በሰብዓዊ መብት ይዞታ ኢትዮጵያ «አብነት» ተባለች
ሐሙስ፣ ጥር 9 2011ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዉማን ራይትስ ዎች የ100 ሀገራትን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ አስመልክቶ ዛሬ ባወጣዉ ዘገባ የምስራቅ አፍሪቃ መንግስታት የዜጎቻቸዉን መብት እያከበሩ እያስከበሩ አይደለም አለ። የኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ተስፋ ሰጭ ነዉ ብሏል። የዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት «ሂውመን ራይትስ ዎች» የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ኃላፊ ጀሃን ሄንሪን አነጋግረናል።
ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዉማን ራይትስ ዎች ዛሬ ይፋ ባደረገዉ መግለጫ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳን የመሳሰሉ በአፍሪቃዉ ቀንድ አካባቢ የሚገኙት ሃገራት ሰላማዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴዎችን፣ ጋዜጠኞችንና የመብት ተሟጋቶችን፣ የመናገር እና የመፃፍ ነፃነትን ያፍናሉ ሲል ተችቷል። ድርጅቱ ዛሬ ይፋ ባደረገዉ 674 ገጽ መግለጫ ላይ የድርጅቱ የአፍሪቃ ዳይሬክተር ኬኔት ሮዝን ጠቅሶ እንዳስነበበዉ በሶማልያ፤ ሱዳን፤ ኬንያ፤ ታንዛንያ እና ኡጋንዳ ዉስጥ የሚገኙ የታጠቁ ሀይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከፍተኛ ነዉ። ስለሆነም መንግስታቱ የዜጎቻቸዉን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት በማክበር ረገድ ጠንክረዉ ሊሰሩ ይገባል ብሎአል። በአፍሪቃዉ ቀንድ አካባቢ ሃገራት መካከል ካለፈዉ መጋቢት ማብቂያ ጀምሮ አዲስ ከተሾሙት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከዐቢይ አሕመድ በኋላ ሃገሪቱ መብትን በማክበር ረገድ ጥሩ መሻሻል አሳይታለች። ኢትዮጵያ ዉስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማንሳቱ፣በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ እስረኞችን መልቀቁ፣ ጨቋኝ የሚባሉ ባለሥልጣናትን ከሥልጣን ማንሳትና ጨቋኝ የሚባሉ ሕግጋትን ለመሻር መታቀዱን ዓለም አቀፉ ድርጅት ለሰብአዊ መብት መከበር እንደ ጥሩ እርምጃ ሲል አዉድሶታል። የዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት «ሂውመን ራይትስ ዎች» የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ኃላፊ ጀሃን ሄንሪ ዛሬ ለ «DW» ኢትዮጵያ ለቀጣናዉ ሃገራት በምሳሌነት የምትቀርብ ናት ብለዋል።
« እርግጥ ነዉ በኢትዮጵያ ታህድሶ እየተደረጉ መሆናቸዉን የሚመለክቱ ኽዉነቶች ይታያሉ። በሃገሪቱን ጨቋኝ የተባሉ ሕጎች ዳግም እየተፈተሹ ነዉ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነስቶአል ፤ የፖለቲካ እስረኞች ተፈተዋል። በርግጥ ይህ ተፈፃሚ ሆኖ መቀጠሉን የምናየዉ ይሆናል። እርግጥ ነዉ ኢትዮጵያ ያሳየችዉ አወንታዊ ለዉጥ በቀጠናዉ ሃገሮች አሁንም ጭቆናና ግፍ ዉዝግብና ግጭት እንዲሁም እስራት ለሚታይባቸዉ የአካባቢዉ ሃገራት በምሳሌነት እንድትጠቀስ ያደርጋታል።»
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ እስረኞችን የመፍታት፤ በሶማሌ ክልል ይገኝ የነበረውን “ጄል ኦጋዴን” የመሳሰሉ የማሰቃያ እስር ቤቶችን የመዝጋት እንዲሁም አፋኝ ህጎችን ለማሻሻል ጥረት መደረጉን ሂዉማን ራይትስ ዎች ይፋ ባደረገዉ ዘገባዉ አስነብቦአል። የኢትዮጵያን መሻሻል አወንታዊና ተስፋ ሰጪም ነዉ ብሎታል። ኢትዮጵያ ካለፉት 27 ዓመታት ወዲህ በድርጅቱ ስሟ በበጎ ሲነሳ ይህ የመጀመሪያዉ መሆኑ ነዉ።
በኤርትራም ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያኑ 2018 መጠነኛ መሻሻል መታየቱን ያስነበበዉ ይሐዉ መግለጫ ፤ እንድያም ሆኖ ሃገሪቱ አሁንም ነፃ ሚዲያ ፤ የተደራጁ የሲቪክ ድርጅቶች ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ እንዲሁም የፍትሕ ሥርዓት የለም ፤ በሃገሪቱ አሁንም የዘፈቀደ እስራት የተለመደ ነዉ ብሎአል። በኒዮርክ የሚገኙት «ሂውመን ራይትስ ዎች» የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ኃላፊ ጀሃን ሄንሪም ይህንኑ ነዉ የደገሙት።
«በኤርትራ የሚታየዉ ልክ እንደ ሱዳን ነዉ ። የተሻሻl ነገር የለም ፤ የተደራጀ የሲቢክ ማኅበራት እጥረት ይታያል። በሃገሪቱ ገለልተኛ የመገናኛ ብዙሃን የለም። ነፃ የፍትህ ስርዓት የለም። በግፍ እስራት አላቆመም። አሁንም በግዳጅ የዉትድርና ምልመላ፤ በኤርትራ ዉስጥ የሚታይ ትልቅ ችግር ነዉ።»
እንደ ሱዳን ሁሉ በኤርትራም ያለዉ ሁኔታ ተመሳሳይ ነዉ ያሉት የ«ሂውመን ራይትስ ዎች» የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ኃላፊ ጀሃን ሄንሪን ምንም እንኳ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ በሃገራቱ ላይ የጣለዉን ማኅቀብ አንስቶ ከሃገራቱ ጋር በአንዳንድ ነገራት ያለዉን ተሳትፎ ከፍ ቢያደርግም በሁለቱም ሃገራት የሚታየዉ የሰብዓት ይዞታ አሁንም በጣም ችግር ይታየበታል፤ ምንም አይነት መሻሻልም አላየንም ብለዋል።
አዜብ ታደሰ
ተስፋለም ወልደየስ