1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቻይናውያን በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 1 2011

ከቻይና የሚገኝ ገንዘብ የአፍሪቃን ኤኮኖሚ አነቃቅቷል። ይሁን እንጂ፣ አንዳንድ በአህጉሩ የሚሰሩ ቻይናውያን ለአፍሪቃውያን የሚያሳዩት አመለካከት በአፍሪቃውያን ዘንድ ቅሬታ አስከትሏል።

https://p.dw.com/p/37yII
Uganda chinesicher und ugandesicher Bauarbeiter auf der Baustelle des Entebbe-Kampala-Autobahn-Projekts
ምስል picture-alliance/Photoshot/Zhang Gaiping

«ቻይናውያኑ ለአፍሪቃውያኑ ክብር አልባ ናቸው።»

በአፍሪቃ የቻይና ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ዋነኛዋ የአፍሪቃ አጋር ሆናለች። አህጉሩ የመሰረተ ልማቱን ለማስፋፋት ፣ ማለትም፣ መንገዶች፣ ሀኪም ቤቶች፣ ስታድየሞች ወይም የኃይል ማመንጫ ተቋሞች ግንባታ የሚያስፈልገው  ገንዘብ አዘውትራ ስታቀቀርብ ትታያለች።  እነዚህን ግዙፍ ፕሮዤዎች በመገንባቱ ስራ ላይ ከሚሳተፉት ሰራተኞች መካከል ብዙዎቹ ቻይናውያን ናቸው። እነዚህ ሰራተኞችም ሙያቸውን ብቻ ሳይሆን የሀገራቸውን  ባህላዊ እና ፖለቲካዊ አመለካከትም ጭምር ይዘው ነው ወደ አህጉሩ የሚመጡት። ይህም አዘውትሮ በአፍሪቃውያን እና በቻይናውያኑ መካከል ውዝግብ እንዲነሳ ምክንያት እየሆነ ተገኝቷል። በቻይናውያን ድጋፍ በተነቃቁ ፕሮዤዎች ውስጥ የሚሰሩ አፍሪቃውያን ለአድልዎ እንደተጋለጡ የሚወጡ ዘገቦች ያሳያሉ።

ሌሎች እሴቶች፣ ሌላ አመለካከት


ቻይና በአፍሪቃ በምታደርገው ውረታ እውን ከሆኑ ግዙፍ ፕሮዤዎች መካከል በኬንያ የተገነባው የባቡር መስመር አንዱ ነው። የባቡሩ መስመር ካለፈው አንድ ዓመት ገደማ ወዲህ ትልቁን የሞምባሳ ወደብ ከመዲናይቱ ናይሮቢ ጋር አገናኝቷል።  ይህ ፕሮዤ ኬንያ በጎርጎሪዮሳዊው 1963 ዓም ነፃነቷን ከተጎናጸፈች ወዲህ የተከናወነ ትልቁ መሰረተ ልማት ነው። 
ይሁን እንጂ፣ ይኸው የመሰረተ ልማት ፕሮዤ ከዘረኝነት ጋር በተያያዘ ወቀሳ ተደጋግሞ ሲነሳ ይሰማል። ኬንያውያን ጋዜጠኞች ሰራተኞችን በማነጋገር ባደረጉት ምርመራ፣ በሰራተኞቹ የእረፍት ጊዜ ቻይናውያኑ የፕሮዤው ተሳታፊዎች ከአፍሪቃውያኑ ባልደረቦቻቸው ጋር አብረው መቀመጥ እንደማይፈልጉ ደርሰውበታል፣ አፍሪቃውያኑ ሰራተኞች በቻይናውያኑ መሰደብ እና መዋረድ የእለት ከእለት እጣቸው ሆኗል።
ቻይናውያን በአፍሪቃውያኔ አኳያ ይፈጽሙታል ለሚባለው አድልዎ ምክንያቱ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለው ባህላዊ ልዩነት እንደሆነ የሀገራት ባህላዊ ግንኙነት እና ልዩነትን በተመለከተ ስልጠና የሚሰጡት ኬንያዊቷ ወይዘሮ ኤሊዛቤት ሆርለማን ለ«DW» አስረድተዋል። 
« እኛ የራሳችን ህብረተሰብ ልማድ ነው የምንከተለው። ለእኛ ቅድሚያ የሚይዘው እኔ የሚለው ሳይሆን እኛ የሚለው አስተሳሰብ ነው። ቻይናውያኑ ደግሞ የሚከተሉት የራሳቸውን ፖለቲካ፣ ርዕዮተ ዓለም ነው። ይህን አለማወቅ ታድያ በአፍሪቃ የውዝግብ መንስዔ እየሆነ መጥቷል። »
እንደ ኤሊዛቤት ሆርለማን አስተያየት፣ የስራ ባህልን በተመለከተ በቻይናውያን እና አፍሪቃውያን መካከል ልዩነት አለ።
« ቻይናውያን ካለእረፍት የመስራት፣ ከአለቃ ወይም ከፓርቲ የሚመጣ ትዕዛዝን ተቀብሎ የመፈጸም ልምድ አላቸው። ግን አፍሪቃውያኑ ምናልባት የማይገነዘቡት አንድ ነገር ቻይናውያኑ የፍርሀት ኑሮ እንደሚመሩ ነው። »
በግዙፎቹ የመሰረተ ልማት ፕሮዤዎች ውስጥ የተሰማሩት ቻይናውያን፣ ለምሳሌ በማዕድን ማውጫ ተቋማት ውስጥ አዘውትሮ በሚታይ  እጅግ አስከፊ የስራ ሁኔታ መስራት የሚገደዱበት ሁኔታም ሌላ የውዝግብ መነሻ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኝ ስቲቭ ሳንግ  ገልጸዋል። በብሪታንያ የለንደን የእስያ እና የአፍሪቃ ጥናት ተመራማሪ ትምህርት ቤት ውስጥ የቻይና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሳንግ እንደሚገምቱት፣ በቻይና የሚሰጠው የፖለቲካ ትምህርት በአፍሪቃ የሚሰሩ ቻይናውያኑ በአህጉሩ ዜጎች አኳያ ይከተሉታል በሚል ለሚወቀጡበት የአድልዎ አሰራር ሚና ሳይኖረው አልቀረም።
« የቻይና መንግሥት በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ባህሎች መቀየጥ አስተሳሰብን አይደለም እያራመደ ያለው። በአንጻሩ አንድ የቻይና ማንነትን ነው ለማጠናከር ነው እየሰራ ያለው። እና ስለ አንድ ቻይና ማንነት፣ ስለ ቻይና ስልጣኔ፣ ስለቻይና ባህል ተደጋግሞ የሚነገርህ ከሆነ፣ ይህ የዘረኝነትን አስተሳሰብ እንድትይዝ ያደርግሀል ማለት ነው፣ ይህ ዘረንነት ደግሞ የአድልዎ አሰራር መሰረት ነው። »
ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ቻይና በዓለም በብዛት አንድ ዓይነት ህዝብ የሚኖርባት ብቸናዋ ሀገር ናት። ከ1,3 ቢልዮን ቻይና ህዝብ መካከል 92% የሀን ቻይናውያን ብሔረሰብ አባላት ናቸው። 0,4% ብቻ ናቸው ከቻይና ውጭ የተወለዱት።

