ስፖርት፤ የካቲት 9 ቀን፣ 2012 ዓ.ም
ሰኞ፣ የካቲት 9 2012የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ላትሲዮ የሴሪኣውን ዋንጫ ቢያነሳ ምኞታቸው እንደኾነ ተናግረዋል። እንደ ሴሪኣው ኹሉ በስፔን ላሊጋም መሪው ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና በአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ ተፋጠዋል። የአፍሪቃ ዋንጫ ቡድኖች ድልድል ከሰአታት በኋላ ይፋ ይኾናል። ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት የሚደረገው የሻምፒዮንስ ሊግ የዙር ፍልሚያ ነገ ይጀምራል።
አትሌቲክስ
ትናንት በተከናወነው የባርሴሎና የግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አሸቴ በከሪ በአንደኛነት አጠናቃ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች። አሸቴ 1:06:37 በመሮጥ ለድል ስትበቃ፤ ሌላኛዋ የሀገሯ ልጅ አስናቀች ዐወቀ በ27 ሰከንዶች ብቻ ተቀድማ በመግባት የብር ሜዳሊያ አጥልቃለች። የሦስተኛ ደረጃውን ኬኒያዊቷ ዶርካስ ኪሜሊ በመያዝ የነሐስ ሜዳሊያ ወስዳለች። የአራተኛም ደረጃ በኢትዮጵያዊቷ ሮዛ ደረጀ ነው የተያዘው። የኬንያ እና የዩጋንዳ ተፎካካሪዎች ለድል በበቁበት በወንዶች ተመሳሳይ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ተስፋሁን አካልነው የኤርትራውን ሯጭ አብራር ዖስማን ተከትሎ አምስተኛ ደረጃ ይዟል።
ፈረንሳይ ሞናኮ ውስጥ በተደረገ ሌላ የአምስት ሺህ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ፉክክር ደግሞ ዩጋንዳዊው አትሌት ጆሱዋ ቼፕቴጌ 12 ደቂቃ ከ51 ሰከንድ በመሮጥ የርቀቱን የዓለም ክብር ወሰን መስበር ችሏል። እስከ ትናንት ድረስ ርቀቱን ከ13 ደቂቃ በታች ማሸነፍ የቻለ አትሌት አልነበረም። ቀደም ሲል የ13 ደቂቃ ከ18 ሰከንዱ ክብሯ ወሰን ተይዞ የቆየው በበኬኒያዊው አትሌት ሮኔክስ ኪፕሩቶ ሲኾን፤ ውድድሩም ቫለንሺያ ከተማ ውስጥ ባለፈው ወር ነበር የተኪያሄደው።
በአምስት ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ግን አኹንም ድረስ የዓለም ክብረ-ወሰኑ በአትሌት ቀነኒሳ በቀለ እንደተያዘ ነው። ቀነኒሳ 12:37.35 በመሮጥ የያዘው የዓለም ክብረ-ወሰን ግን አኹንም አልተደፈረም። አትሌት ጆሱዋ ቼፕቴጌ በሪዮ 2016 ኦሎምፒክ በአምስት እና ዐስር ሺህ ሜትሮች ተፎካካሪ የነበረ ሲኾን፤ ስምንተኛ እና ስድስተኛ ነበር ያጠናቀቀው። አትሌቱ ወደፊት በሚያደርጋቸው ውድድሮች አስደማሚ ውጤት ማስመዝገብ የመቻል አቅም ያለው ነው።
እግር ኳስ
ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ በጣሊያን ሴሪ ኣ ዘንድሮ ማን አሸንፎ ዋንጫ እንደሚያነሳ ተጠይቀው፦ «ላትሲዮ የዋንጫው አሸናፊ ቢኾን ደስተኛ ነኝ» ብለዋል። ለዚያ ደግሞ ምክንያታቸውን ሲገልጡ የቀድሞ የሊቨርፑል ተጨዋች ሉካስ ሌይቫ ላትሲዮ ውስጥ ስለሚጫወት ነው ሲሉ አክለዋል። «ለአሰልጣኝ ማውሪትሲዮ እና አንቶኒዮ ኮንቴ አዝናለሁ፤ ግን ላትሲዮ እጅግ ማስደመሙ የማይቀር ይመስለኛል» ያሉት ዬርገን ክሎፕ፦ «ላትሲዮ በዚህ የጨዋታ ዘመን ድንቅ ኾኗል» ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጠዋል። በጣሊያኑ ሴሪ ኣ ትናንት ኢንተር ሚላንን 2 ለ1 ያስደመመው ላትሲዮ ከመሪው ጁቬንቱስ የሚበለጠው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው። 