1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፍሪቃ የሞባይል ገበያ አትራፊ የሆነችዉ ቻይና

ዓርብ፣ ጥቅምት 14 2012

አፍሪቃ የተንቀሳቃሽ ስልክ ከፍተኛ ግብይትና የቻይና የስልክ አምራች ኩባንያን ከፍተኛ ገቢ እያስገኘለት ነዉ ተባለ።   77 በመቶዉ ሕዝብ ከ 35 ዓመት በታች በሆነበት በአፍሪቃ አሕጉር አብዛኛዉ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ ወጣቱ መሆኑም ተገልፆአል።

https://p.dw.com/p/3Rxz2
Kenia Warten auf  Papst Franziskus in Nairobi
ምስል picture-alliance/AP Photo/B. Curtis

በ2018ዓ.ም ብቻ 124 ሚሊዮን ሞባይል ወደ አፍሪቃ ገብቶአል

በተለያዩ አፍሪቃ ሃገራት የተንቀሳቃሽ ስልክ ፍላጎት ከጊዚ ወደጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነዉ። በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ በአፍሪቃ አህጉር ብቻ 900ሚሊዮን ተንቀሳቃሽ ስልኮች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። የአፍሪቃ ሃገራት በግዢ ወደ ሃገራቸዉ በገፍ ከሚያስገቡት ተንቀሳቃሽ ስልኮች በመጀመርያ ደረጃ ተጠቃሚዎቹ የቻይና ስልክ አምራች ኩባንያዎች ሲሆኑ በሁለተኛ ደረጃ ከቻይና ወደ አፍሪቃዉያኑ ሃገራት የሚገቡትን ስልኮች ተቀብለዉ የሚሸጡ የአፍሪቃዉያን የሽያጭ ድርጅቶች ናቸዉ።
የ35 ዓመቱ የጊኒቢሳዎ ተወላጅ ላፉ ባልዴ ስራዉ በመዲና ጊኒቢሳዉ ጎዳና ላይ ነዉ። ባልዴ የሚተዳደረው ለዉጭ ሃገር ዜጎች ገንዘብ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ በመመንዘር ነው። አንዳንዴ ስራዉ ቀዝቀዝ ሲልበት ለባለሱቆች በመላላክም ገንዘብ ያገኛል።    
« ያለ ተንቀሳቃሽ ስልክ ሕይወቴ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ይከብደኛል። እዚህ ጊኒቢሳዎ ከሚገኙ የገበያ ደንበኞቼ ጋር ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ካሉ ዘመዶቼ ጓደኞቼ ጋር የምገናኘዉ በዚሁ በተንቀሳቃሽ ስልኬ ነዉ። መብራት፣ ዉኃ እና ዳቦ እንደሚያስፈልገኝ ሁሉ ተንቀሳቃሽ ስልኬም ለእኔ አሁን እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነዉ።»
የጥናት መዘርዝር እንደሚያመለክተዉ በአፍሪቃ አህጉር 77 በመቶው ሕዝብ ከ 35 ዓመት እድሜ በታች ነዉ። ከዚህ ሕዝብ መካከል ደግሞ አብዛኛዉ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ ሆኗል። 
« ለምሳሌ በባንክ የምናዛዉረዉ ገንዘብ አልያም መክፈል ያለንን ሂሳብ ተንቀሳቃሽ ስልካችን በመጠቀም እንከፍላለን ። አልያም የስልክ ካርድ ገዝተን ገጠር አልያም ከከተማ ራቅ ብለዉ ለሚኖሩት ዘመዶቻችን፣ ጓደኞቻችን በአጭር መልዕክት ወደ ስልካቸዉ በመላክ ገንዘብ እንዲሞሉ ማድረግ እንችላለን። ስልካችንን ለሁሉ ነገር ግልጋሎት ይሰጠናል።» 
በሃገሪቱ ባሉ የተለያዩ ዩንቨርስቲዎች ቅጽር ጊቢ ዉስጥ ያለዉን የገመድ አልባ የኢንተርኔት አገልግሎት (ዋይፋይ) ተጠቅሞ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቶች እና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ደብዳቤም ሆነ የክፍት ስራ ቦታ ማመልከቻን መላክ ይቻላል። የቻይና የተንቀሳቃሽ ስልክ ምርት በአፍሪቃ የስማርት ስልኮች ገበያን ለማስፋፋት ከባድ ቢሆንም ጥቂት የተንቀሳቃሽ ስልክ ድርጅቶች የአፍሪቃዉያኑን የተንቀሳቃሽ ስልክ ፍላጎት ለማሟላት እየጣሩ ነዉ። «ትራንሽን» የተሰኘዉ የቻይናዉ የተንቀሳቃሽ ስልክ አቅራቢ ድርጅት በአለፉት አስር ዓመታት አፍሪቃ ዉስጥ በሸጠዉ ተንቀሳቃሽ ስልክ በአህጉሪቱ የመጀመርያዉን ስፍራ ይዟል። ድርጅቱ በአፍሪቃ የስልክ ገበያ መድረክ ካቀረባቸዉ የስልክ አይነቶች መካከል፤ «ቴክኖ» «ኢቲል» እንዲሁም «ትራንሽን» የተሰኙ መጠሪያ እንዳላቸዉ እና ባለፉት አስር ዓመታት በአፍሪቃ አህጉር ከ130 ሚሊዮን በላይ ስልኮችን መሸጡን ይፋ አድርጓል።     
