1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ጥር 23 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

ሰኞ፣ ጥር 23 2008

ኃያሉ ሪያል ማድሪድ ኤስፓኞላን 6 ለዜሮ አንኮታኩቶዋል። የዓለማችን ምርጡ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሦስት ግቦችን በተከታታይ በማስቆጠር ሔትትሪክ ሠርቷል። የስፔን ላሊጋ፤ የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ እንዲሁም የጀርመን ቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ውጤቶችን አሰባሰብናል። በሜዳ ቴኒስ የፍፃሜ ፍልሚያ ያልተጠበቁ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

https://p.dw.com/p/1Hn8J
Handball EM Finale - Deutschland vs. Spanien
ምስል Getty Images/Bongarts/A. Nurkiewicz

[No title]

በእንግሊዝ FA cup ዋንጫ ቅዳሜ ዕለት ሊቨርፑል ከዌስትሐም ዩናይትድ ያለምንም ግብ ተለያይቷል። በጨዋታው ብልጫ ያሳየው ሊቨርፑል ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርግም ግብ ማስቆጠር ግን አልቻለም። ትናንትና ኤቨርተን ካርሊስሌን 3 ለባዶ እንዲሁም ቸልሲ ሜ ኬ ዶንስን 5 ለ1 ማሸነፍ ችለዋል። ሊቨርፑል እና ዌስትሐም ብሮሚች እንዲሁም ዌስትሐም ዩናይትድ ከፔተርቦዎው የነገ ሣምንት ዳግም ይገናኛሉ። ነገ ደግሞ የፕሬሜየር ሊግ 24ኛ ሣምንት ግጥሚያ ይቀጥላል።

ጆን ቴሪ ከቸልሲ ቡድን ራሱን እንደሚያሰናብት ገልጿል። ጆን ቴሪ ገና የ14 ዓመት ታዳጊ ሳለ የተቀላቀለው ቡድኑን ትቶ ለመሄድ የተገደደው ሰማያዊዎቹ ቸልሲዎች «የተለየ መንገድ መከተል በመጀመራቸው» ነው ብሏል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ለረዥም ዓመታት በአንድ ቡድን ውስጥ ከተጫወቱ ጥቂት ተጨዋቾች ውስጥ ጆን ቴሪም ይመደባል። ለሰማያዊ ለባሾቹ ለ696 ጊዜያት ተሰልፏል። በፕሬሚየር ሊግ ደግሞ 477 ጊዜ ተጫውቷል። ቡድኑ በርካታ ስኬቶችን ባስመዘገበባቸው ዘመናት አምበል ሆኖ አገልግሏል። የ35 ዓመቱ ተከላካይ ጆን ቴሪ በቸልሲ ቆይታው 40 ግቦችን በማስቆጠር ከእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ተከላካዮች ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል።

ለረዥም ጊዜ በመሰለፍ ከሁሉም ቀዳሚው ግን ለማንቸስተር ዩናይትድ ለ632 ጊዜያት መሰለፍ የቻለው ሪያን ጊግስ ነው። የሊቨርፑሎቹ ጄሚ ካራጋር ለ508 ጊዜ እንዲሁም ሽቴፋን ዤራርድ ለ504 ጊዜያት በመሰለፍ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ከዚያም ፖል ስኮልስ ለ499 ጊዜያት የማንቸስተርን መለያ ለብሶ በመጫወት አራተኛ ደረጃ ሲይዝ፤ የቸልሲው ጆን ቴሪ አምስተኛ ነው። ከቸልሲእንደወጣ ወደየት እንደሚያቀና ባይገልጽም፤ እንግሊዝ ውስጥ ለሚገኙ ቡድኖች እንደማይጫወት ግን በእርግጠኝነት ተናግሯል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ የክረምቱ ረፍት ለቦሩስያ ዶርትሙንድ ስኬት ይዞ ነው የመጣው። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን ባለፈው ሣምንት 3 ለ1 የረታው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቅዳሜ ዕለት ደግሞ ኢንግሎሽታድትን 2 ለዜሮ ሸኝቷል። ቡንደስሊጋውን ዘንድሮ የተቀላቀለው ኢንግሎሽታድት ለቦሩስያ ዶርትሙንድ ፈተና ኾኖ ነው ያመሸው። የቦሩስያ ዶርትሙንድ አሠልጣኝ ቶማስ ቱሽል በጣምራ ድሉ እጅግ መደሰታቸውን ገልጠዋል።

