ስፖርት፤ ጥር 18 ቀን፣ 2012 ዓ.ም
ሰኞ፣ ጥር 18 2012በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የእግር ኳስ ፍልሚያ የፕሬሚየር ሊጉ ዋነኛ ተዋናዮች ድል ሲቀናቸው በወጣት ተጨዋቾቹ ተማምኖ የነበረው ሊቨርፑል በአቻ ተለያይቷል። በመልሱ ጨዋታም ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ዋናውን ቡድናቸውን እንደማያሰልፉ ተናግረዋል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን ዳግም አንሰራርቶ ወደ ቀድሞ አቋሙ ተመስልሷል፤ በዚህ አካሄዱ ዘንድሮ ዋንጫ ሊወስዱ ከሚችሉ ጥቂት ቡድኖች መካከል ቀዳሚ መኾን ችሏል። በጣሊያን ሴሪ ኣ ሮናልዶ ግብ ቢያስቆጥርም ቡድኑን ከሽንፈት መታደግ አልቻለም። በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና በቫለንሺያ ድል ተነስቷል። ሪያል ማድሪድ በመሪነቱ እየገሰገሰ ነው። ተጨማሪ ዘገባዎች ይኖረናል።
የሎስ አንጀለስ ሌከርስ የቅርጫት ኳስ ተጨዋች የነበረው ዝነኛው የ41 ዓመቱ ኮቤ ብራያን የግል ሔሊኮፕተሩ ተከስክሳ ከታዳጊ ሴት ልጁ እና ሌሎች ተሳፋሪዎች ጋር ሕይወቱ ማለፉ በመላው ዓለም የሚገኝ የስፖርት አፍቃሪን እጅግ አሳዝኗል። በዩናይትድ ስቴትስ ተወዳጁ ብሔራዊ የቅርጫት ኳስ ማኅበር (NBA)ለ18 ጊዜያት የምርጥ ተጨዋችነት ግርማን የተጎናጸፈው ኮቤ በሎስ አንጀለስ ሌከርስ ቡድን የኹለት ዐሥርተ ዓመት ቆይታው ለአምስት ጊዜያት ዋንጫ ያነሳ ሲኾን፤ የዘመኑ ምርጥ የዓለማችን የቅርጫት ኳስ ተጨዋች ነበር። ለኹለት ጊዜያትም የኦሎምፒክ ሜዳሊያ አግኝቷል።
ኮቤ፤ የ13 ዓመት ታዳጊ የኾነችው ልጁ ጂያና እና ሌሎች ሰባት ተሳፋሪዎችን የጫነችው ሔሊኮፕተር እሁድ ዕለት በካሊፎርኒያ ግዛት ካላባሳስ በተባለችው ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ስፍራ ነበር የተከሰከሰችው። ከተሳፋሪዎቹ መካከል አንድም የተረፈ የለም። ሌላኛው ዘመን የማይሽረው የዓለማችን ዝነኛ የቅርጫት ኳስ ተጨዋች ማይክል ጆርዳን ኮቤን «እንደ ታናሽ ወንድሜ» ነበር የማየው ሲል የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጧል።
በተለይ ኮቤ በልጅነቱ እና ወጣትነቱ በርካታ ዓመታትን ያሳለፈባት ሀገር ጣሊያን የስፖርት ፌዴሬሽን ጥልቅ ሐዘኑን በመግለጥ በሚቀጥለው አንድ ሳምንት ውስጥ ማንኛውም ስፖርታዊ ጨዋታ ከመከናወኑ አስቀድሞ ለኮቤ የደቂቃ የኅሊና ጽሞና እንዲደረግ ወስኗል። በሔሊኮፕተሩ ተሳፍራ የነበረችው የኮቤ ሴት ልጅ ጂያና ስሟን ከጣሊያን ነው ያገኘችው። በጭጋጋማ የአየር ኹኔታ ወቅት 9 ሰዎችን ጭና የተከሰከሰችው ሔሊኮፕተር አደጋ መንስዔ እየተጣራ ነው።
እግር ኳስ
በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች በፕሬሚየር ሊጉ ታዋቂ የኾኑ ቡድኖች ከሊቨርፑል በስተቀር አሸንፈዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ ሮቨርስን ያንኮታኮተበት ድል በግብ ክፍያ ከፍተኛው ነው። ሮቨርስ ትናንት ከማንቸስተር ዩናይትድ ስድስት ግቦች ሲቆጠሩበት በዜሮ ከመውጣት ውጪ ምንም አማራጭ አልነበረውም። አንድ ተጨዋቹን ያጣው ፉልሃምን ማንቸስተር ሲቲ ያሸነፈው 4 ለ0 ነው። ቸልሲ ሁል ሲቲን 2 ለ1 ድል አድርጓል። ቶትንሀም ከሳውዝሀምፕተን ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል።
