ስፖርት፤ ጥቅምት 3 ቀን፣ 2012 ዓ.ም
ሰኞ፣ ጥቅምት 3 2012ትናንት ጀርመን ለአውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ኤስቶኒያን 3 ለ0 ያሸነፈችበት ግጥሚያ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አትርፎላታል። አጀማመሩ ላይ ውሉ የጠፋበት የሁለቱ ሃገራት ግጥሚያ ኤምሬ ቻን በሠራው ስህተት ገና በ14ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲሰናበት መልኩን ቀይሯል። የጀርመን ቡድን ወደ ቀልቡ ተመልሶ የጨዋታውን መልክ ለመቀየር የመጀመሪያው አጋማሽ እስኪጠናቀቅ ድረስ መጠበቅ ነበረበት።
ከእረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች ባዶ ለባዶ ኾኖም ጀርመን በአንድ ተጨዋች ተጓድሎ ወደ ሜዳ ቢገቡም ድሉ ግን የማታ ማታ የጀርመን ኾኗል። 51ኛው ደቂቃ ላይ የቱርክ ዝርያ ያለው ኤልካይ ጉንዶዋን የመታትን ኳስ ማርኮ ሮይስ ባጋጣሚ በተረከዝ ነክቶ ግብ ሆነች። ከዚያም ብዙም ሳይቆይ በ56ኛው ደቂቃ ላይ ኤልካይ ጉንዶዋን ድጋሚ የመታት ኳስ በኢስቶንያ ተከላካይ ተጋጭታ ገባች። በ70ኛው ደቂቃ ቲሞ ቬርነር የጀርመን አሸናፊነት ማረጋገጫ የኾነውን የመጨረሻውን ግብ አስቆጠረ። እናም በ10 ተጨዋች ለመጫወት የተገደደው ጀርመን በሰፋ ልዩነት አሸንፎ ሦስት ነጥብ ይዞ ወጥቷል።
የአውሮጳ ዋንጫ ማጣሪያ
በምድብ «ሐ» ጀርመን ከኔዘርላንድ ጋር ተመሳሳይ 15 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሰሜን አየርላንድ በ12 ነጥብ ሦስተኛ፤ እንዲሁም ቤላሩስ እና ኢስትላንድ በ4 እና አንድ ነጥባቸው አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃ ላይ ናቸው።
እንደ ሕጉ ከኾነ ከ55ቱ ተጋጣሚ ሃገራት ለአውሮጳ ዋንጫ ማጣሪያውን የሚያልፉት ከየምድቡ አንደኛ እና ሁለተኛ ያጠናቀቁት ናቸው። ኾኖም በአንድ ምድብ ውስጥ ከሁለት በላይ ቡድኖች ተመሳሳይ ነጥብ ካላቸው አላፊዎቹን ለመለየት የአውሮጳ ኅብረት እግር ኳስ ማኅበር(UEFA)ሕግ ተግባራዊ ይኾናል። በዚያም መሠረት፦ በሁለት ተጋጣሚዎች መካከል ያለው የነጥብ መበላለጥ፤ የግብ ክፍያ ልዩነት፤ ወደ ዒላማቸው የተላኩ በርካታ ኳሶች፤ እንዲሁም ወደ ግብ ተመትተው የተጨናገፉ ኳሶች ብዛት ይታያል። በዚያ መለያየት ካልቻሉ ደግሞ ተመሳሳይ መለኪያ በጠቅላላ ምድቡ ላይ ይታያል።
ካዛክስታንን 2 ለ0 ትናንት ያሸነፈችው ቤልጂየም ሐሙስ ዕለት ሣን ማሪኖን 9 ለ0 ጉድ ያደረገች ጊዜ ነው ለአውሮጳ ዋንጫ ማለፏን በማረጋገጥ የመጀመሪያ ሀገር የኾነችው። ኔዘርላንድ ሚንስክ ከተማ ውስጥ ቤላሩስን 2 ለ1 አሸንፋለች። ሁለቱንም ግቦች ያስቆጠረው የሊቨርፑሉ ጂኦርጂኒዮ ቪጅናልዱም ነው። 12 ነጥብ ይዛ በደረጃ ስንጠረዡ 3ኛ ላይ ከምትገኘው ሰሜን አየርላንድ ጋር ረቡዕ እለት ትጋጠማለች። ሦስት ቀን ቆይታ ደግሞ ከኤስቶኒያ ጋር ትጫወታለች።
ከቤልጂየም ቀጥሎ ጣሊያን እና ሩስያ ለአውሮጳ ዋንጫ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። የ2018 የዓለም ዋንጫ አዘጋጁዋ ሩስያ ሲፕረስን 5 ለ0 ነበር ያሸነፈችው።
