በትግራይ የኤርትራውያን መጠለያ ሊዘጋ ነው መባሉ
ሰኞ፣ የካቲት 30 2012በኢትዮጵያ የሚገኘው ኤርትራውያን ስደተኞችን የሚያስተናግደው ሕንፃፅ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ እንዲዘጋ መወሰኑ ተነገረ፡፡ በመጠልያ ካምፑ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ኤርትራውያን ስደተኞች በአስር ቀናት ውስጥ መጠልያው ለቀው እንዲወጡ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር በኩል እንደተነገራቸው ለዶቼቨሌ ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከሚገኙ ስድስት ኤርትራውያን ስደተኞች ከሚያስተናግዱ መጠለያ ጣብያዎች መካከል አንዱ የሆነው በትግራይ ክልል ሽረ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው ሕንፃፅ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ከሰባት ዓመት በፊት ተቋቁሞ 18 ሺህ ገደማ ኤርትራወውያን ስደተኞች እያስተናገደ የሚገኝ ማእከል ነው፡፡
በስደተኞች መጠልያ ጣብያው ሕንፃፅ የሚኖሩ ኤርትራውያን እንደሚሉት ባለፈው ዕለተ ሐሙስ ነበር የሚኖሩበት መጠልያ እንደሚዘጋና በአስር ቀናት ውስጥ ቦታ እንዲቀይሩ የተነገራቸው፡፡
በሕንፃፅ የስደተኞች መጠለያ ጣብያ የሚኖር ኤርትራዊ ስደተኞ ሓዱሽ ታደለ እንደሚለው በኢትዮጵያ መንግስታት የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር በኩል የመጣው ይኽ ውሳኔ በካምፑ የሚኖሩ በርካታ ስደተኞችን ያሳዘነ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ የስደተኞቹ ተወካዮችም ውሳኔው ከተነገረ በኋላ ከUNHCR ተወካዮችና ከትግራይ ክልል የአስተዳደር አካላት ጋር ትላንት መወያየታቸው ጠቅሶ መጠልያው እንደሚዘጋ አስቀድሞ የተነገራቸው ነገር አለመኖሩ መረዳታቸው የሕንፃፅ ስደተኞች መጠለያ ነዋሪው ሓዱሽ ታደለ ነግሮናል፡፡
18 ሺህ ገደማ ኤርትራውያን የሚኖሩበት ሕንፃፅ የስደተኞች መጠለያ ጣብያ ይዘጋል የተባለው ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ ምክንያት መሆኑ አንድ ስሙ መጥቀስ ያልፈለገ በጣቢያው የሚሰራ የአንድ ውጭ ድርጅት ተቀጣሪ ይገልፃል፡፡ ይሁንና ስደተኞቹ ወደ ማይዓይኒ እና ዓዲሓርሽ የተባሉ ሌሎች በአቅራቢያው የሚገኙ መጠልያዎች ለመቀየር ሀሳብ መኖሩ መረዳቱ ጨምሮ ይገልፃል፡፡
ኤርትራውያን ስደተኞቹ ግን ሕንፃፅ መጠለያ ካምፕ ለመዝጋት የተፈለገው በኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስታት የውስጥ ስምምነት ሊሆን እንደሚችል ይጠረጥራሉ፡፡ ሕንፃፅ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ወደ ኤርትራ ድንበር የቀረበ በመሆኑ በርካታ ድንበር አቋርጠው የሚጓዙ ስደተኞች ወደ ካምፑ ለመግባት ተስፋ አድርገው ከሀገራቸው እንደሚወጡ ያስረዳሉ፡፡
በዚህ ጉዳይ ዙርያ የኢትዮጵያ መንግስት የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር የስራ ሐላፊዎች ለማነጋገር በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
የትግራይ ክልል መንግስት ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ፣ የተቋቋሙ የስደተኞች መጠልያ ጣብያዎች እንዲዘጉ መንግስታት "እያሴሩ ነው" ሲል ሲከስ ቆይቷል፡፡ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል 45ኛ ዓመት የህወሓት ምስረታ የካቲት 11 በሚከበርበት ወቅት ባደረጉት ንግግር "ማነኛውም ሐይል" የኤርትራ ስደቸኞች መጠለያ ጣብያዎች መዝጋት አይችልም ሲሉ ገልፀው እንደነበረ ይታወሳል፡፡
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