ባለፈው ግጥሚያ ወጣት ተጨዋቾቹን አሰልፎ ድል የቀናው የዬርገን ክሎፕ ሊቨርፑል ትናንት እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ በተፋለሙት የሽሬስውቤሪ ተጨዋቾች ጉድ ኾኗል። በኩርቲስ ጆነስ ገና በ6ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ሊቨርፑል የመጀመሪያዋን ግብ አስቆጥሮ መምራት የጀመረው። 46ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ዶናልድ ሎብ ኹለተኛዋን በማስቆጠር ሊቨርፑል ከረፍት መልስ የገባው ኹለት ለዜሮ በመምራት ነበር። በእንግሊዝ ሦስተኛ ዲቪዚዮን የሚገኘው ተጋጣሚው ሽሬውስቤሪ ተጨዋቾች ግን እስከ መጨረሻው ተፋልመው ኹለት እኩል መውጣት ችለዋል። የመልሱ ጨዋታ ላይ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ዋና ቡድናቸውን እንደማያሰልፉ ይፋ አድርገዋል። ዋናው ቡድን እና ዬርገን ክሎፕ ረፍት ሲያደርጉ ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ያሉ ተጨዋቾችን ይዘው ለመልሱ ጨዋታ የሚሰናዱት የቡድኑ ወጣት አሰልጣኝ ናይል ክሪችሌይ ናቸው ተብሏል። ዛሬ በርመስ እና አርሰናል ለኤፍ ኤ ካፕ ይጋጠማሉ።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን ዳግም ድል ቀንቶታል። ቅዳሜ ዕለት ሻልከን 5 ለ0 ነው ያንኮታኮተው። ቀዳሚዋን ግብ በ6ኛው ደቂቃ ላይ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ሲያስቆጥር፤ ኹለተኛዋን በመጀመሪያው አጋማሽ 47ኛ ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ቶማስ ሙይለር ነው። ለባየር ሙይንሽን ሊዮን ጎሬትስካ በ50ኛው ደቂቃ ላይ ሦስተኛውን ከመረብ አሳርፏል። ቲያጎ እና ሠርጌ ግናብሬ በ58 እና 89 ደቂቃ ላይ ቀሪዎቹን ግብ አስቆጥረዋል። በተለይ ቶማስ ሙይለር ወደ ቀድሞ ግብ የማስቆጠር ብቃቱ መመለሱ፤ የቡድኑ ሜዳ ላይ መናበብ ባየር ሙይንሽን ዋንጫውን ዘንድሮ ሊያሸንፍ ይችላል አስብሏል።
በእርግጥ በአንድ ነጥብ ልዩነትም ቢኾን በቡንደስሊጋው በመሪነት የሰፈረው ላይፕሲሽ ነው። 40 ነጥብ ያለው ላይፕሲሽ ከትናንት በስትያ በአይንትራኅት ፍራንክፉርት 2 ለ0 ተሸንፏል። 38 ነጥብ ይዞ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ቅዳሜ ዕለት ማይንትስን 3 ለ1 ድል አድርጓል። ሆፈንሃይም ቬርደር ብሬመንን ትናንት 3 ለ0 አሸንፏል። ባየር ሌቨርኩሰን ከፎርቱና ዱይስልዶርፍ ጋር ትናንት ያከናወኑት ጨዋታ በወሳኝነቱ የሚጠቀስ ነበር። ባየር ሌቨርኩሰን ከ6ኛ ደረጃ ከፍ ብሎ በቀጣይ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደሚያስገባው አምስተኛ ደረጃ ለመድረስ ፎርቱና ዱይስልዶርፍ ደግሞ ከ18ኛ ደረጃ ለመውጣት ነበር የተፋለሙት። ፎርቱና ዱይስልዶርፍ 15 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ 18ኛ ላይ ተዘርግቷል። ለጊዜው የአውሮጳ ሊግ የምድብ ተጋጣሚ የሚሳተፉበት አምስተኛ ደረጃ ላይ ያለው ባየር ሌቨርኩሰን ከቦሩስያ ዶርትሙንድ የሚበለጠው በ4 ነጥብ ብቻ ነው። ለሻፕሚዮንስ ሊግ አላፊ ከኾኑት ውስጥ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዐርብ ዕለት ኮሎኝን 5 ለ1 ድል አድርጎ ነጥቡን 36 አድርሷል። በቡንደስ ሊጋው ከ1 እስከ 7ና ደረጃ ያሉት ቡድኖች የመጀመሪያው እና 7ኛው የነጥብ ልዩነታቸው ስድስት ብቻ ነው። መሪው ላይፕሲሽ 40 ነጥብ ሲኖረው 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አለው ሆፈንሃይም 30 ነጥብ ሰብስቧል።