56 ነጥብ የሰበሰበው ላትሲዮ ትናንት ድል ያደረገው ኢንተር ሚላንን በ2 ነጥብ ይበልጣል። ላትሲዮ ያለፉትን ኹለት የሊግ ዋንጫዎች ያሸነፈው ከኹለት ዐስርተዓመት በፊት ቢኾንም አሁን ጁቬንቱስንም ኾነ ኢንተር ሚላንን ድል በማድረግ በቡድኑ ታሪክ ለ19ኛ ጊዜ ምንም ሳይሸነፍ መገስገስ ችሏል።
እንደ ላትሲዮ ኹሉ የዬርገን ክሎፕ ሊቨርፑልም ዘንድሮ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ከአንድ ጨዋታ ውጪ ኹሉንም በማሸነፍ ለሦስት ዐሥርተ ዓመት ቡድኑ ያጣውን ዋንጫ ከእጅ ለማስገባት ጫፍ ደርሷል። ዘንድሮ እስካሁን በተደረጉ የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሊቨርፑል በአንዱ ብቻ አቻ በመውጣት እስካሁን ከአጠቃላዩ 78 ነጥብ 76 በመሰብሰብ ብርታቱን አሳይቷል።
ከኹለት ሳምንት በኋላ ከቀላል ጉዳት የተመለሰው ሳዲዮ ማኔ ቅዳሜ ዕለት ተቀይሮ ገብቶ በ78ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ብቸኛ ግብ ሊቨርፑልን ከኖርዊች ሲቲ ጋር ነጥብ ከመጋራት አድኖታል። ሊቨርፑሎች አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ሲቲን በ25 ነጥብ ርቀው ይገኛሉ። የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ስለ ነጥብ ርቀቱ ሲናገሩ፦ «ልዩነቱ ትንግርታዊ ነው። ያ ምንም ሊገባኝ አልቻለም» ብለዋል። «ከዚህ ቀደም እንደዚህ አጋጥሞኝ አያውቅም። እጅግ አስደማሚ፤ እጅግ አስቸጋሪ ነው» በማለትም የፕሬሚየር ሊግ ግስጋሴያቸው ለሳቸውም ሳያስደንቃቸው እንዳልቀረ ሳይሸሽጉ አልቀሩም። ሊቨርፑል እስካሁን ካደረጋቸው ያለፉት 11 ጨዋታዎች ግብ የተቆጠረበት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በዚህ አያያዙ ሊቨርፑል የፕሬሚየር ሊጉን በ102 አለያም በ105 ነጥብ ሊያጠናቅቅ ይችላል። ባለፈው የጨዋታ ዘመን ሊቨርፑልን በ1 ነጥብ ብቻ በልጦ ዋንጫውን ያነሳው ማንቸስተር ሲቲ 38 የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ያጠናቀቀበት ነጥብ 98 ነበር።
በፕሬሚየር ሊጉ ዛሬ ማታ ቸልሲ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ይጋጠማል። 41 ነጥብ ያለው ቸልሲ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲገን በዚሁ ከቀጠለ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ለሻምፒዮንስ ሊግ ማለፉን ያረጋግጣል። ተፎካካሪው ማንቸስተር ዩናይትድ ከመሪው ሊቨርፑል በ41 ነጥብ ርቀት 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። እንዲያም ኾኖ ግን አሰልጣኝ ኦሌ ጉናር ቡድናቸው ያለሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር እንኳን የዓለም ምርጥ ተጨዋቾችን መሳብ ይችላል ሲሉ ተናግረዋል። ማንቸስተር ዩናይትዶች በጀርመን ቡንደስሊጋ የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ምርጥ ጃዶን ሳንቾ፤ የላይስተር ሲቲው ጄምስ ማዲሰን እና የአስቶን ቪላው ኮከብ ጃክ ግሪሊሽን ለማስመጣት ላይ ታች እያሉ ነው።
