1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ጥቅምት 17 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

ሰኞ፣ ጥቅምት 17 2012

በቶትንሀም ሲመራ የቆየው ሊቨርፑል በጨዋታ በልጦ በስተመጨረሻ አሸናፊነቱን አረጋግጧል። 2 የፍጹም ቅጣት ምቶችን የግብ ጠባቂ ሲሳይ ያደረገው ማንቸስተር ዩናይትድም ለድል በቅቷል። ማንቸስተር ሲቲና ቸልሲ ተጋጣሚዎቻቸውን በሰፋ ልዩነት ሲያሸንፉ፤ ላይስተር ሲቲ ሳውዝሐምተንን የግብ ጎተራ አድርጎታል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማራቶን ሩጫ አሸንፈዋል።

https://p.dw.com/p/3S6et
Deutschland Bundesliga Borussia Mönchengladbach gegen Eintracht Frankfurt | Marcus Thuram
ምስል AFP/I. Fassbender

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በቶትንሀም ሲመራ የቆየው ሊቨርፑል በጨዋታ በልጦ በስተመጨረሻ አሸናፊነቱን አረጋግጧል። ሁለት የፍጹም ቅጣት ምቶችን የግብ ጠባቂ ሲሳይ ያደረገው ማንቸስተር ዩናይትድም ለድል በቅቷል። ማንቸስተር ሲቲ እና ቸልሲ ተጋጣሚዎቻቸውን በሰፋ ልዩነት ሲያሸንፉ፤ ላይስተር ሲቲ ሳውዝሐምተን ላይ 9 ግብ በማስቆጠር የግብ ጎተራ አድርጎታል። አርሰናል ነጥብ ተጋርቷል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ መሪነቱን ሲያስጠብቅ፤ ባየር ሙይንሽን እና ፍራይቡርግም ተጨማሪ ሦስት ነጥብ አግኝተዋል። አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቮልፍስቡርግ እና ተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ግብ ማግባት ተስኗቸው ነጥብ ጥለዋል። በፎርሙላ 1 የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን ድል ቀንቶታል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ ማሳረጊያ በማራቶን ሩጫ አሸንፈዋል።

እግር ኳስ

የሊቨርፑሉ ሞሀመድ ሣላኅ እና ሳዲዮ ማኔ
የሊቨርፑሉ ሞሀመድ ሣላኅ እና ሳዲዮ ማኔምስል AFP/F. Walschaerts

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በስድስት ነጥብ ግስጋሴውን የቀጠለው መሪው ሊቨርፑል በዚህ ሳምንት ትኩረቱ ብራማዋ ዋንጫን ለማንሳት በሚደረገው የሊግ ካፕ ፍልሚያ ላይ ነው። ከነገ በስተያ በሚደረገው ውድድር ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ አርሰናልን ይገጥማል። የቁርጭምጭሚት ጉዳት የደረሰበት ሞሀመድ ሳላኅ በውድድሩ ላይሰለፍ ይችላል ተብሏል። ቪርጂል ቫን ጂክ፤ አሌክስ ኦክስሌይ ቼምብርሌይ፤ ናቢ ኪዬታ፣ ጆ ጎሜዝ፣ ጄምስ ሚልነር እና ሪያን ብሬውስተር ግን መጫወት ይችላሉ።  በእርግጥ ትናንት በፕሬሚየር ሊጉ በቶትንሀም ሆትስፐር 1 ለ0 ሲመሩ ቆይተውበስተመጨረሻ ቡድናቸው በጨዋታ ልቆ 2 ለ1 እንዲያሸንፍ ያስቻሉት የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ለወጣት ተጨዋቾቻቸው ረቡዕ ዕለት ዕድል ሊሰጡ ይችላሉ። ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ የትናንቱ ድል ተጨምሮ ፕሬሚየር ሊጉን በ28 ነጥብ እየመሩ ነው።

