘንድሮ ብዙም አልሆነለትም፤ 30 ነጥብ ይዞ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቅዳሜ እለት ሐምቡርግን 2 ለ0 ያሸነፈው ኮሎኝ ከቡንደስ ሊጋው ሙሉ ለሙሉ ይወርዳል የሚለውን ስጋት ለጊዜው ገፏል። 12 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ ጥግ ላይ በ18ኛነት የሚገኘው ኮሎኝ 16ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቬርደር ብሬመን የሚለየው በ4 ነጥብ ብቻ ነው።
በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድ ትናንት ዲፖርቲቮ ላኮሩኛን 7 ለ1 በኾነ ሰፊ የግብ ልዩነት አይቀጡ ቅጣት ቀጥቷል። በእለቱ ግጥሚያ ለሪያል ማድሪድ 6ኛዋን ለራሱ ደግሞ 2ኛውን ግብ በጭንቅላት ገጭቶ ያስቆጠረው ፖርቹጋላዊው አጥቂ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ቅንድቡ ላይ ተገጭቶ ፊቱ በደም አበላ ተውጦ ታይቷል። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ጉዳት የደረሰበት በስዊትዘርላንዳዊው የዲፖርቲቮ ላኮሩኛ የመሀል ተመላላሽ ተጨዋች ፋቢያን ሼይር ነው። ፋቢያን 84ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ ለማውጣት እንጂ ሆን ብሎ ክሪስቲያኖ ላይ ጉዳት አለማድረሱን ተናግሯል። «ያሳዝናል መልበሻ ክፍል ውስጥ ድጋሚ አላየሁትም፤ ግን እዛው ሜዳ ውስጥ ተቀይሮ ሲወጣ ይቅርታ ጠይቄዋለሁ» ብሏል። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሜዳው ውስጥ እያለ ከቡድኑ ሐኪም የእጅ ስልክ ጠይቆ የተጎዳ ፊቱን ተመልክቷል። ይህን ድርጊቱንም አንዳንዶች ሮናልዶ የገዛ መልኩ እና ቁመናው ላይ የመመሰጥ ፍላጎቱን ይበልጥ አጉልቶ የሚያሳይ ነው ሲሉ ተችተዋል። ሌሎች ምን ችግር አለ ሲሉ ተከራክረዋል። ሊኔል ሜሲ በገነነበት የትናንቱ ምሽት የላሊጋ መሪው ባርሴሎና ሪያል ቤቲስን 5 ለ0 ድል አድርጓል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