በእርግጥ በፕሬሚየር ሊግ ፉክክር ለሻምፒዮንስ ሊግ ተፎካካሪ ኾኖ ማጠናቀቅ ተጨዋቾቹን እጅግ ሊስብ ቢችልም አሰልጣኙ ግን እንዲያም ኾኖ ቡድናቸው ምርጥ ተጨዋቾች ዐይናቸው የሚያርፍበት ነው ብለዋል። ዛሬ በስታምፎርድ ብሪጅ ከቸልሲ ጋር የሚደረገው ፍልሚያም ለማንቸስተር ዩናይድት በልዩ ኹኔታ የሚታይ ነው። በሜዳው የሚጫወተው ቸልሲም ለቀጣይ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ተፎካካሪ ለመኾን የዛሬው ጨዋታ ወሳኝ በመኾኑ ከባድ ፍልሚያ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
በሌላ ዜና በፕሬሚየር ሊጉ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 51 ነጥብ ይዞ በኹለተኛ ደረጃ የሚከተለው የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ምንም እንኳን ቡድናቸው ከአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የኹለት ጨዋታዎች ዘመን ቢታገድም በማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝነታቸው እንደሚቀጥሉ እየተነገረ ነው።
አርሰናል ኒውካስልን ትናንት በሰፋ ልዩነት 4 ለ0 ድል አድርጓል። ደረጃው ግን 34 ነጥብ ይዞ 10ኛ ነው። አስቶን ቪላ በቶትንሀም ትናንት 3 ለ2 ተሸንፏል።
በጀርመን ቡንደስሊጋ 46 ነጥብ ይዞ የሚመራው ባየር ሙይንሽን ትናንት ኮሎኝን 4 ለ1 አሸንፏል። በትናንቱ ጨዋታ ገና ከመነሻው አይሎ የታየው ባየር ሙይንሽን ጨዋታ በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃ ነበር በሮበርት ሌቫንዶቭስኪ የመጀመሪያዋን ግብ ያስቀጠረው። አፍታም ሳይቆይ በ5ኛው ደቂቃ ላይ ኪንግስሌይ ኮማን ኹለኛዋን ግብ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ሠርጌ ግናብሬ ደግሞ በ12ኛው ደቂቃ ላይ ሦስተኛዋን አስቆጥሮ የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ተጠናቀቀ። ለባየር ሙይንሽኑ ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር ግን ቡድኑ 3 ለ 0 ረፍት መውጣቱ በቂ አልነበረም።
ማኑዌል ኖየር፦ «ጅማሬው እጅግ በጣም ምርጥ ነው። አጀማመራችን በጣም አስደማሚ ነበር፤ ከመረብ ያረፉ ኳሶች ቁጥርም ድንቅ የሚባል ነው። በጨዋታው መሀል ግን ትንሽ ቀዝቀዝ ብለን ነበር ማለት ይቻላል። ሲመስለኝ በአጠቃላይ ዐሥር ኳሶችን ከመረብ ማሳረፍ እንችል ነበር። እግር ኳስ ውስጥ የተመታ ኳስ ኹሉ ከመረብ ያርፋል ማለት እንዳልነ ግልጽ ነው። ግን ደግሞ አንዳንዶቹ መሳት የሌለባቸውም ነበሩ። እናም በመጀመሪያው አጋማሽ እንዲያ እጅግ ጫና ፈጥረን እንደተጫወትነውን ያኽል በዚያው መዝለቅ ባለመቻላችን ራሳችን ን መውቀስ ይኖርብናል።»
ከረፍት መልስ ለቡድኑ አራተኛዋን ለራሱ ደግሞ ኹለተኛዋን ግብ በ66ኛው ደቂቃ ላይ ሰርጌ ግናብሬ አስቆጥሯል። በዕለቱ ተፎካካሪው ኮሎኝ 6 ጊዜ ወደ ግብ ሙከራ በማድረግ አንዱ ተሳክቶለት በዜሮ ከመውጣት ተርፏል። ለኮሎኝ 70ኛ ደቂቃ ላይ ግብ ያስቆጠረው ማርክ ዑት ነው። የኮሎኝ አሰልጣኝ ማርኩስ ጊስዶል የትናeንቱ ሽንፈታቸውን በጸጋ ተቀብለው ቀጣዩን ብለዋል።