Chinesen bauen Straßen in Kenia
ምስል picture alliance/Photoshot
Kenia chinesische Investitionen in die Eisenbahnstrecke Mombasa-Nairobi
ምስል Reuters/N. Khamis

የአፍሪቃውያን መንግሥታት ዝምታ


በአህጉሩ የሚያፈሱት ወረት በቀላሉ የማይገመት በመሆኑ የተነሳ አንዳንድ አፍሪቃውን መንግሥታት በአፍሪቃ የሚሰሩ ቻይናውያን ለአፍሪቃውያኑ ክብር አልባ ናቸው በተባሉበት ሁኔታ አንጻር ርምጃ መውሰድ እንደሚያመነቱ ኤሊዛቤት ሆርለማን ጠቁመዋል። በመንግሥታቸው ቅር የተሰኙ ብዙ ኬንያውያን መንግሥታቸው ሀገራቸውን ለቻይናውያን የሸጠ ያህል እንደሚሰማቸው ነው የሚሰማቸው።
የቻይና መንግሥትም ቢሆን ዜጎቹ በአፍሪቃ ይፈጽሙታል በሚባለው ዘረኝነትን መሰረት ያደረገ በደል ያን ያህል ርምጃ ሲወስድ አይታይም። ይህ ግን የፖለቲካ ተንታኙ ስቲቭ ሳንግ አላስገረማቸውም።
« የቻይና መንግሥት በወቅቱ ትኩረት የሰጠው ከአፍሪቃውያን መንግሥታት ጋር ለሚያደርገው የንግድ ግንኙነት ነው፣ የንግዱ ግንኙነት ከሚያስገኘው ጥቅም ጎን በሰበቡ በሚፈጠረው መዘዝ ችግር እያጋጠመው ላለው ተራ ሰው ደንታ የለውም፣  ይህን ለአፍሪቃውያኑ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ነው የተዉት። » 

Südsudan Ausländische Arbeiter Chinesen
ምስል picture-alliance/Imaginechina/Tong Jiang

ግኝኙነት በመፍጠር የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት

የችግሩ ገፈት ቀማሾች ተራ አፍሪቃውያን ሰራተኞች ናቸው።  እንደ ስቲብ ሳንግ አስተያየት፣ አፍሪቃውያኑ ሰራተኞች ከቻይናውያኑ በሚደርስባቸው አድልዎ አንጻር ምን ዓይነት ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው አዘውትረው አያውቁም።  ይሁን እንጂ፣ አፍሪቃውያን ሰራተኞች በቻይናውያን የሚደርስባቸውን በደል እንደሚደርስባቸው በብዛት የሚናገሩ ከሆነ ምናልባት ቻይናውያን አስተሳሰብ ላይ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ተስፋ አድርገዋል። ይህ ዓይነቱ የአስተሳሰብ ለውጥ እውን ሊሆን እንደሚችል በደቡብ ቻይና የሚኖሩ አፍሪቃውያን ተሞክሮ አሳይቷል። በይፋ የመንግሥት ዘገባ መሰረት፣ በግዋንዡ ከተማ  16,000 አፍሪቃውያን ይኖራሉ። በእስያ ትልቁ መሆኑ የሚነገርለት ይህ የአፍሪቃውያን ማህበረሰብ አሁንም በቻይና በስፋት ስለሚታየው የዘረኝነት ጉዳይ  ከቻይናውያን  ጋር እየተገናኙ በግልጽ በመወያየት ሀሳብ በመለዋወጥ ችግሩን ለመቀነስ ጥረት ጀምረዋል።
 

አርያም ተክሌ/ማርቲና ሺቭኮቭስኪ