«ጨዋታው አደገኛ ነበር። ከራሳችን ጋር፤ ከባላጋራችን ጋር፤ ከአየር ጠባዩ ጋር ብሎም ከሜዳው ጋር ታግለናል። ከባድ ጨዋታ ነው ያኪያሄድነው። በእንደዚያ አይነት ኹናቴ እንደሚከሰተው ሁሉ በጣም አስቸጋሪ ጨዋታ ነበር። ያም በመሆኑ ጥርሳችንን በመንከስ ጨዋታውን ማሸነፋችን ወሳኝ ነበር። ጣምራ ድል በለው። ለአውባሜያንግ በግሉ ዕፁብ ድንቅ ነበር። ግላድባኅን በረታንበት ታላቅ ድል በእዚህኛው የተቆጠሩት ሁለት ግቦች ለእኛ እጅግ ወሳኝ ነበሩ።»

ፒዬር ኤመሪክ አውባሜያንግ እሁድ ያገባቸው ግቦች 19ኛ እና 20ኛ ኾነው ተመዝግበውለታል። በቡንደስ ሊጋው ብዙ ግብ በማስቆጠር እየመራ ይገኛል። የባየር ሙይንሽኑ አጥቂ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ በ17 ግቦች ይከተለዋል።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ በቅዳሜው ድል ያገኘው ሦስት ነጥብ ተደምሮለት አሁን 44 ነጥብ አለው። ከመሪው ባየር ሙይንሽን በስምንት ነጥቦች ልዩነት በደረጃ ሠንጠረዡ ሁለተኛ ነው።

የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ፒዬር ኤመሪክ አውባሜያንግ
የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ፒዬር ኤመሪክ አውባሜያንግምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen
የቸልሲው ጆን ቴሪ
የቸልሲው ጆን ቴሪምስል Reuters

መሪው ባየር ሙይንሽን እሁድ ሆፈንሐይምን 2 ለባዶ ሸኝቷል። ቮልፍስቡርግ ከኮሎኝ 1 ለ1 አቻ ወጥቷል። ባየር ሌቨርኩሰን ሐኖቨርን ከትናንት በስትያ 3 ለዜሮ ድል አድርጓል። አይንትራኅት ፍራንክፉርት ከአውስቡርግ ያለምንም ግብ ተለያይቷል። ሻልከ ዳርምሽታድትን 2 ለባዶ አሸንፏል። ቬርደር ብሬመን በደረጃ ሠንጠረዡ 34 ነጥብ ይዞ በሦስተኛነት ከሚገኘው ሔርታ ቤርሊን ጋር 3 እኩል ወጥቷል። ሐምቡርግ በሽቱትጋርት 2 ለ1 ተሸንፏል።

በስፔን ላሊጋ የሣምንቱ ማሳረጊያ ግጥሚያ ኃያሉ ሪያል ማድሪድ ኤስፓኞላን ትናንት 6 ለዜሮ ድባቅ በመምታት አይበገሬነቱን አሳይቷል። ለሪያል ማድሪድ ሦስቱን ግቦች ያስቆጠረው የፖርቹጋሉ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነው። ሪያል ማድሪድ በቤንዜማ ቀዳሚነት የመጀመሪያዎቹን ሦስት ግቦች ያስቆጠረው ጨዋታው በተጀመረ በ16 ደቂቃዎች ውስጥ ነበር። ዚነዲን ዚዳን ማድሪድን ከአሠልጣኝ ራፋኤል ቤኒቴዝ ከተረከበ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ አራት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችሏል። 10 ነጥቦችን በመሰብሰብም 17 ግቦችን አስቆጥሯል።

ላ ፓልማ ሴልታቪጎን 2 ለ1፤ ሴቪላ ሌቫንቴን 3 ለ1 እንዲሁም ስፖርቲንግ ጂዮን ቫሌንሺያን 1 ለምንም አሸንፈዋል። 21 ነጥብ ብቻ ያለው ስፖርቲንግ ጂዮን በ17ኛነት የደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ላይ ተጋድሟል። ቅዳሜ ዕለት አትሌቲኮ ማድሪድን 2 ለ1 ያሸነፈው ባርሴሎና የደረጃ ሠንጠረዡን በ51 ነጥብ ይመራል። ተሸናፊው አትሌቲኮ ማድሪድ 48 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ነው። ሪያል ማድሪድ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የሪያል ማድሪዱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ እና የባርሴሎናው ሉዊስ ሱዋሬዝ 19 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ቀዳሚ ደረጃ ይዘዋል። የሪያል ማድሪዱ ቤንዜማ በ18 ይከተላቸዋል። የባርሴሎናው ኔይማር በ16 ግቦች ሦስተኛ ነው።