ተከታዩ ማንቸስተር ሲቲ ቅዳሜ ዕለት አስቶን ቪላን 3 ለ0 ድል ቢያደርግም ከሊቨርፑል በ6 ነጥብ ዝቅ ብሏል። በዚህ ጨዋታ ፈርናንዲንሆ 87ኛው ደቂቃ ላይ በፈጸመው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ትናንት ማንቸስተር ዩናይትድ ኖርዊች ሲቲን 3 ለ1 ድል አድርጓል። ማንቸስተር ዩናይትድ ሁለት ጊዜ ፍጹም ቅጣት ምት ቢያገኝም ሊጠቀምበት ግን አልቻለም። የኖርዊች ሲቲው ግብ ጠባቂ ቲም ክሩል የማርኩስ ራሽፎርድ እና የአንቶኒ ማርሲያል ፍጹም ቅጣት ምቶችን በብቃት ማዳን ቢችልም፤ ቡድኑ ኖርዊች ሲቲ ግን 3 ለ1 መሸነፍ አልቀረለትም። ማርኩስ ራሽፎርድ ፍጹም ቅጣት ምቱን ማግባት ባይችልም ብዙም ሳይቆይ ግን ሁለተኛውን ግብ ተረጋግቶ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። አንቶኒ ማርሲያል በበኩሉ 73ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥሯል። ማንቸስተር ዩናይትድ በ8 ወራት ውስጥ በፕሬሚየር ሊጉ ግጥሚያ ከሜዳው ውጪ ሲያሸንፍ የቅዳሜው ጨዋታ የመጀመሪያው ነው። በዚህም አሠልጣኙ ኦሌ ጉናር ሶልስካዬር እፎይታ ተሰምቷቸዋል። ዐርብ ዕለት ሳውዝሀምፕተንን 9 ለ0 ያደባየው ላይስተር ሲቲ 20 ነጥብ ይዞ በፕሬሚየ ርሊጉ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በማንቸስተር ሲቲ የሚበለጠውም በ2 ነጥብ ብቻ ነው። ከቸልሲ ጋር በግብ ክፍያ ብቻ ይለያያል። አርሰናል 16 ነጥብ ይዞ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የባየር ሙይንሽኑ ሊዮን ጎሬትስካ ግብ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቶ እንደተበሳጨ
የባየር ሙይንሽኑ ሊዮን ጎሬትስካ ግብ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቶ እንደተበሳጨምስል Imago Images/M. Weber

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ትናንት አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 4 ለ2 አሸንፎ የደረጃ ሰንጠረዡን በ19 ነጥብ ይመራል። ባየር ሙይንሽን በ18 ነጥብ ይከተላል። ፍራይቡርግ እና ቮልፍስቡርግ ተመሳሳይ 17 ነጥብ ይዘው በግብ ክፍያ ብቻ ይበላለጣሉ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከቮልፍስቡርግ በ1 ነጥብ ዝቅ ብሎ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።   ቮልፍስቡርግ ከአውስቡርግ ጋር ትናንት፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከሻልከ ጋር ከትናንት በስትያ ያለምንም ግብ ነው የተለያዩት። ቅዳሜ ዕለት ባየር ሙይንሽን በሜዳው ከዩኒየን ቤርሊንን ጋር ተጋጥሞ 2 ለ1 አሸንፏል።

ከጀርመን ቡንደስ ሊጋ ግን ሁለተኛ ዲቪዚዮን ላይ በነበሩት የሳምንቱ መጨረሺያ ግጥሚያዎች አስገራሚ ነገሮች ተከስተዋል።  አስገራሚ ነገሩ የጀመረው ዐርብ ዕለት ነበር። ሆልሽታይን ኪል በሰሜናዊ የወደብ ከተማዋ ኪይል ቦኹምን የገጠመ ጊዜ።በ37ኛው ደቂቃ ቦኹም 1 ለ0 እየተመራ ነበር። የቦኹም አጥቂ ምቦሲ ጋንቩላ በተልፈሰፈሰ ኹኔታ ኳሷን ወደግብ ይልካል።  እናም ኳሷ ከመስመር ውጪ ኾነች ብሎ ነበር ሁሉም ያሰበው። ኾኖም ዳኛው ፊሽካ ነፉ። ጨዋታው በቪዲዮ የሚተነትንበት (VAR)ጋር ሄዱ እና ተመለሱ። የቪዲዮ ደጋፊ ዳኛ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ተግባራዊ የኾነው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። እናም ዳኛው ቪዲዮውን ተመልክተው ከሜዳ ውጪ ለሚገኘው የሆልሽታይን ኪል ተቀያሪ ተጨዋች ሚሻኤል ኤበርቫይን ቢጫ ለቦኹም ደግሞ ፍጹም ቅጣት ምት ሰጡ። ተቀያሪው ተጨዋች ለካ ኳሷ ከመስመር ሳትወጣ ጫፍ ላይ ሳለች ለማቆም ሞክሯል። ቢተዋት በቀጥታ ወደ ውጭ ነበር የምትወጣው።  ከ2 ዓመት በፊት ተግባራዊ በኾነው ሕግ መሠረት ከሜዳ ውቺ ያለ ተጨዋች ሜዳ ውስጥ ያለች ኳስን ከነካ ቢጫ ካርድ እና ፍጹም ቅጣት ምት ይሰጣል። ሕጉ ተግባራዊ ከኾነበት ጊዜ አንስቶ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ቅጣት የተሰጠው በዐርቡ ግጥሚያ ነው። እንደ ዕድል ኾኖ ግን የ23 ዓመቱ ወጣት ተቀያሪ ቡድኑ በስተመጨረሻ 2 ለ1 አሸንፎለታል።

