1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

በሳውዲ አረቢያ የቀጠለው የኢትዮጵያውያን ሰቆቃ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 2 2014

ሳውድ አረቢያ ውስጥ በስደት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚያሰሙት የድረሱልን ድምጽ ዛሬም ቀጥሏል። ለደህንነታቸው ከሚሰጉት በተጨማሪ እስር ቤት የሚገኙት እና በህመም የሚሰቃዩት ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ ቢመኙም መውጫ ማግኘት አለመቻላቸውን ይናገራሉ። የተወሰኑትን በማነጋገር ሸዋዬ ለገሠ ተከታዩን አጠናቅራለች።

https://p.dw.com/p/41aRx
ፎቶ ከክምችት ክፍል
ፎቶ ከክምችት ክፍልምስል DW/S. Shiberu

በሳውዲ አረቢያ የቀጠለው የኢትዮጵያውያን ሰቆቃ

ሳውድ አረቢያ፣ የመኖሪያ እና የሥራ ሕግን የጣሱ ያለቻቸውን ከ16 ሺህ በላይ  ስደተኞችን ማሰሯን የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ከቀናት በፊት ይፋ አድርጓል። በአንድ ሳምንት ውስጥ እስራቱ የተከናወነው በተለያዩ የሀገሪቱ ግዛት በተካሄደ የተጠናከረ አሰሳ መሆኑንም አመልክቷል። ሪያድ የምትገኘዉ ኢትዮጵያዊት ረዥም ዓመታት ሳውድ አረቢያ በኖሩት ላይ ሳይቀር ወከባው እና እስራቱ ከጀመረ መቆየቱን ትናገራለች።

«አሰሳውማ ከሦስት ወር ከአራት ወር ይበልጣል። ስንት ዓመት ለፍተን እኔ ለምሳሌ ዘጠኝ ዓመት ይሆነኛል እና ያን ሁሉ መቼም እንዲህ በአንድ ሀገር ስንኖር ስንት ንገር ይኖራል? ለእኛ አንዲት ብጣቂ ልብሳችን እንኳ ብትሆን ትልቅ ነገር ናት እና ያንን እንኳ ለመያዝ አይታገሱሽም።»

በዚህ መሀል የታመመች ሌላ ኢትዮጵያዊት ወደ ሀገሯ ለመመለስ አለመቻሉን በመጥቀስም መፍትሄ የሚሰጣት አካል ካለ ትጣራለች።

«አንዲት የታመመች እህት ከስድስት ወር በላይ ይሆናታል። ኤምባሲ ጋር በአሁኑ ሰአት ህመምተኛ ያስተናግዳሉ በሚለው ሄደች ማንም ዞር ብሎ የሚያያት የለም። እንደዚ ሰውነቷ ምንምን ብሎ ተደግፋ ሄዳ እሷን እንኳ ሊያስተናግዱ አልቻሉም እንኳን ጤነኛውን።»

ኢትዮጵያውን ኢላማ ሆነዋል የሚለው ሌላው እማኝ እስር ቤት የሚገኙ እየገፉት ያለውን የስቃይ ሕይወት ያስረዳል።

«ከአንድ ወር ሕጻን ልጅ እስከ 49 እና 50 አዛውንት ጥርግ አድርገው ነው የሚያስገቡት ማለት ኢትዮጵያዊ ብቻ በመሆናችን። እስር ቤት አንድ ክፍል ውስጥ 50 እና 30 ሰዎች አጉረዋቸዋል። ታማሚዎች አሉ ህክምና እንኳ አያደርሷቸውም፤ በሰው ፍጡር ላይ የማይደረግ ሥራ ነው እየተደረገ ያለው።»

ሳውድ አረቢያ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ላይ ያነጣጠረ ቤት ሰበራ እና ፍተሻው ተጠናክሮ ቀጥሏል የሚለው ሌላው የዓይን ምስክር በሰው ሀገር ለሚዋከቡት ወገኖች በኢትዮጵያ ቆንስላ በኩል በቂ ድጋፍ እየተደረገ አይደለም ባይ ነው።

በአንጻሩ በጣም በርካታ ታማሚዎች እንዳሉ እና ገንዘብ የመክፈል አቅም ስለሌላቸውም ስቃይ ውስጥ ይገኛሉ ነው ያለው። ይኽን መሰል ተመሳሳይ ችግር መኖሩን የገለጹልን በርካቶች ናቸው። መረጃ እጃቸው ላይ እያለ የሚከራከርላቸው ወገን ባለመኖሩ ለእስር የተዳረጉ፤ እነሱ በጎን ይከፈላል የሚሉትን በሺህ የሚቆጠር የሳውዲ ገንዘብ መክፈል ባለመቻላቸውም ተገቢውን ትብብር ከኤምባሲያችን አላገኘንም የሚሉትም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። እንዲህ ያለውን አቤቱታ ይዘን የደወልንላቸው በጅዳ ቆንስላ ጀነራል አምባሳደር አብዱ ያሲን ዛሬ ከንጋቱ ጀምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ ችግር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት በሥራ ላይ መጠመዳቸውን በመግለጽ ለማንኛውም ማብራሪያ አዲስ አበባ ወደሚገኘው መስሪያ ቤት ወይም የቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ደውሉ በማለታቸው ከቢሯቸው ወገን ያለውን ምላሽ ማካተት አልቻልንም።  የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይን ለማግኘት ያደርግነው የስልክ ጥሪም አልተመለሰም።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