«እኔ ራሴ ትራንሽን የተባለዉን ተንቀሳቃሽ ስልክ የገዛሁት በቅርቡ ነዉ» የሚለዉ የጊኒቢሳዊዎ ተወላጁ ላፉ ባልዴ «በአፍሪቃ ለሚገኙ ወጣቶች የሚያስፈልገን ነገር ቢኖር ተንቀሳቃሽ ስልክ ብቻ ነዉ» ይላል።  ላፉ ስልኩን የገዛዉ ወደ 76 ዩሮ  አዉጥቶ ነዉ። በስልኩ ላይ ታዋቂዎቹ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እንደ «ፌስቡክ»፣ «ዋትስ አፕ»፣ «ትዊተር» እንዲኖሩት መተግበሪያዎችን ሁሉ ጭኖአል።  
ስልኩ እጅግ ጥሩ እና የኤሌትሪክ ኃይልንም ለቀናቶች እንደሚቆጥብ በኩራት ይናገራል። «ስለዚህም» ይላል «በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድንገናኛ ቻይናዉያኑ የተንቀሳቃሽ ስልክን በቀላሉ ስላቀረቡልን ላመሰግናቸዉ እወዳለሁ»። «ትራንሽን» የተባለዉ የቻይናዉያኑ ተንቀሳቃሽ ስልክ ምርት ሁለት ሲም ካርዶችን የሚቀበል ብሎም አፍሪቃዉያን የሚጠቀሙበትን የቋንቋ ፊደላትንም የያዘ በመሆኑ በወጣት አፍሪቃዉያን ዘንድ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ መሆኑን ተናግሯል።   
ከጊኒቢሳዎ ቀጥሎ ሴኔጋል ብሎም በሕዝብ ብዛት አንደኛ በሆነችዉ ናይጀርያም የቻይናዉያኑ ተንቀሳቃሽ ስልክ «ትራንሽን» በተለይ በመካከለኛ ኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኘዉ ማኅበረሰብ ዘንድ ተፈላጊነት እና ተወዳጅነትን አትርፏል። በኢትዮጵያም የእዚህ ስልክ ተጠቃሚ ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም። ስልኩ በአማርኛ ለመተየብ የሚያስችሉ ፊደላትን ይዞ ብቅ ካለም አስር ዓመታትን ማስቆጠሩ ተነግሮለታል።      
የዶይቼ ቬለዉ የቻይና ቋንቋ ስርጭት በቅርቡ እንደዘገበዉ ከሆነ ትራንዚሽን የተባለዉ የቻይና የተንቀሳቃሽ ምርት በአፍሪቃ ዉስጥ ከፈተኛ ተፈላጊነት እና ትርፍን አስገኝቶአል። የእዚህ ተንቀሳቃሽ ስልክ ኩባንያ ባለፈዉ አንድ ወር ብቻ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ግድም ገቢን አስገኝቷል። የቻይናዉ ኩባንያ ይህን የተንቀሳቃሽ ስልክ ምርቱን ወደ አፍሪቃ ማስገባት የጀመረዉ በጎርጎረሳዉያኑ 2008 ዓ.ም እንደሆነም የዶቼ ቬለዉ የቻይና ቋንቋ ስርጭት ክፍል በዘገባዉ አሳይቷል። ኩባንያዉ ከሰሃራ በታች ላሉ ሃገራት በጎርጎረሳዉያኑ 2018  ወደ 124 ሚሊዮን ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ልኮአል ይህ ማለት በአፍሪቃ አህጉር 50 በመቶ ያህሉን የተንቀሳቃሽ ስልክ ሽያጭ የቻይናዉ የትራንዚሽን የተንቀሳቃሽ ስልክ ኩባንያ እንደተቆጣጠረዉ ያመላክታል። ይህን ተከትሎ ቻይናዊዉ የኮምፒዉተር ሥራ ምሁር ዋንግ ታንግ ለዶይቼ ቬለ በሰጠዉ ቃለምልልስ የቻይናዉ ተንቀሳቃሽ ስልክ አምራች ኩባንያ «ትራዚሽን» ርካሽ የገበያ አቅርቦት ጠንካራ ገቢ ማግኛ ስልቱ ነዉ ብሎአል። 
«ማራ የተሰኙት ተንቀሳቃሽ ስልኮች «በጉግል»  «አንሮይድ» ስርዓተ ክወና ላይ የተመሠረተ የማህበራዊ ሚዲያ ማቅረቢያዎቹም ከአፍሪካውያን ተጠቃሚዎች ፍላጎት ጋር የሚስማ ነው ፡፡ ዓመታዊው ምርት አሁንም በ 1.2 ሚሊዮን ስልኮችን ያቀርባል። በዚህም የማራ ተፈላጊነትን በጣም ከፍተኛ ያደርገዋል ፡፡ በስልክ ቴክኒክ ስራ ላይ ከአፍሪቃ ከፍተኛ እንቅስቃሴን በማድረግዋ የምትታወቀዉ ሩዋንዳ በዚህ የተንቀሳቃሽ ስልክ የቴክኒክ ስራ ላይ ሚናን ተጫዉታለች። የሩዋንዳ የልማት ሚኒስትር ክላራ ካሚኒዚ ለዶይቼ ቬሌ እንደገለፁት የሩዋንዳን መንግስት ከመጀመሪያው ጀምሮ በንቃት የደገፈዉ የስልክ ቴክኖሎጂ ነዉ። 