ጨዋታ በቪዲዮ የሚተነትንበት ሥልት (VAR) «የቪዲዮ ደጋፊ ዳኛ»
ጨዋታ በቪዲዮ የሚተነትንበት ሥልት (VAR) «የቪዲዮ ደጋፊ ዳኛ»ምስል Getty Images/AFP/N. Duarte

ሌላው አስደማሚ ክስተት ደግሞ ቅዳሜ ዕለት በዚሁ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ግጥሚያ ካርልስሩኸ እና ሐኖቨር ባደረጉት ግጥሚያ ላይ የታየው ነው። በ93ኛው ደቂቃ ላይ ሔንሪክ ቪጃንት ቡድኑን 3 ለ2 ያደረገችውን ግብ ያስቆጥራል። ከዳንኤል ጎርደን ጋር እየፈነጠዘም መሮጥ ይጀምራል። እጅግ የተበሳጨው የሐኖቨሩ ግብ ጠባቂ ሮን ሮበርት ኳሷን በቡጢ ለማጎን ብሎ ሲሰነዝር ግን ሳያስበው ዳንኤል ጎርዶንን ይመታውና ዳንኤል መሬት ላይ ይንፈራፈራል። ዳኛው ቀደም ሲል ጨዋታ በማዘግየት ያስቸገራቸውን ግብ ጠባቂ ቢጫ ሰጥተውት ነበር። አሁን በድጋሚ ቢጫ ከሜዳ ያሰናብቱታል። ግብ ጠባቂው በሐኖቨር ቆይታው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ከሜዳ ሲሰናበት። ባላሰበው ጥፋትም ሊያሸንፍ ጫፍ የደረሰው ቡድኑን ሦስት እኩል ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ አድርጎታል።

አትሌቲክስ

ትናንት እና በተከናወኑ የማራቶን እና የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች አሸናፊ ኾነዋል። ኢትዮጵያውያኑ ለድል የበቁት በጎዳና ላይ ውድድር የረዥም ጊዜ ታሪክ ባለው የጀርመን፣ ፍራንክፈርት ማራቶን እና በስፔን፣ ቫሌንሽያ ከተሞች በተደረጉ የሩጫ ውድድሮች ነው። በፍራንክፈርት የማራቶን ውድድር ከ110 ሃገራት የተውጣጡትን ጨምሮ 14.196 ሯጮች የተሳተፉ ሲኾን፤ ሁለት ሰዓት ከሰባት ደቂቃ ከስምንት ሰከንድ ሮጦ የገባው ኢትዮጵያዊው አትሌት በቀለ ተፈራ አንደኛ ወጥቷል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ሯጭ ዳዊት ወልዴ በሁለት ሰከንድ ብቻ ተበልጦ የሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። ለባህሬን የሚሮጠው ሌላኛው ትውልደ-ኢትዮጵያዊ ዐወቀ አያሌው ከአሸናፊው በአራት ሰከንድ ዘግይቶ ሦስተኛ ኾኗል።

