1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቅሬታ ያስነሳው የክላስተር ከተሞች አደረጃጀት

ሐሙስ፣ ነሐሴ 4 2015

አዲስ በሚዋቀሩት የቀድሞው የደቡብ ክልል ዞኖች የተካሄደው የአስፈጻሚ ቢሮዎች እና ተቋማት የመቀመጫ ከተሞች ድልድል ቅሬታና ተቃውሞ ገጥሟታል፡፡ በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ ዞኖች ድልድሉ ፍትሃዊነት የጎደለው ነው በሚል አደባባይ በመውጣት ተቋውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ ፡፡

https://p.dw.com/p/4V0to
SNNPR President office

SNNPR President office
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤትምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ቅሬታ ያስነሳው የክላስተር ከተሞች አደረጃጀት

«የማዕከላዊ ኢትዮጵያ» እና «የደቡብ ኢትዮጵያ» በሚል መጠሪያ በሁለት ተከፍለው የሚዋቀሩት አዳዲስ ክልሎች ራሳቸውን ለማደራጀት ከጫፍ ደርሰዋል። ክልሎቹ ራሳቸውን ወደማደራጀት የገቡት እየከሰመ የሚገኘው የደቡብ ክልል ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል «የመጨረሻ» ያለውን ጉባኤ ከቀናት በፊት ማካሄዱን ተከትሎ ነው። ያም ሆኖ የአዳዲሶቹ ክልሎች አስፈጻሚ ቢሮዎች እና ተቋማት የመቀመጫ ከተሞች ድልድል ግን በአንዳንድ ዞኖች ላይ ቅሬታ እያስነሳ ይገኛል። የከምባታ ጠንባሮ፣ የጋሞ እና  የሃድያ ዞኖች ነዋሪዎች  የአስፈጻሚ ቢሮዎችና ተቋማት ድልድሉ ፍትሃዊነት የጎደለው ነው የሚል ከወዲሁ ቅሬታ እያቀረቡ ይገኛሉ።

ቅሬታው በከምባታ ጠንባሮ ዞን ለምን በረታ?

የደቡብ ክልል ሕዝበ ውሳኔ ውጤት በፌዴሬሽን ም/ቤት ጸደቀ

በከምባታ ጠንባሮ ዞን ዱራሜ ከተማና በተለያዩ ወረዳዎች ኢፍትሃዊ ነው ያሉትን ድልድል በአደባባይ በመውጣት ጭምር ተቃውሟቸውን መግለጻቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። «አብዛኛው የዞኑ ነዋሪ የክልሉን  አደረጃጀት ተስማምቶ ተቀብሏል፤» በማለት ለዶቼ ቬለ የተናገሩት አንድ የድራሜ ከተማ ነዋሪ  «ይሁን እንጂ የቢሮዎች ክፍፍሉ ፍትሃዊነት የጎደለው ነው። ለምሳሌ ሌሎች ዞኖች እስከ ሰባትና ስምንት ቢሮዎች ሲያገኙ እኛ ግን አንድ የግብርና ቢሮ ብቻ ነው የደረሰን። ይህ የሆነው በሥልጣን ላይ ያሉ የክልሉ አመራሮች ክፍፍሉ ላይ ለራሳቸው በማድላታቸው ነው የሚል ድምዳሜ በነዋሪዎች ላይ እንዲያጭር አድርጓል» ብለዋል። «ክልሉ ቅሬታችንን ዳግም ሊያጤነው ይገባል በሚል ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ አሁን ድረስ ድምጻችንን በሠልፍ ጭምር እያሰማን እንገኛለን» ያሉት ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው «ቅሬታችሁን ለምን ገለጻችሁ በሚል በርካታ ሰዎች በፀጥታ አባላት ታስረውብን ይገኛሉ» ብለዋል።