ሌላው በሳምንቱ በስፖርት አፍቃሪዎች ዘንድ ጀርመን ውስጥ መነጋገሪያ የነበረው የሁለት ተጨዋቾች ጉዳይ ነበር። በትናንቱ ግጥሚያ ግብ ያስቆጠረውን ጨምሮ ሁለት የጀርመን ተጨዋቾች የቱርክ ጦርን የሚደግፍ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ፎቶ ላይ ድጋፋቸውን ገልጠዋል በሚል ውዝግብ አስነስቶ ነበር። ወዲያውኑ ግን ፌስቡክ ላይ ያኖሩትን ላይክ አጥፍተዋል። ቱርክ ሶሪያ ውስጥ የጀመረችው ወታደራዊ ጥቃት ጀርመን ውስጥ በልዩ ጥንቃቄ ነው የሚታየው።
የጀርመን ቡንድ እነ ሊዮኔል ሜሲ ሠርጂዮ አጉዌሮ እና አንጄል ዲ ማሪያን የመሳሰሉ ወሳን ተጨዋቾች ባልተሰለፉበት ጨዋታ ባለፈው ረቡዕ ከጀርመን ቡድን ጋር ሁለት እኩል አቻ ወጥተዋል። የዶርትሙንዱ ሲግናል ኢዱና ፓርክ ስታዲየም ውስጥ በታደመው ደጋፊ ፊት የተጋጠመው የጀርመን ቡድን ውጤት ለጀርመናውያን ብዙም አስደሳች አልነበረም።
ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር
ለጀርመን ቡድን ለ121 ጊዜ ተሰልፎ 24 ግቦችን አስቆጥሯል። ጀርመናውያን ሽቫይኒ ሲሉ ያቆላምጡታል። ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር። 5.1 ሚሊዮን ተከታዮች ባሉበት ይፋዊ የትዊተር ገጹ ላይ ማክሰኞ እለት ነው እግር ኳስ እንደሚያቆም ያስታወቀው። «አሁን ጊዜው መጥቷል፤ እናንተንም ቡድኖቼንም ሁለታችሁንም አመሠግናለሁ» ሲል ጽፏል ቡድኖቹንም ዘርዝሯል፦ ባየር ሙይንሽን፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ቺካጎ ፋይር በማለት። «እንዲሁም አናልቫኖቪች እና ቤተሰቦቼ ለድጋፋችሁ አመሰግናለሁ» ብሏል።
የአዲዳስ ቃል አቀባዩዋ አና አናልቫኖቪች የባስቲያን ባለቤት ናት። እሷም በበኩሉዋ 2.8 ሚሊዮን ተከታዮች ባሉበት ይፋዊ የትዊተር ገጹዋ ደስታዋን ገልጻለታለች። «ለድንቅ የእግርኳስ ዘመንህ እንኳን ደስ ያለህ ፍቅሬ» ስትል።
ባስቲያን ወደፊት በምን ሥራ ላይ እንደሚሰማራ ዐርብ እለት አጠር ባለው የጀርመንኛና የእንግሊዝኛ የትዊተር ጽሑፉ ዐስታውቋል፤ እንዲህ ሲል፦ «በአኤርዴ ስፖርት ሻው የቲቪ ተንታኝ አዲስ ሥራ በማግኘቴ እና አብረን ስለምንሠራም ደስ ብሎኛል» ሲል።
የጀርመንኛው (ARD) ምኅጻረቃል በፌዴራል ጀርመን የሚገኙ የሕዝብ መገናኛ አውታሮች የሥራ ማኅበር እንደ ማለት ነው። እንደነ አኦሊቨር ካን ያሉ ብዙ የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋቾች ኳስ ሲያቆሙ በዚህ ቲቪ ተንትኝ ኾነው ይቀርባሉ። ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት ጀርመን ለወዳጅነት ከአርጀንቲና ጋር 2እኩል በተለያየችበት ጨዋታ ዬርገን ክሊንስማን ተንታኝ ኾኖ ቀርቦ ነበር። ስለ ባስቲያን ሽቫይንሽታየገርም ተናግሯል በእለቱ።
