በቆጂ ሥመጥር አትሌቶችን ማፍራት ለምን ተሳናት?
የአርሲ ዞን አንዷ ከተማ በቆጂ ከአትሌት ደራርቱ ቱሉ እስከ ቀኒሳ በቀለ፤ የዲባባ ስኬታማ ቤተሰብ እና ሌሎችም በቁጥር የላቁ ስኬታማ አትሌቶች ከዚህች ስፍራ ወጥተዋል። በአንድ ወቅት ዓለምን ያስደመሙ አትሌቶች ይፈልቁባት የነበረችው በቆጂ አሁን አሁን ስመ ጥር አትሌቶችን እንደ ቀድሞ ማፍለቅ የተሳናት ለምን ይሆን?
የበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል
ይህ የበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በ2004 ዓ.ም. ጥቅምት ወር ላይ ነበር ተከፍቶ ታዳጊ አትሌቶችን ለማሰልጠን መቀበል የጀመረው። ማዕከሉ ባለፉት 10 ዓመታት 193 አትሌቶችን ሲያሰለጥን፤ 133 ያህሉን ደግሞ የአትሌቲክስ ቡድኖችን እንዲቀላቀሉ አስችሏል። በአሁን ወቅት ከ18 ዓመት በታች 36 አትሌቶችን በማሰልጠን ላይ ይገኛል።
የበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል
የበቆጂ አትሌቲክስ ማዕከል ከበቆጂ ከተማ መውጫ ስፍራ ላይ የሚገኝ ነው። ይህ ስፍራ ስመጥር አትሌቶችን ያፈራ አካባቢ ነው። ከዚህ ማዕከል ጀርባ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ተወልዳ አድጋበታለች። ከመንገዱ ዝቅ ሲል ደግሞ የአትሌት ቀኔኒሳ በቀለ የትውልድ ስፍራ በቅርበት ላይ ይገኛል።
ለአትሌቶች አመቺው የበቆጂ አቀማመጥ
ይህ ስፍራ ዳሞታ ይባላል። ከበቆጂ ከተማ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ውስን ኪሎ ሜትሮች ወጣ ብሎ ይገኛል። በዳሞታ ደን እና አቀበታማ ስፍራ ወጥቶ ያልወረደ የበቆጂ ዙሪያ አትሌት የለም። በደኖቹ መሀል ሰውነታቸውን የሚያቀላጥፍ የስፖርት ስልጠና ይወስዳሉ። አቀበታማ ስፍራው ደግሞ ጥንካሬን የሚሰጥ ለአካል ማጎልበቻ መለማመጃ ነው።
ታዳጊ አትሌቶች ለስልጠና ተሰባስበው
እነዚህ አትሌቶች ወደ ልምምድ ስፍራቸው ከመሄዳቸው አስቀድሞ ተሰባስበው አሰልጣኛቸውን በመጠባበቅም ላይ ናቸው። እንደ አየሩ ጠባይ እዚህ ቦታ የሚሰባሰቡበት ሰአት አንዳንዴ ቢሸጋሸግም ጠዋት ከ12 ሰዓት ጀምሮ ግን ወደ ልምምድ ስፍራቸው ለመሄድ የመሰባሰብ ግዴታም አለባቸው።
ታዳጊ አትሌቶች በስልጠና ላይ
እነዚህ ታዳጊ ልጃገረድ ተስፈኛ አትሌቶች በበቆጂ ከተማ ሲንቄ የሴቶች ልማት ማኅበር በሚሰኝ ግብረሰናይ ድርጅት እየተደገፉ የአትሌቲክስ ልምምድ የሚያደርጉ ናቸው። በምስሉ እንደሚታየው አትሌቶቹ ወደ ልምምድ ከመግባታቸው በፊት ከአሰልጣኛቸው ፈቲያ አብዲ ምክርና ትዕዛዝ በመቀበል ላይ ናቸው። ሜዳ አቀበቱ ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል።
የበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል የመለማመጃ ሜዳ
ይህ ሜዳ በርካታ ዕውቅ የኢትዮጵያ አትሌቶችን ያፈራ ነው። ሜዳው ካለፉት 10 ዓመታት አንስቶ በበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ስር ይገኛል። የአፍሪቃ ሴት አትሌቶች ተምሳሌት የሆነችው የአትሌት ደራርቱ ቱሉ የትውልድና እድገት ስፍራም እዚሁ ሜዳ አጠገብ ነው።
የበቆጂ ከተማ ስፖርት ጽ/ቤት
ይህች በምስሉ የምትታየው አነስተኛ ቤት ለበቆጂ ተለማማጅ አትሌቶች መመሪያ የሚሰጥባት ስፍራ ነው፡፡ በውስጧ አራት የጽ/ቤቱ ሠራተኞች ተጣበው ይቀመጡባታል። ባለሞያዎቹ የዚያች የአትሌቲክስ ምንጭ የሆነችውን የበቆጂ ስፖርት ልማትንም ይመራሉ። በውስጧም በስኬታማ አትሌቶች ምስል ተሽቆጥቁጣለች። በስፖርት ውድድሮች የተገኙ በርካታ ዋንጫዎችም ይገኙበታል ።
በበቆጂ ስፖርት ጽ/ቤት ውስጥ የተከማቹ ዋንጫዎች