በሴቶቹ የፍራንክፉርት የማራቶን ሩጫ ውድድር ኬንያዊቷ ቫላሪ አያባይ አሸናፊ ኾናለች። ሮጣ የገባችበት የ2 ሰዓት ከ19 ደቂቃ ከ10 ሰከንድ የፍራንክፉርት ማራቶን የቦታው ክብረወሰን ተሰኝቷል። ከቫለሪ በሁለት ደቂቃ ዘግይታ የገባችው መገርቱ ከበደ ሁለተኛ ስትወጣ፤ የአምናው የውድድሩ አሸናፊ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት መስከረም አሰፋ ሦስተኛ ሆናለች። መስከረም ውድድሩን ያጠናቀቀችው 2ሰአት፤ ከ22 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ በመሮጥ ነው። ጀርመናዊቷ ካታሪና ሽታይንሩክ ከቀዳሚዋ በ8 ደቂቃ ከ16 ሰከንድ ተበልጣ ዐሥረኛ ወጥታለች። የአይንኅራኅት ፍራንክፉርቷ ሯጭ በዚኽ ውጤቷ የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ መግቢያ ዝቅተኛ መስፈርትን አሟልታለች። ሮጣ የገባችው ከመስፈርቱ ከ2 ደቂቃ ከ4 ሰከንድ ያነሰ በመኾኑ የጀርመን መገናኛ ብዙኃን ስለ ሯጫ በስፋት ዘግበዋል።

የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማኅበር (IAAF)
የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማኅበር (IAAF)

የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማኅበር (IAAF)ምክር ቤት መጋቢት ወር ላይ ዶሃ ካታር ውስጥ ተሰብስቦ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት እ.ጎ.አ. በ2020 ጃፓን ቶኪዮ በሚደረገው የኦሎምፒክ የበጋ ውድድር በማራቶን ለመሳተፍ ሴት ተፎካካሪዎች በትንሹ 2 ሰአት፤ ከ29 ደቂቃ፤ ከ30 ሰከንድ ሮጠው ውድድራቸውን መጨረስ ይገባቸዋል። ወንዶች ደግሞ በጃፓን ማራቶን ለመሳተፍ ውጤታቸው 2 ሰአት፤ ከ11 ደቂቃ፤ ከ30 ሰከንድ እና ከዚያ በላይ መኾን ይኖርበታል ተብሎ ነው የተወሰነው።

ስፔን ቫሌንሽያ ከተማ በተከናወነው የግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ እና ዮሚፍ ቀጀልቻ ድል ተቀዳጅተዋል። የግማሽ ማራቶን ክብረ-ወሰንን ለመስበር አልማ የነበረችው ትውልደ-ኢትዮጵያዊቷ የሆላንድ ሯጭ አትሌት ሲፋን ሐሰን አልተሳካላትም። ክብረ-ወሰኑ በኬንያዊቷ አትሌት ጆይሲሊን ጄፕኮስጂ የተያዘ ሲኾን፤ 1 ሰአት ከ4ደቂቃ ከ51 ሰከንድ ነው። አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ ውድድሩን በአንደኛነት ስታጠናቅቅ የገባችው 1 ሰአት ከ5ደቂቃ ከ32 ሰከንድ በመሮጥ ነው። በዚህ ፍጥነቷም ሰንበሬ የኢትዮጵያ ክብረወሰንን በ13 ሰከንድ ማሻሻል ችላለች። በግማሽ ማራቶን የሴቶች የሩጫ ውድድር ታሪክ ደግሞ 12ኛው ፈጣኑ ተብሎላታል።

በስፔን ቫለንሺያ የተከናወነው የግማሽ ማራቶን የወንዶች ሩጫ ብርቱ ፉክክር የታየበት ነበር። በ59 ደቂቃ ከ05 ሰከንድ ውድድሩን የጨረሰው ዮሚፍ ቀጄልቻ አንደኛ ወጥቷል። በዶሃው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ያስገኘው ዮሚፍ ቀጀልቻ የትናንቱ ተጨማሪ ድል ኾኖለታል። ዮሚፍ የትናንቱ ውጤቱ የግሉ ምርጥ ተብሎ የተመዘገበለት ሲኾን፤ በዓለም የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች መዝገብ ላይም አራተኛ ደረጃ ላይ መስፈር ችሏል።  በሁለት ሰከንድ በመዘግየት ሁለተኛ የወጣው ኬንያዊ ቤናርድ ንጌኖ ሲኾን፤ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ጀማል ይመር ሦስተኛ በመሆን በውድድሩ ኢትዮጵያውያን የበላይነታቸውን እንዲያስመሰክሩ አስችሏል። ሌላኛው ኬንያዊ ሌዮናርዶ ባርሶቶን በአንድ  ሰከንድ ተበልጦ ለጥቂት አራተኛ ወጥቷል።

