ስፖርት፤ ጥቅምት 20 ቀን፣ 2010 ዓ.ም.
ሰኞ፣ ጥቅምት 20 2010የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች የመጀመሪያ ማጣሪያውን እሁድ በሜዳው አዲስ አበባ ውስጥ ያከናውናል። የሲቲ ካፕ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ዘንድሮ በእጁ ያስገባው ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ቡድን 9 ተጨዋቾቹ ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ደርሶ መልስ ውድድር ተመርጠዋል። በፍራንክፉርት የማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው በመግባት ድል ተቀዳጅተዋል። በሴቶች ውድድር ኬንያዊቷን ተከትለው ኢትዮጵያውያቱ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን አግኝተዋል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የሜክሲኮ ግራንድ ፕሪ 9ኛ የወጣው ብሪታንያዊው ሌዊስ ሐሚልተን ዋንጫውን ለ4ኛ ጊዜ በእጁ አስገባ። ጀርመናዊው ሰባስቲያን ፌትል በሁለተኛነት አጠናቋል።
አትሌቲክስ
ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (IAAF) ትናንት ፍራንክፉርት ከተማ ውስጥ ባሰናዳው የማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው በመግባት አሸናፊ ኾነዋል። በውድድሩ አንደኛ የወጣው ሹራ ቂጣታ ቶላ ሲሆን ሩጫውን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀበት 2:05:50 ጊዜ ነው። ከልክሌ ገዛኸኝ ከአንድ ደቂቃ ከስድስት ሰከንድ በኋላ ሹራን ተከትሎ ሁለተኛ ወጥቷል። ጌጡ ፈለቀ በ2:07:46 የሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል።
በሴቶች የፍራንክፉርት የማራቶን ሩጫ ፉክክር ደግሞ፦ ኬንያዊቷ አትሌት ቪቪያን ቼሩዮት የአንደኛ ደረጃን አግኝታለች። በዚሁ ውድድር ኢትዮጵያውያቱ የብርጓል መለሰ እና መስከረም አሠፋ የሁለተኛነት እና ሦስተኛነት ደረጃን ይዘዋል። በኦሎምፒክ የ5000 ሜትር ሩጫ ባለድሏ ቪቪያን ያሸነፈችው በ2:23:35 ሮጣ በመጨረስ ነው። የብርጓል ሁለተኛ የወጣችው በቪቪያን ለጥቂት በ55 ሰከንዶች ብቻ ተበልጣ ነው። መስከረም እጅግ ጠባብ በሆነ ልዩነት በየብርጓል በ8 ሰከንድ ብቻ ተቀድማለች የፍራንክፉርት ማራቶን የሩጫ ውድድር ላይ ከ108 ሃገራት የተውጣጡ 14,513 ተፎካካሪዎች ተካፍለውበታል።
እግር ኳስ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2108 ሞሮኮ ውስጥ ለሚከናወነው የአፍሪቃ ዋንጫ ግጥሚያ ማጣሪያ ጨዋታ 9 ተጨዋቾችን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን መረጠ። በሱዳን ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ግጥሚያ ተሸንፎ ከማጣሪያው ተሰናብቶ የነበረው የኢትዮጵያ ቡድን በማጣሪያው ያልታሰበ ዕድሉን ያገኘው የግብጽ ቡድን ከውድድሩ መውጣቱን በማሳወቁ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፉት የቅርብ ጊዜያት ግጥሚያዎቹ በደርሶ መልስ ማሸነፍ የቻለው የጅቡቲ ቡድንን ብቻ ነው። በብሥራት 101.1 ኤፍ ኤም የትሪቡን ስፖርት ዋና አዘጋጅ ፍቅር ይልቃል በአጭር ጊዜ የተዋቀረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ግጥሚያውን እሁድ በሜዳው ማድረጉ ተጨማሪ ዕድል ነው ብሏል። አጋጣሚውንም «ያልታሰበ እድል ነው» ሲል ገልጦታል። «የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሱዳን በደርሶ መልስ ከተሸነፈ በኋላ የ2018 የቻን የሞሮኮ ተሳትፎው መደምደሙ ይታወስ ነበር» ሲልም አክሏል። ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመሳተፍ የተጠሩ አብዛኞቹ ተጨዋቾች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን መሆናቸውንም ጠቅሷል። «በቁጥር 9 የሚደርሱ ተጨዋቾች የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች ናቸው።» ተጨዋቾቹ ከአንድ ቡድን መሰባሰባቸው ለመናበብ ይኖር የነበረውን ችግር እንደሚቀርፍ የገለጠው ፍቅር «የመጀመሪያው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ መሆኑም በራሱ» ሌላ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ጠቊሟል።
ግብጽ ከውድሩ በመውጣቷ የተሰጠውን ዕድል በመጠቀም ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን የፊታችን እሁድ በሜዳዋ አከናውና በሳምንቱ ኅዳር 3 ሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ ውስጥ የመልሱን ጨዋታ ትጋጠማለች። ግብጽ ከውድድሩ ራሷን ያገለለችው የእግር ኳስ ቡድኖቿ የሀገር ውስጥ ተጨዋቾችን ለብሔራዊ ቡድኑ ግጥሚያ አንለቅም በማለታቸው ነው።
የመኪና ሽቅድምድም
በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ከሦስት ውድድሮች አስቀድሞ የሜክሲኮ ግራንድ ፕሬ ፉክክር ላይ የዋንጫ ባለቤት ይኾናል ተብሎ የተጠበቀው እንግሊዛዊው ሌዊስ ሐሚልተን 9ኛ ወጥቶ የዋንጫ ባለቤት ኾነ። ሌዊስ የዓመቱ ውድድር ሳይጠናቀቅ ባሰባሰበው ነጥብ ብልጫ ትናንት ለ4ኛ ጊዜ ዋንጫውን ማንሳት ችሏል። ሌዎስ ሐሚልተን በአጠቃላይ 333 ነጥብ ነው አሸናፊ የኾነው። ሰባስቲያን ፌትል በ56 ነጥቦች ተበልጦ 277 በማሰባሰብ በአጠቃላይ ድምር በ2ናነት አጠናቋል።
ቡጢ
የከባድ ሚዛን ቡጢ ፍልሚያ ባለድሉ ብሪታንያዊው አንቶኒ ጆሹዋ በሚቀጥለው ዓመት ከቀድሞው የከባድ ሚዛን ባለድል ታይሰን ፉሪ ጋር እንደሚጋጠም ፕሮሞተሩ ዛሬ አስታወቀ። አንቶኒ ጆሹዋ ከክሊችኮ የነጠቀውን ቀበቶ እሁድ ዕለት ባደረገው ግጥሚያ ማስጠበቅ ችሏል። አንቶኒ እሁድ 10ኛው ዙር ላይ በዳኛ ውሳኔ ያሸነፈው ካርሎስ ታካምን ነው። በውድድሩ ፍጻሜ ግራና ቀኝ ቅንድቦቹ በከባድ ቡጢ የተሰነጠቁት ካርሎስ ታካም ዳኛው ጨዋታውን ሲያቋርጡ ብስጭቱን ገልጧል። በእርግጥም በመቧቀሻ ስፍራ የነበሩት ሐኪም ጨዋታው እንዲቀጥል ፈቅደው ዳኛው ብዙም ሳይቆዩ ጨዋታውን ማቋረጣቸው በብዙዎች ዘንድ አስተችቷቸዋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