Symbolbild - Handys in Afrika
ምስል Getty Images
Afrika | Mara Smartphone in Ruanda
ምስል Reuters/J. Bizimana
Afrika | Mara Smartphone in Ruanda
ምስል Reuters/J. Bizimana
Universität Lagos, Nigeria
ምስል AFP/Getty Images/S. Heunis

«ማራ ተንቀሳቃሽ ስልክ የሕዝቡን ፍላጎት በማቅለሉ የሩዋንዳ መንግሥትን ትኩረት እንዲስብ አድርጎታል። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የዚህ ስልክ ተጠቃሚ 13 በመቶ የሚሆነዉ ሩዋንዳዊ ብቻ ነዉ፡፡ ሆኖም የተንቀሳቃሽ ስልክ ቴክኒክ ግንባታን በማነቃቃት እና ዲጂታል ለውጥን በማበረታታት ትልቅ ደረጃን መያዝ እንፈልጋለን» የስማርት ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ክንዉን ዲጂታል ግንባታን በተመለከተ «የአፍሪቃ ስሪት» ማለት «ሚድ ኢን አፍሪቃ » የሚል ስልክን ማየት በሌሎች አፍሪቃ ሃገራትም ያለዉ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ ይታያል። የጊኒቢሳዎ ተወላጁ ላፉ ባልዴ እንደሚለዉ «እኔ እዚህ ጊኒቢሳዎ ብሆንም  ከኪጋሊ ስለአዲሱ የተንቀሳቃሽ ስልክ ስሪት መስማቴ አስደንቆኛል አኩርቶኛልም»  ሲል ተናግሯል። «ይበልጥ የምኮራዉ ደግሞ ይላል»  በመቀጠል «ሙሉ በሙሉ በአፍሪቃ የተመረተ ስልክ መኖሩን ስሰማ ነዉ»። እንዲያም ሆኖ በዲጂታል ስራዉ ሩዋንዳ የተካፈለችበት የማራ ተንቀሳቃሽ ስልክ ዋጋዉ ወደ 130 ዩሮ ነዉ። የጊኒቢሳዎ ተወላጁ ላፉ ባልዴ ከሚጠቀምበት ከቻይናዉ ተንቀሳቃሽ ጋር ሲያነፃፅረዉ ግን ዋጋዉ ተወዶበታል።

አዜብ ታደሰ 
ተስፋለም ወልደየስ