«በጀመሪያው አጋማሽ በአጠቃላይ ግራ ተጋብተን ተቸግረን ነበር ማለት ይቻላል። ባየርኖች ከመነሻው አንስቶ ምርጥ ነበሩ። በመጀመሪያው አጋማሽ ምንም ማድረግ አልቻልንም። ልይነቱ ትልቅ ነበር። በእያንዳንዱ ቦታ ላይም በደንብ ጫና አልፈጠርንም። በዚያ ላይ ባየርኖች በአኹኑ ወቅት የሚገኙበት ጥሩ አቋም አንዳች ነገር ሲያገኙ የሚከሰተው እጅግ ሊፈጥን ይችላል።»
የባየር ሙይንሽኑ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ 23 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ በቡንደስሊጋው መሪ ነው። የላይፕሲሹ ቲሞ ቬርነር በ20 ግቦች ይከተለዋል። የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ጃዶን ሳንቾ 13 ግብ በማስቆጠር 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት ሻልከ ከማይንትስ ጋር ያደረገው ግጥሚያ ያለግብ ተጠናቋል።
በፖርቹጋል ፕሪሚየራ ሊጋ የፖርቶው አጥቂ የዘረኝነት ሰለባ ከመኾኑም ባሻገር ቢጫ ካርድ ማየቱ አነጋጋሪ ኾኗል። ማሊያዊው አጥቂ ሞሳ ማሬጋ ፖርቶ ጉዊማሬስን 2 ለ1 ባሸነፈበት ግጥሚያ የማሸነፊያዋን ግብ ሲያስቆጥር ተመልካቾች እንደጦጣ በመጮኽ የዘረኝነት ስድብ ሰድበውታል። ግቡን ባስቆጠረበት ወቅት መቀመጫ ፕላስቲክ አንስቶ ጭንቅላቱ ላይ በማድረግ የቆዳ ቀለሙን እያሳየ ንዴቱን ገልጧል። በዚያም ቢጫ ካርድ አይቷል። ኹኔታው እጅግ ያበሳጨው አጥቂ በንዴት ከሜዳ ለመውጣት ሲልም በቡድኑ እና በተቃራኒው ቡድን ተጨዋቾች እንዳይወጣ ሲወተወት ነበር። ከደቂቃዎች ንትርክ በኋላ ተቀይሮ ወደ መልበሻ ክፍል ሲያመራ ኹለት አውራ ጣቶቹን ወደ መሬት በመዘቅዘቅ ተሳዳቢዎችን ለማናደድ ጥሯል።
በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ውድድር ቀጥሎ ትናንት አራት ጨዋታዎች በተለያዩ ከተሞች ተከናውነዋል። ከትናንት በስትያ አንድ ጨዋታ የተደረገ ሲኾን መቀሌ እንደርታ ተጋጣሚው ሀዋሳ ከነማን 5 ለ1 በኾነ ሰፊ ልዩነት አሸንፏል። በመወዳደሪያ ስታዲየሙ ውስጥ «ስፖርት ለሰላም» የሚል ጽሑፍ በደጋፊዎች ተሰርቶ ታይቷል። በትናንት ጨዋታዎች በብዙዎች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የፋሲል ከነማ ግጥሚያ 2 እኩል ተጠናቋል። ሀዲያ ሆሳዕና እና ስሑል ሽረም ያለምንም ግብ ነው የተለያዩት። በሌሎች ጨዋታዎች፦ ጅማ አባጅፋር ድሬዳዋ ከተማን 2 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አዳማ ከተማን ገጥሞ 2 ለ0 ተሸንፏል። ወላይታ ድቻ ባሕር ዳርን 1 ለ0 አሸንፏል።
በሻምፒዮንስ ሊግወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ በሚደረገው ግጥሚያ ነገ ማታ ሊቨርፑል ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ይጋጠማl። የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድም የፈረንሳዩ ፓሬስ ሰንጄርሜንን የሚገጥመው ነገ በተመሳሳይ ሰአት ነው። ሌላኛው የጀርመን ቡድን ላይፕሲሽ ቶትንሀምን እንዲሁም ቫሌንሺያ አታላንታን ረቡዕ ይገጥማሉ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