1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመሻሻል ላይ ያለው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት

ሰኞ፣ ጥር 5 2017

ውጥረት ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት በአንካራው ስምምነት የለዘበ ሲሆን የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሙሐሙድ በሳምንቱ መጨረሻ አዲስ አበባን እንዲጎበኙም አስችሏል። አንድ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ ለዶቼቬለ እንዳሉት "ወሳኙ ነገር መሪዎቹ በሚነጋገሩት ልክ ቁርጠኛ ሆነው በተግባር ንግግራቸውን መከወናቸው»ነው።

https://p.dw.com/p/4p6ct
Äthiopien Addis Abeba 2025 | Überraschungsbesuch des somalischen Präsidenten
ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

በመሻሻል ላይ ያለው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት

የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ መሐሙድ ቅዳሜ እና እሑድ አዲስ አበባን የጎበኙ ሲሆን ደማቅ የሆነ አቀባበልም፣ ሽኝትም ተደርጎላቸዋል። ይህም ለአንድ ዓመት ያህል ጊዜ በውጥረትና ውዝግብ ይገለጥ የነበረውን የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን ግንኙነት ወቅታዊ መልክ እና ምዕራፍ የለወጠ መስሏል። የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተመራማሪ እና "ኢንተራክሽን ፎር ቼንጅ ኢን አፍሪካ" የተባለ ተቋም ሥራ አሥኪያጅ የሆኑት ዶክተር ወርቁ ያዕቆብም ይህንኑ ታዝበዋል፤ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ። "በመካከላቸው ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ አምጥተው ሰላም ፈልገው፣ ለጋራ ተጠቃሚነት በጥሩ ሁኔታ እየሠሩ መሆናቸውን ነው የሚያመላክተው።"ብለዋል።

ኢትዮጵያና አዲሱ «የአፍሪቃ ኅብረት የድጋፍና ማረጋጋት የሶማሊያ ተልዕኮ»
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ቅዳሜ ዕለት አዲስ አበባ ውስጥ ከተወያዩ በኋላ በወጣ መግለጫ አንድም ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ወደነበረበት ለመመለስ፣ በሌላ በኩል በየመንግሥታቶቻቸው ዋና መቀመጫዎች የተሟላ ዲፕሎማሲያዊ ውክልና እንዲኖርም መስማማታቸው ይፋ ተደርጓል። በመግለጫው ይህ ቀጣና የሁለቱን ሀገራት መተማመን እና መከባበር መሠረተ ያደረገ ትብብር እንደሚስፈልገውም ተጠቅሷል።

በከፍተኛ ባለሥልጣናት የታጀበው የሰሞኑ የሁለቱ ሀገራት ተከታታይ ግንኙነት ግን ቁርጠኝነት የሚፈልግ ተግባር የሚያሻው መሆኑን ዶክተር ወርቁ ያዕቆብ ገልፀዋል።የሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የአንካራ ስምምነት፥ የሶማሊላንድ በዓለ ሲመት
"ዋናው ወሳኝ የሚሆነው በተነጋገሩት ወይም በሚነጋገሩት ልክ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ቁርጠኛ ሆነው በቃላት ደረጃ የሚያሰፍሯቸውን ጉዳዮች በተግባር መከወናቸው ነው፣ አብረው ይሠራሉ የሚለውን ነገር ሊያረጋግጥ የሚችለው።"የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በቱርክ ሸምጋይነት የተደረሰውን ስምምነት በቁርጠኝነት ለማስፈፀም መስማማታቸውም በወጣው መግለጫ ተጠቅሷል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ መሐመድ በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በእዮቤልዩ ቤተ መንግሥት አቀባበል ሲደረግላቸው
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ መሐመድ በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በእዮቤልዩ ቤተ መንግሥት አቀባበል ሲደረግላቸው ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ዕጣ ፋንታ ምን ይሆን ?

ሌላኛው የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ ይህ ስምምነት ምናልባትም የሁለቱ ሀገራት ውዝግብ ምንጭ የሆነው የአዲስ አበባ - ሀርጌሳው የመግባቢያ ስምምነት ዕጣ ፋንታ ላይ የወሰነ ሳይሆን እንደማይቀር አብራርተዋል። "የኢትዮጵያ መንግሥት የሚኖረውን ስምምነት [የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ የተምለከተን] በሞቃዲሾ የፌዴራሉ መንግሥት ሉዓላዊ ግዛት ሥር ያደርጋል የሚለው ሀሰብ ምናልባትም በሶማሊላንድ እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ተስማሙበት የተባለው የጋራ መግባቢያ ሰነድ ምናልባት ቀሪ ተደርጓል የሚል እንድምታ ይኖረዋል።"

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ መሐመድና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በእዮቤልዩ ቤተ መንግሥት
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ መሐመድና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በእዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia


ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር እንጂ ለሶማሊላንድ የተለየ ወገንተኝነት ኖሯት ወይም ከሶማሊያ የተለየ ችግር ኖሮባት አይደለም የሚሉት ዶክተር ወርቁ ያዕቆብ ኢትዮጵያ ትልቁን የባህር በር የማግኘት ፍላጎቷን ከሶማሊያ መንግሥት እስካገኘች ድርስ የሶማሊላንዱ የመግባቢያ ስምምነት ቢቀር ነውር የለውም ባይ ናቸው። "ለብሔራዊ ጥቅም ሲባል የተለያዩ ውሳኔዎችን ሊወስኑ ይችላሉ [ሀገራት]። ዋናው ነገር ሀገር መጠቀሟ ነው ከምታደርገው እንቅስቃሴ።"

የሞቃዲሾና አስመራ ንግግር አንድምታ
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ አሰላለፍ እየፈጠሩ ያሉ የሚመስሉት የሶማሊያ፣ የኤርትራ እና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዚሁ ሳምንት ካይሮ ውስጥ ተወያይተዋል።
ግብጽ የቀይ ባሕር ተዋሳኝ ያልሆነ ሀገር የባሕር በር ሊያገኝ አይችልም የሚለውን አቋሟን አሁንም ማስተጋባቷን ብትቀጥልም፣ ተንታኞች ይህ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንፃር ተቀባይነት እንደሌለው እና ይልቁንም ቁልፉ እና ወሳኙ ጉዳይ የኢትዮጵያ፣ የሶማሊያ፣ የኤርትራ እና የጅቡቲ መሪዎች የሚያደርጓቸው ግንኙነቶች እና ስምምነቶች ናቸው ብለዋል።
ሰሎሞን ሙጬ 
ኂሩት መለሰ