በአነስተኛዋ የበቆጂ ስፖርት ጽ/ቤት ውስጥ ያሉት እነዚህ ዋንጫዎች በበቆጂ ከተማ በተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች የተገኙ ናቸው። በአትሌቲክስ ስፖርት ለምትታወቀው በቆጂ ከውስን ዋንጫዎች በስተቀር በርካታዎቹ የተገኙትም በአትሌቲክስ ስፖርት ውጤት ነው። የዋንጫዎቹ ግዝፈት እና የቤቷ ወቅታዊ ሁኔታ ግን ፍጹም አይመጣጠኑም።
አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ
የዓለም ዓቀፍ አትሌቲክስ በርካታ ድሎችና ክብረወሰኖች ባለቤት አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ የአትሌቶች ከተማ የሆነችው በቆጂ ስመ ጥር አትሌቶችን የማፍራት የስኬት ሰንሰለቷን ስለመግታቷ አውስቷል። ተፈጥሮ ባደለው አከባቢ ላይ ትኩረት ሰጥቶ አለመሥራት ስፖርቱን የጎዳው ትልቁ ምክንያት ነውም ይላል። በዓለም ድንቅ አትሌቶችን በማፍራት ዕውቅናን ያተረፈችው በቆጂ ውስጥ የስፖርት መሰረተ ልማት በማሟላት በርካታ ዓለም አቀፍ አትሌቶችን ለልምምድ እና ከተማዋንም ለቱሪዝም ሳቢ ማድረግ እንደሚቻል መክሯል።
የበርካታ ስመጥር አትሌቶች አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ
አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ ከ1976 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 38 ዓመታት በበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል አሰልጣኝነት እያገለገሉ ነው። ከአትሌት ደራርቱ ቱሉ እስከ ቀነኒሳ በቀለ፤ ጥሩነሽ ዲባባን ጨምሮ ስኬታማዎቹን የዲባባ ቤተሰቦች እንዲሁም በርካታ የበቆጂ ዙሪያ ስመ-ጥር አትሌቶችን አፍርተዋል።
አቶ ሳሙኤል ብርሃኑ
አቶ ሳሙኤል ብርሃኑ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስልጠና ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ናቸው። የኢትዮጵያ የረጅም ርቀት ሩጫ ውጤት ማሽቆልቆል ላይ ከበርካቶች የሚሰማውን ትችት የተሳሳተ ይሉታል። ኢትዮጵያ ውጤታማ አትሌቶችን የማፍራት ችግር የለባትም ይላሉ። ኢትዮጵያ ውጤታማ አትሌቶችን በአገራዊ ውድድሮች ላይ የመጠቀም ስልት መንደፍ ላይ ግን እንድታተኩር ይመክራሉ። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የዘርፉን ማነቆ ለመለየት የሚረዳ ጥናት በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ ከፕሮጀክት እስከ አካዳሚዎች ላይ ብርቱ ሥራ እንደሚያስፈልግም ያመለክታሉ።
አትሌት ሃና ጪምዲ
አትሌት ሃና ጪምዲ በበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል እየሰለጠነች ነው። አምና ማዕከሉን የተቀላቀለችው ይህች ወጣት አትሌት ለአራት ዓመታት ስልጠና በምትወስድበት ማዕከል የ800 ሜትር የሩጫ ውድድር ልምምድ በማድረግ ላይም ትገኛለች። አትሌት ሃና የአትሌት ደራርቱ ቱሉ አድናቂ ስትሆን፤ በሂደት በረጅም ሩጫ ተፎካካሪ ለመሆንም ታልማለች። ህልሟ አንድ ቀን እውን እስኪሆንም እንደ የዕድሜ እኩያዎቿ ሰልጣኞች ላቧን ጠብ አድርጋ በትጋት ትሰለጥናለች።
የቀድሞ የበቆጂ አትሌቶች የስልጠና ስፍራ በቤቶች ተከቧል
በቀድሞ የበቆጂ አትሌቶች የስልጠና ስፍራ ግን መኖሪያ ቤቶች እንደ እንጉዳይ ፈልተውበታል። ይህ ከቤቶቹ ባሻገር የምትመለከቱት የተራራ ጫፍ ፎርቲኖ ይባላል። ከተራራው ስር በአሁኑ ወቅት ቤቶች የተሠሩበት ስፍራ ደግሞ ቀደም ሲል ከበቆጂ የወጡ አትሌቶች ልምምድ የሚያደርጉበት ቦታ ነበረ። የቀድሞ ስመ ጥር አትሌቶች ከከተማ ብዙም ርቀው መሄድ ሳያስፈልጋቸው እዚህ ስፍራ ይለማመዱ ነበር። በስፍራው የነበረው ደን ተጨፍጭፎ ነው ቤቶቹ የተሠሩት።