ባስቲያን ሽቫይንሽታየገር እድገቱ ባየርን ግዛት ውስጥ በአልፐን ከፍታማ ቦታዎች ነው። ኳስ የጀመረው ገና የ3 ዓመት ልጅ ሳለ ነው። ለኦበራውዶርፍ፤ ከዚያም ለቲኤስቪ 1860 ሮዘንሃይም ተጫውቷል። የ14 ዓመት ልጅ ሳለ ወደ ባየር ሙይንሽን ወጣት ቡድን ተቀይሯል። ልክ የ18 ዓመት ታዳጊ ወጣት ሳለም ነው እ.ጎ.አ. በ2002 ዓ.ም ለዋናው የባየር ሙይንሽን ቡድን የፈረመው። ከዚያም ረዥም ዘመኑን ከዚሁ ቡድን ጋር አሳልፏል።
በሁለተኛ ዓመቱም በ2004 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ ተጫወተ። ከሀንጋሪ ጋር ለሙከራ የተደረገ በ2 ለ0 የተጠናቀቀ ጨዋታ ነበር። በ2006 የዓለም ዋንጫ ከፖርቹጋል ጋር በተደረገው የደረጃ ጨዋታ 2 ግቦችን አስቆጥሮ 3ኛውን አመቻችቷል። በዚህም ምርጥ ተጨዋች ተሰኝቷል። በአማካይ የሚጫወት ነበር። ከአርጀንቲና ጋር ጀርመን ተጫውታ 1 ለ0 ስታሸንፍ በደረሰበት ጉዳት ፊቱ በደም አበላ ተውጦም 120 ደቂቃ መጫወቱ አስደምሟል።
በ2014 ፊሊፕ ላምስ እግር ኳስ ሲያበቃ ሽቫይንሽታይገር የአምበልነት ስፍራውን አገኘ። በተደጋጋሚ ጉዳት ስለደረሰበት አምበልነቱን ብዙም አልሰራበትም። በ2016 ብዙም አመርቂ ጨዋታ አላደረገም። በዚያን ጊዜ ጀርመን በአውሮጳ ዋንጫ በፈረንሳይ ከግማሽ ፍስጻሜው ተሰናብቷል።
ከዓለም ዋንጫ በኋላ ባሉት ሁለት ዓመታት የእግር ኳስ ሕይወቱ እምብዛም ነበር። በ2016 ዝነኛ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቿ አና ኢቫኖቪችን ቬኒስ ውስጥ አገባ። በ2016 ከጀርመን ብሔራዊ ቡድን በ32 ዓመቱ የተሰናበተው ሞይንሽንግላድባኅ ውስጥ ጀርመን ፊንላንድን ካሸነፈች በኋላ ነበር። በ2017 ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አቅንቶ ለቺካጎ ፋይርስ ቡድን መጫወት ጀመረ። በ2018 ነሐሴ ወር ውስጥ በባየር ሙይንሽን የስንብት ጨዋታ አደረገ። ከባየር ሙይንሽን ጋር 18 ዋንጫ አሸንፏል። ቡድኑ ቺካጎ ፋየርስ ኦርላንዶ ሲቲን 5 ለ2 ባሸነፈበት ጨዋታ ነው የእግር ኳስ ሕይወቱ ለ17 ዓመት ዘልቆ ያከተመው።
አትሌቲክስ፦
የሳምንቱ መጨረሻ በተለይ ለኬንያውያን የማራቶን ሯጮች መቼም የማይረሳ ነበር ማለት ይቻላል። ኬንያዊቷ የማራቶን ሯጭ ቢርጊድ ኮስጄይ ሁለት ሰአት ከ14 ደቂቃ ከ04 ሰከንድ በመሮጥ አዲስ ክብረ-ወሰን ሰብራለች ትናንት በቺካጎ ማራቶን። ኢትዮጵያውያቱ እና ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በሴትም በወንድም ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል።
ከትናንቱ ውድድር ቀደም ብሎ ደግሞ ቅዳሜ ዕለት ሌላኛው ኬንያዊ የዓለማችን የማራቶን ክብር ወሰን ባለቤት ኤሊውድ ኪፕቾጌ በኦስትሪያ ልዩ የማራቶን ሩጫ ከ2 ሰአት በታች በመግባት አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል። ኪፕቾጌ የማራቶን ሩጫውን በ1 ሰአት ከ59 ደቂቃ ከ40,2 ሰከንድ ነው ያጠናቀቀው። የ34 ዓመቱ ኬንያዊ አትሌት ታሪክ በመሥራቱም የኬንያ መዲና የናይሮቢ ጎዳናዎች በደስታ በፈነጠዙ ደጋፊዎች ተዘጋግተው ነበር። ኤሊውድ ኪፕቾጌ አይደረግም የተባለውን አድርጎ በመገኘቱ ቀጣዩን መልዕክት አስተላልፏል። «ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር የተገደበ እንዳልኾነ ለሰዎች መንገር እሻለሁ። ከዛሬ ጀምሮ በዓለም ዙሪያ ብዙ ሰዎች ከሁለት ሰአት በታች ይሮጣሉ ብዬ እጠብቃለሁ» ሲል።
