1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የቅመማ ቅመም ዘርፍ ምርት፣ የገበያ ዕድልና ተግዳሮት

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 23 2017

ትዮጵያ ከ50 በላይ የቅመማ ቅመም አይነቶችን ለማምረት የሚያስችል የእርሻ ሥነ ምህዳር እንዳላት ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡ በአውሮፕያኑ 2022 ዓ.ም በተደረገ ጥናት በአገሪቱ ከ386 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የቅመማ ቅመም ምርት ይውላል ፡፡

https://p.dw.com/p/4ojUo
Äthiopien | Die Ingwerproduktion und ihr wirtschaftlicher Wert in Südäthiopien
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የዝንጅብል አምራቾች የገጠማቸው የገበያ ተግዳሮት

የቅመማ ቅመም ዘርፍ የገበያ ዕድልና ተግዳሮት

ኢትዮጵያ ከ50 በላይ የቅመማ ቅመም አይነቶችን ለማምረት የሚያስችል የእርሻ ሥነ ምህዳር እንዳላት ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል   ፡፡ በአውሮፕያኑ  2022  ዓ.ም በተደረገ ጥናት በአገሪቱ ከ386 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የቅመማ ቅመም ምርት ይውላል  ፡፡ ከ 600 ሺህ በላይ አርሶአደሮችም ኑሯቸውን በዚሁ ዘርፍ ላይ የመሠረቱ ናቸው ፡፡

የአምራቾቹ  ተስፋና ፈተና

እዚህ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከምባታ ዞን ሀደሮ ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ የዝንጅብል ምርት ከማሳ እየተሰበሰበ ይገኛል ፡፡ በአካባቢው ከታህሳስ እስከ ጥር ያሉት ወራቶች የደረሰ የዝንጅብል ምርት የሚለቀምበት ወቅት ነው  ፡፡ በወረዳው አጆራ ቀበሌ የዝንጅብል አምራች የሆኑት ኢንዲሪያስ ላሞሬ እና ዳዊት ደጀኔ ምርቱ በስፋት ከተተከለ ጥሩ ውጤት ይገኝበታል ይላሉ ፡፡

እንድሪያስ ላሞሬ
እዚህ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከምባታ ዞን ሀደሮ ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ የዝንጅብል ምርት ከማሳ እየተሰበሰበ ይገኛል ፡ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በዝንጅል ምርት የተሰማራ ሰው የተሸለ ትርፍ እንዳለው የጠቀሱት እንዲሪያና ዳዊት “ ለምሳሌ አንድ ኩንታል የዝንጅብል ዘር ከተከልክ ከአሥር ኩንታል በላይ ይወጣዋል ፡፡ በዚህ መሠረት በዓመት እስከ ሦስት መቶ እና አራት መቶ ኩንታል ይገኛል ማለት ነው ፡፡ ይሁንእንጂ የምርት አቅርቦቱን ለመጨመር የሚያስፈልጉ የእርሻ ማዳበሪያና የፀረ ነፍሳት ኬሚካል አቅርቦት የለም ፡፡ ይህ በመንግሥት በኩል ሥለማይገኝ አቅርቦቱን በውድ ዋጋ ከነጋዴ እጅ ለመግዛት ተገደናል ፡፡ ይህም ጭማሪ ያለው ምርት እንዳናመርት እያደረገን ይገኛል  “ ብለዋል ፡፡

አቶ ዳዊት ደጀኔ
አንድ ኩንታል የዝንጅብል ዘር ከተከልክ ከአሥር ኩንታል በላይ ይወጣዋልምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የቅመማ ቅመም ምርት ውጤት ተመልካቹ ምክክር

በደላላ የሚመራው የዝንጅብል ገበያ

በከምባታ ዞን ሀደሮ ጡንጦ ወረዳ ዘወትር ረዕቡ እና ቅዳሜ የዘንጅብል ገበያ የሚቆምበት ቀን ነው ፡፡ በዝንጅብል ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ ደሳለኝ ሀደሮ ብዛት ያለው ምርት ለመረከብ መምጣታቸውን ይናገራሉ ፡፡ ግን ደግሞ በገበያው የፈለጉትን መጠን ሊያገኙ አልቻሉም ፡፡ ምርቱ በገጠር በስፋት መመረቱን እንደሚያውቁ የጠቀሱት ደሳለኝ “ ወደ ገበያ ሊወጣ ያልቻለቀው በመጓጓዣ ችግር የተነሳ ነው ፡፡ ምርቱ በሚገኝባቸው የገጠር ቀበሌያት በመንገዶች መበላሸት የተነሳ ሊደርሱ  የሚችሉት ባለሦስት እግር ባጃጅ እና ባለሁለት እግር ሞተር ሳይክሎች ብቻ ናቸው ፡፡  በአንዴ በርከት ያለ ምርት ሊይዝ የሚችል የጭነት ተሸከርካሪ አለመግባቱ በገበያ ላይ ብዙ ምርት እንዳይወጣ አድርጓል ፡፡ የመጣውም ቢሆን  ሙሉ በሙሉ በደላላ ቁጥጥር ሥር ሆኖ የሚሸጥ በመሆኑ አምራቹም ሆነ ነጋዴው ተጠቃሚ እየሆነ አይደለም “ ብለዋል ፡፡

