1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ

ሐሙስ፣ መጋቢት 29 2014

መልዕክቴ በኢትዮጵያዊነት ኮርቶ መኖር ነዉ። ሌላ ነገር ማፈላለግ አያስፈልግም። እኔ አርመን ነኝ ኢትዮጵያዊም ነኝ። እኔ ራሴን ሳስተዋዉቅ የኢትዮጵያ አርመን ነኝ ብዬ ነዉ የምጠራዉ። ኢትዮጵያን ነዉ የማስቀድመዉ። ሁሉም እንዲህ ማድረግ አለበት ብዬ ነዉ የማምነዉ

https://p.dw.com/p/49dBE
Äthiopien | Vartkes Nalbandian "I Want To Die With A Flag"
ምስል Vartkes Nalbandian

«መልዕክቴ በኢትዮጵያዊነት ኮርቶ መኖር ነዉ።» ቫርትኬስ ናልባንድያን

«መልዕክቴ በኢትዮጵያዊነት ኮርቶ መኖር ነዉ። ