1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቀዝቃዛው የአየር ጠባይ ያበረታው ኢንፍሉዌንዛ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 11 2015

ባለፉት ሦስት ዓመታት በክረምቱ የቅዝቃዜ ወቅት በምድረ ጀርመን የከረመው የኮሮና ተሃዋሲ ማገርሸት ብዙዎችን ሲያዳርስ እንዳልከረመ በዘንድሮው ክረምት ደግሞ በኢንፍሉዌንዛ ብዙዎች ተይዘዋል። ሀኪም ቤቶችም የታማሚዎች ብዛት የማስተናገድ አቅማቸውን እየተፈታተነው መሆኑን እየገለጹ ነው።

https://p.dw.com/p/4LCIU
Symbolbild I Grippe
ምስል blackday/Zoonar/picture alliance

ጤና እና አካባቢ

 

የኮሮና ተሃዋሲ መዛመት ጋብ አለ በተባለበት በዚህ ወቅት የጉንፋን ታማሚዎች ጀርመን ውስጥ ተበራክተዋል። ተማሪዎች ከትምህት ቤት ሠራተኞችም ከሥራ ቦታቸው ለመቅረት ተገድደዋል። ልጆች ላይ ህመሙ መጽናቱን ተከትሎም የሕጻናት መድኃኒት እጥረት ማጋጠሙም ተሰምቷል። ሀኪም ቤቶችም የታማሚዎች ብዛት የማስተናገድ አቅማቸውን እየተፈታተነ ነው። ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ ነበር የበርሊኑ ቻሪቴ ሆስፒታል በርካታ ሀኪሞች በመታመማቸው ምክንያት እጅግ አስፈላጊና እና አስቸኳይ ካልሆነ በቀር የቀዶ ህክምና ለመጪዎቹ ሦስት ሳምንታት አላደርግም ሲል በይፋ ያሳወቀው። የጀርመን የጽኑ ህሙማን እና የድንገተኛ ህክምና ማኅበረሰብ ፕሬዝደንት ክርስቲያን ክራጋንዲስም እንዲሁ በመላው ጀርመን የታማሚው ቁጥር በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ መጨመሩን ተናግረዋል። እሳቸው እንደሚሉትም በአብዛኞቹ የጀርመን ፌደራል ግዛቶች የሚገኙ የጽኑ ህሙማን ክፍሎች ሞልተዋል። ለዚህ ደግሞ ባለፉት ጊዜያት እንደታየው ዋነኛው ምክንያት የኮሮና ተሃዋሲ ብቻ አይደለም። ቀዳሚው ጉንፋን፤ RS የተሰኘው ተሐዋሲ እንዲሁም ሌሎች የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቁ ህመሞች መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል። በጀርመን ሙኒክ ከተማ የግል ክኒሊክ ያላቸው አጠቃላይ እና የውስጥ ደዌ ሀኪም ዶክተር ሊበን በሽርም በየዕለቱ የሚያስተውሉትን መነሻ በማድረግ ይኽንኑ ነው የሚያጠናክሩት።  «ያው ማስክ ተጠቅመን ስለቆየንና አሁን በአብዛኛው ማስክ ስናወልቅ፣ እና ከቅዝቃዜው እና ከክረምቱ መምጣት ጋር ኮሮና ብቻ ሳይሆን ብዙ አይነት ቫይረስ ነው አሁን ያለው።» ይላሉ ዶክተር ሊበን።

Winterwetter in Bonn
በቀዝቃዛው ክረምት የማትሞቀው ፀሐይ ምስል Marc John/IMAGO

የዶክተር ሊበን በሽር የግል ክሊኒክ በሚገኝበት የጀርመን ፌደራል ግዛት ባየርን ውስጥ የታማሚውን ቁጥር እና የህመሙን አይነት ለማወቅ የናሙና ጥናትም እየተደረገ ነው።

እነዚህ የመተንፈሻ አካላትን የሚያውኩ ህመሞች የሚያስከትሉት የህመም ምልክት በአንድ ወቅት የብዙዎች ህይወት ከቀጠፈው የኮሮና ተሐዋሲ የሚለይበት ነገር ቢኖርም በጥቅሉ ሲታይ ተመሳሳይ መሆኑን ነው የህክምና ባለሙያው የሚናገሩት። በእሳቸው ክልኒክም በሳምንት አንድ ቀን በሚያደርጉት የናሙና ጥናት በየጊዜ አንድ በኢንፉሌንዛ፣ አንድ RS ተሃዋሲ፣ እንዲሁም በኮሮና የተያዙ ታማሚዎችን እንደሚያገኙም ጠቁመዋል። 

በዚህ ጉንፋን ለሁለተኛ ጊዜ መያዛቸውን ነው የገለጹልን እዚህ ጀርመን ኤንግልስ ኬርሸ በተሰኘች አነስተኛ ከተማ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል የሚሠሩት የውስጥ ደዌ ሀኪም ዶክተር ሰብለወንጌል ይመኔ፤ ስለህመም ስሜቱ ሲገልጹ፤ «የእራስ ምታት፣ትኩሳት፣ የመገጣጠሚያ አካልት ህመም እንዲሁም ሳል አንዳለው» ተናግረዋል።

Berlin | Grippe | Impfung
የኢንፍሉዌንዛ ክትባት በየዓመቱ ጀርመን ውስጥ ጉንፋን ለሚያጠቃቸው መስጠት የተለመደ ነውምስል Omer Messinger/ZUMA Wire/imago images

ከሁለት ዓመታት በላይ በኮሮና ተሃዋሲ ስርጭት ሲሳቀቅ የከረመው የጀርመን ማኅበረሰብ ካለፉት ሳምንታት ወዲህ ደግሞ ከጉንፋን እና ኢንፍሉዌንዛ ጋር እየታገለ ነው። በርካቶችም ከሥራም ሆነ ትምህርት ቤት ለመቅረት ተገድደዋል። «እኔ እስከማውቀው  ቢያንስ እኔ በምሠራበት ሀኪም ቤት ከሥራ ብልደረቦቼ ለሁለተኛ ሳምንት ታምመው እቤታቸው የቀሩ አሉ።» ነው ያሉት ዶክተር ሰብለወንጌል።

ጀርመን ውስጥ በዚህ የክረምትና ቅዝቃዜ ወቅት የጉንፋን ህመም ልጆች ላይ ሳይቀር ተጠናክሮ ለመታየቱ የሚሰጡ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ዶክተር ሊበን፤ «የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መቅረቱ አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ እንዲያም ሆኖ ኢንፍሉዌንዛ በየዓመቱ የሚመጣ በሽታ ነው።» ብለዋል።

Atemwegserkrankung
የመተንፈሻ አካላትን ነጻ ለማድረግ መታጠንምስል imago images

አሁን ጀርመን ውስጥ ብዙዎችን የያዘው RS ተሃዋሲን ጨምሮ ኢንፍሉዌንዛ ነው ቢባልም የጉንፋን አይነቱ ከአንድ መቶ በላይ መሆኑንም አብራርተዋል። የህክምና ባለሙያዎቹ በዚህ አጋጣሚም ታማሚዎች ብዙ ፈሳሽ መጠጣት እንዲሁም እረፍት ማድረግ እንደሚጠቅማቸው መክረዋል። ሳል ያለባቸው ደግሞ ለዚሁ ሲባል የሚዘጋጁ የሳል ማስታገሻዎችን ቢወስዱ እንደሚረዳቸውም ጠቁመዋል። ላለፉት ዓመታት ለኮሮና ተዋሃሲ መከላከያ ሲባል በሚደረገው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ምክንያት በዚህ ወቅት የጉንፋን እና ኢንፍሉዌንዛ ታማሚዎች ቁጥር እጅግ መቀነሱ ሲነገር ነበር። ዘንድሮ በኮሮና ተሃዋሲ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነሱን ተከትሎ ከህዝብ መጓጓዣዎች እና ከሀኪም ቤቶች ውጪ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ መሆኑ በመቅረቱ ለጉንፋን መዛመት ብሎም ለኢንፍሉዌንዛ ታማሚዎች መበራከት በምክንያትነት እየተጠቀሰ ነው።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