የሜዳ ቴኒስ
በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ፍፃሜ ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች ትናንት የብሪታኒያው አንዲ ሙራይን ድል በመንሣት ዋንጫውን በድጋሚ በእጁ ማስገባት ችሏል። ኖቫክ አንዲን ሦስቴ በተከታታይ፤ በጥቅሉ 7 ለ3 ነው ያሸነፈው። ኖቫክ ጄኮቪች ለፍፃሜ በደረሰባቸው ስድስቱም የአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያዎች ሜልቦርን ከተማ ውስጥ አሸናፊ ለመሆን የበቃ ብርቱ ተወዳዳሪ ነው። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2011 ባከናወናቸው 43 ጨዋታዎች አንዴም ሳይሸነፍ በተከታታይ ድል በማድረግ ሦስቱንም የዓለም የሜዳ ቴኒስ ፍፃሜዎች በማሸነፍ የሠራው ታሪክ የብቃቱን ጥግ ያሳየበት ነው። 21 የፍፃሜ ግጥሚያዎችንም በተከታታይ በማሸነፍ ይታወቃል። ከአጠቃላይ 88 ጨዋታዎቹ 82ቱን በማሸነፍም ወደር ያልተገኘለት ተጨዋች መሆኑን አሳይቷል። ሮጀር ፌዴረርም ኾነ ራፋኤል ናዳል ሊደርሱበት አልቻሉም።

ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች
ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪችምስል picture-alliance/dpa/M. Nagi
ለሪያል ማድሪድ ሦስቱን ግቦች ያስቆጠረው የፖርቹጋሉ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ
ለሪያል ማድሪድ ሦስቱን ግቦች ያስቆጠረው የፖርቹጋሉ ክሪስቲያኖ ሮናልዶምስል picture-alliance/AP Photo/M. Meissner

ለ21 ጊዜያት የፍፃሜ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ዋንጫዎችን የሰበሰበችው አሜሪካዊቷ ሴሬና ዊሊያምስ በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ የሴቶች ግጥሚያ ቅዳሜ ዕለት ተሸንፋለች። የተሸነፈችውም በጀርመናዊቷ አንጄሊክ ኬርበር ነው። አንጄሊክ በሜልቦርኑ የአውስትራሊያ ፍፃሜ ስታሸንፍ የመጀመሪያዋ ነው። የ28 ዓመቷ ጀርመናዊት 6-4 3-6 6-4 በኾነ ድምር ውጤት ስታሸንፍ በ1999 የፈረንሣይ ፍፃሜ ላይ ባለድል ከነበረችው ሌላኛዋ ጀርመናዊት ወዲህ የመጀመሪያዋ ናት። የ34 ዓመቷ አሜሪካዊት ሴሬና ዊሊያምስ በ26 የፍፃሜ ግጥሚያዎች ስትሸነፍ የአሁኑ ለአምስተኛ ጊዜ መኾኑ ነው።

የእጅ ኳስ

የጀርመን የእጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን እሁድ የስፔን አቻውን በማሸነፍ የአውሮጳ ዋንጫ ባለቤት ለመሆን ችሏል። ከጎርጎሪዮሱ 2004 ወዲህ ቡድኑ በአውሮጳ ፍፃሜ ዋንጫውን በእጁ ሲያስገባ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከግብ ጠባቂው አንድሪያስ ቮልፍ ድንቅ ብቃት ጋር ተደምሮ የጀርመን ቡድን የስፔን ተፎካካሪውን የረታው 24:17 (10:6) በኾነ ውጤት ነው። የጀርመን ቡድን በዚህ ውጤት ሪዮ ብራዚል ውስጥ ለሚከናወነው የኦሎምፒክ ውድድር በቀጥታ ማለፉ ተረጋግጧል።

በፕሬሚየር ሊግ የተጨዋች ዝውውር ክፍያ የዘንድሮ የጨዋታ ዘመን በመዝጊያው ዕለት ክብር ወሰን የሚሰበርበት ነው ተብሏል። ባለፈው የጎርጎሪዮስ ዓመት የ2014-15 ዓመት የጨዋታ ዘመን ለዝውውር የወጣው £965 ሚሊዮን ፓውንድ ነበር። ዘንድሮ ለተጨዋች የሚወጣው የዝውውር ክፍያ 1 ቢሊዮን ፓውንድን እንደሚልቅ ተገምቷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