ሴሪኣ
በጣሊያን ሴሪኣ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ናፖሊ ላይ ግብ ማስቆጠር ቢችልም ቡድኑ ጁቬንቱስ ግን 2 ለ1 መሸነፉ አልቀረለትም። ጁቬንቱስ መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው እስኪጠናቀቅ ድረስ በናፖሊ 2 ለ0 እየተመራ ነበር። የማታ ማታ ግን ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ቡድኑን በባዶ ከመሸነፍ ያዳነችውን ብቸኛ ግብ በ90ኛው ደቂቃ ላይ ማስቆጠር ችሏል። ጁቬንቱስ በትናንቱ ግጥሚያ ሽንፈት ቢገጥመውም ሴሪአውን ግን በ51 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ኢንተር ሚላን በ48፤ ላትሲዮ በ46 ኹለተኛ እና ሦስተኛ ኾነው ይከተሉታል። 39 ነጥብ የሰበሰበው ላትሲዮ በአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት ጁቬንቱስን ያሸነፈው ናፖሊ 27 ነጥብ ይዞ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ላሊጋ
በስፔን ላሊጋ የእነ ሊዮኔል ሜሲ ባርሴሎናም ሽንፈት ቀምሷል። ምንም እንኳን ሊዮኔል ሜሲ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ቢያደርግም ቡድኑ ባርሴሎና በቫለንሺያ መሸነፉ አልቀረለትም። ቫሌንሺያ የመጀመሪያዋን ግብ 48ኛው ደቂቃ ላይ ያገኘው ማክሲ ጎሜዝ የመታትን ኳስ ጆርዲ አልባ በትከሻው ገጭቶ በራሱ መረብ ላይ በማረፏ ነው። ማክሲ ጎሜዝ በዕለቱ በርካታ ግብ መኾን የሚችሉ ኳሶችን በድንቅ ኹኔታ ያጨናገፈው ግብ ጠባቂው ማርክ አንድሬ ቴር ስቴጋን አፍዝዞ 77ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፋት ኹለተኛ ግብ አስደማሚ ነበረች። ግብ ጠባቂው ስቴገን ፒኬ በመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ያገኘውን ፍጹም ቅጣት ምትም በድንቅ ኹኔታ አጨናግፎ ነበር። ግብ ጠባቂው ባርሴሎና ቢሸነፍም በእለቱ ብቃቱን አሳይቷል።
አትሌቲክስ
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀንን (ማርች 8) ምክንያት በማረግ ላለፉት 16 ዓመታት ቅድሚያ ለሴቶች በሚል መርህ በሃገራችን የሚከበረውን የሴቶች ቀንን ለማክበር እና የ ሴቶችን ስኬት ለማክበር እንዲሁም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማበረታታት በሚል የ5ኪሜ የሩጫ ውድድር ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ የዘንድሮ ውድድርንም መጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሂድ የውድድሩ አዘጋጆች በኢሜል የላኩት መረጃ ይጠቅሳል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