የፍራንክፉርት የማራቶን ሩጫ ውድድር በጀርመን፤ ፍራንክፉርት ከተማ
የፍራንክፉርት የማራቶን ሩጫ ውድድር በጀርመን፤ ፍራንክፉርት ከተማምስል AP

ከዚሁ ከሩጫ ውድድር ሳንወጣ፦ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የማጣሪያ ውድድር አካሂዷል። የማጣሪያ ውድድሩ የተከናወነው አዲስ አበባ ከተማ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ግቢ ውስጥ ጥቅምት 16 ቀን፣ 2012ዓ.ም ነው።  ከዚህ ቀደም በታላቁ ሩጫ ለመወዳደር አትሌቶች በእጣ ይመረጡ የነበረ ሲኾን፤ ዘንድሮ «አቅም ያላቸውን አትሌቶች በማጣሪያ ለመለየት በማሰብ ለግል የወንድ ተወዳዳሪዎች ብቻ» ውድድር መከናወኑ ተገልጧል።

በታላቁ ሩጫ ዓመታዊ የአዋቂ አትሌቶች ዓለም አቀፍ የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ውድድር ላይ የሚሳተፉ አትሌቶችን ለመለየት በማሰብ በተከናወነው የአምስት ኪ.ሜ የማጣሪያ ውድድር 50 ደረጃዎች ይዘው ያጠናቀቁ ወንድ አትሌቶች በ19ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ላይ ተሳታፊ ይኾናሉ። 100 ወንድ አትሌቶች በተፎካከሩበት የትናንቱ ውድድር፦ አትሌት ምትኩ አለሜ (15፡03.55)መሀመድ ዓለሙ(15፡07.74) እና ወንዳለ ከበደ(15፡13.26) በመሮጥ በቅደም ተከተል ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። የተዘጋጀላቸውን የማበረታቻ ሽልማት መቀበላቸውንም በኢሜል የደረሰን መልእክት ይገልጣል። የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በትናንቱ ማጣሪያ ካለፉት በተጨማሪ በክለባቸው ተመዘግበው ለመወዳደር የሚጠባበቁ 250 አትሌቶች ጋር በመሆን ኅዳር 07 ቀን 2012 ዓ.ም ይከናወናል።

የመኪና ሽቅድምድም

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የብሪታንያው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን ላይ የሚደርስ አልተገኘም
በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የብሪታንያው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን ላይ የሚደርስ አልተገኘምምስል Reuters/C. Jasso

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የብሪታንያው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን ትናንት በአንደኛነት አሸንፏል። በሜክሲኮው ሽቅድምድም ለድል የበቃው ሌዊስ ሐሚልተን በአጠቃላይ ውድድር ለስድስተኛ ጊዜ ዋንጫውን ለማንሳት ግን ዩናይትድ ስቴትስ አውስቲን ውስጥ የሚካሄደውን ቀጣዩን ውድድር መጠበቅ ይኖርበታል። የትናንቱ ድል ለሌዊስ ዘንድሮ ዐሥረኛው ሲኾን፤ በውድድር ዘመኑ ደግሞ 83ኛው ነው። ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ቫለሪ ቦታስ ሌዊስ ሐሚልተን በ74 ነጥብ ርቋል። ቫለሪ 289 ነጥብ ሰብስቧል። በሜክሲኮው ሽቅድምድም ሁለተኛ የወጣው የፌራሪ አሽከርካሪ ጀርመናዊው ሠባስቲያን ፌትል በ230 አጠቃላይ ነጥቡ ከሌላኛው የፌራሪ አሽከርካሪ ሻርል ሎክሌይር በ6 ነጥብ ተበልጦ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