አቶ ደሳለኝ ሀደሮ
በከምባታ ዞን ሀደሮ ጡንጦ ወረዳ ዘወትር ረዕቡ እና ቅዳሜ የዘንጅብል ገበያ የሚቆምበት ቀን ነው ፡፡ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የምጣኔ ሃብት ማሻሻያው በአማራ ክልል ግብይት ላይ ምን አስከተለ?

የግብዓት አቅርቦት

በከምባታ ዞን የሚገኘው የሀደሮ ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ በዝንጅብል አምራችነቱ የሚታወቅ ነው ፡፡ በወረዳው 5 ሺህ 700 ሄክታር ለዚሁ ምርት መዋሉን የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ሀብታሙ ዮሀንስ ይናገራሉ ፡፡ ምርቱ ከሌሎች የሰብል አይነቶች ጋር ሲነጻጸር ከገቢ አንጻር የተሻለ ጠቀሜታ እንዳለው የጠቀሱት  የጽህፈት ቤት ሃላፊው “ ነገር ግን አምራች አርሶአደሮች የግበዓት አቅርቦትን በተመለከተ  የሚያነሱት ቅሬታ ትክክል ነው ፡፡ ይህ የሆነው የቅመማ ቅመም ምርት እንደሌሎች የግብርና ምርቶች ትኩረት አግኝተው እንደእፈር ማዳበሪያ የመሳሰሉት የግበዓት አቅርቦት ታቅዶ ሥለማይቀርብላቸው ነው ፡፡ አሁን ላይ ምርቱን ከግበዓት ውጭ በአርሶአደሩ ጥረት ብቻ ማሳደግ እንደማይቻል መግባባት ላይ በመደረሱ ከ2017 ዓም ክረምት ጀምሮ ዝንጅብልን ጨምሮ የቅመማ ቅመም ምርት የግበዓት አቅርቦት ተጠቃሚ ይሆናሉ “ ብለዋል ፡፡

ዶ/ር ሀብታሙ ዮሐንስ
በከምባታ ዞን የሚገኘው የሀደሮ ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ በዝንጅብል አምራችነቱ የሚታወቅ ነው ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የግዙፉ የገበያ ማዕከል - የመርካቶ የዛሬ ውሎ

የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ

በኢትዮጵያ የቅመማ ቅመም ምርትን ለማሻሻል ፣ ለመደገፍና ለመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው ተቋም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ነው ፡፡ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብትም ሆነ አምራች አርሶአደሮች ምንም እንኳን ከዘርፉ በሚፈለገው መጠን ተጠቃሚ ባይሆኑም ምርቱን በስፋት  ለማምረት የሚያስችል የተለያዩ ለምርቱ ተስማማሚ የሆኑ የሥነ-ምህዳር አይነቶች መኖራቸውን በባለሥልጣኑ የቅመማ ቅመም ልማት ዴስክ ሃላፊ  አቶ ሞጎስ አሸናፊ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡

የገበያ ዋጋ ለማረጋጋት መንግስት ምን እያደረገ ይሆን ?

እንደሌሎች ሰብሎች የተሻሻሉ ዝርያዎች አለመቅረባቸው ፣ በዘልማድ የሚመረት በመሆኑ የምርት ጥራት ጉድለት ማስከተሉ እና ጤናማ የግብይት ሠንሰለት አለመኖር በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን የተናገሩት ሃላፊ “ አሁን ላይ ዘርፍን ለማሳደግ እንቅፋት የሆኑና ከግበዓት አቅርቦት ፣ ከምርት ጥራት እና ከግብይት ሠንሠለት ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ ይገኛል  ፡፡ በተለይ የግብይትና የምርት ጥራትን በተመለከተ አስገዳጅ አዋጆችና ደንቦች ከሌሉ ሁኔታዎችን ማስተካከል አዳጋች እንደሆነ ከመግባባት ላይ ተደርሷል ፡፡ ከዚህ መነሻ አሁን ላይ ይህን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችሉ አስገዳጅ አዋጆች እና የህግ ማዕቀፎች የማዘጋጀት  ሥራዎች እየተጠናቀቁ  ይገኛሉ “ ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ታምራት ዲንሳ