ኤሊውድ ኪፕቾጌ ቅዳሜ እለት በኦስትሪያ መዲና ቪዬና 42,195 ኪሎ ሜትሩን ከሁለት ሰአት በታች በመሮጥ ደማቅ ታሪክ ጽፏል። ዘንድሮ ከአንድ ወር በኋላ ፈረንሣይ ሞናኮ ከተማ ውስጥ ይፋ በሚደረገው የዓመቱ ምርጥ የዓለም አትሌት እጩ ውስጥም ተካቷል።
የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማኅበር (IAAF) ዛሬ ይፋ ባደረገው መግለጫው 11 የዓለማችን ምርጥ አትሌቶችን በእጩነት ማቅረቡን በደስታ ገልጧል። በእጩነት ከቀረቡት ምርጥ አትሌቶች መካከል አምስቱ የዩናይትድ ስቴትስ አትሌቶች ናቸው። ከአፍሪቃ የሁለት ሃገራት ሦስት እጩዎች ቀርበዋል። ከእነዚህም መካከል ኡጋንዳ በአትሌት ጆሹዋ ቼፕቴጊ በኩል ስሟ ተነስቷል። ሁለት አትሌቶች ለእጩነት የቀረቡላት ሌላኛዋ አፍሪቃዊት ሀገር ጎረቤት ኬንያ ናት። እጩዎቹም፦ ከ11 የቤት ውጪ ውድድሮች መካከል ዐሥሩን ማሸነፍ የቻለው ብርቱው አትሌት ቲሞቲ ቼሩዪዎት እና በኦስትሪያ ቪዬና ቅዳሜ ዕለት ማራቶንን ከ2 ሰአት በታች መሮጥ እንደሚቻል ያስመሰከረው ኤሊውድ ኪፕቾጌ ናቸው።
ከእጩዎቹ የዘንድሮ ምርጥ አትሌት የሚለየው በሦስት አይነት መንገድ ድምፅ ከተሰጠ በኋላ ነው። የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማኅበር ምክር ቤት እና የማኅበሩ ቤተሰቦች በኢሜል ድምፅ እንዲሰጡ ይደረጋል። ከዚያ ደግሞ ደጋፊዎች በዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማኅበር ድረ-ገጽ በኩል ድምፅ ይሰጡና አሸናፊው ይለያል። ምናልባት አይቻልም የተባለውን ሰብሮ እንደሚቻል ያሳየው ኬንያዊው አትሌት ኤሊውድ ኪፕቾጌ የዓለማችን ምርጥ አትሌት ተሰኝቶ አፍሪቃን ያኮራ ይኾን? አብረን የምናየው ይኾናል።
የመኪና ሽቅድምድም
ጃፓን ውስጥ በተከናወነው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ቫልተሪ ቦታስ በሱዙካ መርሴዲስ ተሽከርካሪው አሸናፊ ኾኗል። ሌዊስ ሐሚልተን በአሁኑ ውድድርም ድል አልቀናውም። ሰባስቲያን ፌትልን ተከትሎ የሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል። እስካሁን በተከናወኑ አጠቃላይ ውድድሮች የመርሴዲስ ቡድን መሪ ነው። ሌዊስ ሐሚልተን 338 ነጥብ ሰብስቦ ውድድሩን ሲመራ፤ ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ቫልተሪ ቦታስ 274 ነጥብ ይዞ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የፌራሪው ሻርል ሎክሌይር በ221 ነጥብ ደረጃው ሦስተኛ ነው። የፌራሪው አሽከርካሪ ጀርመናዊው ሠባስቲያን ፌትል ከሬድ ቡል ሆንዳ አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፓን ጋር ተመሳሳይ 212 ነጥብ ይዞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