አሥራ ሦስት ማዕከላት   

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ
ላለፉት 30 ዓመታት ገደማ የደቡብ ክልል አካል የነበሩት የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የጌዴኦ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የኮንሶ ዞኖችና የደራሼ፣ የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የኧሌና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች «የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል» በሚል አዲስ ክልል የሚደራጁት ጥር 29 2015 ዓም ባካሄዱት የሕዝበ ውሳኔ ውጤት መሠረት ነው።ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ቅሬታ እየቀረበበት የሚገኘው የአስፈጻሚ ቢሮዎችና ተቋማት ድልድል የተዘጋጀው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምሥረታ እና ነባሩን ክልል መልሶ ማደራጀት ፕሮጀክት በተባለው ጽሕፈት ቤት አማካኝነት ነው። የደቡብ ክልል መንግሥት እስካሁን በቅሬታው ላይ በይፋ የሰጠው ምላሽ የለም። ያም ሆኖ ድልድሉ የዞኖችና  የልዩ ወረዳ አመራሮች የተወከሉበትና ሠፊ ውይይት የተደረገበት ነው ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርዕስቱ ይርዳው ከቀናት በፊት በተካሄደው የክልል ምክር ቤት ላይ ለጉባኤተኛው ገልጸዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ የከተሞች ክላስተር አደረጃጀት ያለቸውን ጥቅም ከማብራራት ባለፈ  የቢሮዎቹን ፍትሃዊ ድልድል በሚመለከት ስላለው ቅሬታ በቀጥታ ያሉት ነገር የለም። እስካሁን በነበረው ሁኔታ በአንድ የከተማ ተሰብስበው የነበሩ ተቋማት አሁን በ13 ማዕከላት መደልደላቸውን የጠቀሱት አቶ ርዕስቱ ተቋማቱ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መሄዳቸው «ቀደም ሲል ልማት አላገኘንም፣ ትኩረት አልተሰጠንም በሚል ሲነሱ የቆዩ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያስችላል። ዋናው ነገር ግን ተቋማቱ እዚህ ወይም እዚያ መሆናቸው ሳይሆን በሚሰጡት አገልግሎት ነው መመዘን ያለባቸው» ብለዋል።   

የክላስተር ከተሞች አደረጃጀት ለነዋሪው ጥቅም ወይስ ጉዳት ?

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ
ለሕዝበ ውሳኔው ድምጹን ለመስጠት ከወጣው ሕዝብ በከፊልምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ላለፉት 30 ዓመታት ገደማ የደቡብ ክልል አካል የነበሩት የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የጌዴኦ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የኮንሶ ዞኖችና የደራሼ፣ የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የኧሌና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች «የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል» በሚል አዲስ ክልል የሚደራጁት ጥር 29 2015 ዓም ባካሄዱት የሕዝበ ውሳኔ ውጤት መሠረት ነው።

በአንጻሩ የጉራጌ፣ የሥልጤ፣ የከምባታ ጠንባሮ፣ የሃድያ፣ የሀላባ ዞኖች እንዲሁም የየም ልዩ ወረዳ ደግሞ ያለሕዝበ ውሳኔ ነባሩን ክልል መልሶ በማዋቀር የማዕከላዊ ኢትዮጵያ በሚል እየተደራጁ እንደሚገኙ ይታወቃል። አሁን በክልሎቹ ተግባራዊ እየሆነ የሚገኘው የአስፈጻሚ ቢሮዎችና ተቋማት በተለያዩ ከተሞች እንዲሆኑ ማደረጉ ጠቀሜታው የቱን ያህል ነው በሚል ዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ አቶ ሁለመናዬ ለገሠ አደረጃጀቱ ጥቅምም ጉዳትም አለው ይላሉ።

«አንድ ቦታ ላይ ብቻ የነበረው የቢሮ አሠፋፈር ያንን አንድን ከተማ ብቻ በመጥቀም ሌሎች ከተሞችን የበይ ተመልካች የሚያደርግ ነው» ሚሉት አቶ ሁለመናዬ ይህም «ከተሞቹ ከተቋማት መኖር ጋር ተያይዞ ከሚገኘው የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የሆቴል እና የተለያዩ የንግድ  አንቅስቃሴዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። በአንጻሩ ህዝቡ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ከአንድ ወደ ሌላ ከተማ እንዲጓጓዝ በማድረግ መጉላላትን ሊያስከትል ይችላል። ያምሆኖ ፍትሃዊና ሁሉንም የሚያስማማ እስከሆነ ድረስ በክላስተር መደራጀቱ የጎላ ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል»› ብለዋል።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