1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“በቡግናና ዋግኽምራ በምግብ እጥረት ህፃናት እየሞቱ ነው” ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ

ሰኞ፣ ጥር 5 2017

በ4ቱም ጥናቱ በተካሄደባቸው የቡግና አካባቢዎች 10ሺህ 550 ህፃናት በመካከለኛ የርሀብ ደረጃ ላይ ሲገኙ፣እርዳታ የማይቀርብላቸው ከሆነ በፍጥነት ወደ ከፍተኛ የርሀብ ደረጃ እንደሚሸጋገሩ ሰነዱ ያስጠነቅቃል።ግኝቱ በቡግና ወረዳ 5 ህፃናት በርሀብ ህይዎታቸው ማለፉን ያሳያል። አጥኚዎቹ መረጃ በመስጠታቸው ዛቻና ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4p7Mu
Äthiopien IDPs in der Region Amhara
ምስል Alemenw Mekonnen/DW

“በቡግናና ዋግኽምራ በምግብ እጥረት ህፃናት እየሞቱ ነው” ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ከታህሳስ 10 እስከ ታህሳስ 15/2017 ዓ ም በሁለት ቡድን ባለሙያዎችን መድቦ  በሰሜን ወሎ ቡግና ወረዳና በዋግኽምራ ብሔረስብ አስተዳደር 4 ወረዳዎች ድርቁ ያስከተለውን ጉዳት በተመለከት ጥናቶችን ሲያካሂድ ቆይቶ የጥናቱን ውጤት ሰሞኑን ይፋ አድርጓል። ጥናቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ድርቅ መከሰቱና ሰዎች ለከፋ ይምግብ እጥረት መጋለጣቸውንና ህፃናት መሞታቸውን መረጋገጡን የጥናት ቡድኑ አባላት ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

ህጻናትና እናቶችን ለከፋ ችግር የዳረገው የሰሜን ወሎ ቡግና ወረዳው የምግብ እጥረት

መረጃ ለተለያዩ አካላት በመስጠታቸው ዛቻና ማስፈራሪያ ከተለያዩ አካላት እንደደረሰባቸው የሚግልጡት የአጥኚ ቡድኑ አባላት፣ በዚህ ዘገባም ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ ቆብ፣ ብርኮ፣ አይና ቡግናና ቅዱስ ሐርቤ በተባሉ አካባቢዎች ጥናቱ መካሄዱን የነገሩን አንድ የጥናት ቡድኑ አባል፣ በአራቱም አካባቢዎች 954 ህፃናት በከፍተኛ የምግብ እጥረት (Severe Acute Malnutrition (SAM) በሚባለው ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

“3ሺ 437 ህፃናት ለከፋ ርህብ ሲጋለጡ 23 ህይወታቸው አልፏል” የዳሰሳ ጥናት

የጥናት ሰነዱ እንደሚያመለክተው ደግሞ በአጠቃላይ በ4ቱም ጥናቱ በተካሄደባቸው የቡግናአካባቢዎች 10ሺህ 550 ህፃናት በመካከለኛ የርሀብ ደረጃ ላይ (Moderate Acute Malnutration (MAM)) ያሉ ሲሆን እርዳታ የማይቀርብላቸው ከሆነ በፍጥነት ወደ ከፍተኛ የርሀብ ደረጃ እንደሚሸጋገሩ ሰነዱ ያስጠነቅቃል። የጥናት ግኝቱ  በቡግና ወረዳ 5 ህፃናት በርሀብ ህይዎታቸው ማለፉን ያሳያል።

ጥናቱ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ፣ ፃግብጂ፣ ዳህናና ጋዝጊብላ ወረዳዎች የተካሄድ ሲሆን ጥናቱ እንድሚያሳየው በወረዳዎች ከሚኖረው አጠቃላይ 240ሺህ ያክል ነዋሪ 170ሺህ የሚሆኑት ነዋሪዎችና አርሶአደሮች ለክፍተኛ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ናቸው።

በዚህ የዳሰሳ ጥናት የተሳተፉት ባልሙያ በሰጡን ተጨማሪ አስተያየት ጥናቱ በተካሄደባቸው 4ቱ የዋግኽምራ ወረዳዎች፣ 26ሺህ 653 እናቶችና ህፃናት  ለርሀብ የተጋለጡ ናቸው። ከነዚህ መካከል 3ሺህ 437 ህፃናት በከፋ ርሀብ (Severe Acute Malnutrition (SAM)) በሚባለው የርሀብ ደረጃ ላይ ናቸው ነው ያሉት። 18 ህፃናትም ከምግብ እጥረቱ ጋር በተያያዘ ህይዎታቸው ማለፉ በጥናቱ መረጋገጡን ተናግረዋል።

Äthiopien Tefera Hailu Memorial Hospital
ምስል Mebratu Mekonnen

የጤና፣ የመድኃኒትና የምግብ እጥረቱ የከፋ ስለመሆኑ

የጤና ግብዓቶችና የምግብ አቅርቦት ችግሮች በስፋት እንደሚታዩ የሚናገሩት የአጥኚ ቡድን አባላቱ፣ ለችግሩ ትኩረት እንዲሰጠውና በችግር ላይ ያሉ ወገኖችን ከሞት ለመታደግ መንግሥትና መንግሥታዊ ያለሆኑ አካላት ሳይውሉ ሳያድሩ እንዲረባረቡ ይጠይቀዋል።

ህጻናትና እናቶችን ለከፋ ችግር የዳረገው የሰሜን ወሎ ቡግና ወረዳው የምግብ እጥረት

በተለይ ባለፈው ክረምት ጋር ተያይዞ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ጉዳቶች መድረሳቸውን የጠቆመው የጥናቱ አባላት፣ ጥናቱ በተደረገባቸው 4ቱ ወረዳዎች 40ሺህ ሄክታር ማሳ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን 237 ሺህ ኩንታል የሚገመት ሰብል ወድሟል፣ በ4ቱ ወረዳ 337 እንሣትም በጎርፍና በድርቅ መሞታቸውን ጥናቱ ያሳያል።

ለስሜን ወሎ ዞን አድጋ መከላክለና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዓለሙ ይመር በተድጋጋሚ ደውለን ተጨማሪ አስተያየት እንዲሰጡን ብንጠይቀም “መልሼ እደውላልሁ” ካሉ በኃላ ሊደውሉ አልቻሉም፣ መልሰን ብንደውልም አያነሱም፡፡ ይሁን እንጂ ሰሞኑን ለዞኑ ኮሙዩኒኬሽን በሰጡት መግልጫ “ በቡግ ና ወረዳ 169 ሺህ ኩንታል እህል ለ113ሺህ ሠዎች ማሰራጨት ቢቻልም ሆኖም እየቀረብ ያለው እርዳታ በቂ አይደለ” ብለዋል።

የጥናት ግኝቱን በተመለከት ምላሽ እንዲሰጡን ለዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አድጋ መከላክለና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ፣ እንዲሁም ለቡግና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጌትዬ ካሳሁን ደውልን “ጥናቱን አላየነውም” የሚል ምላሽ ስጥተዋል።

ዓለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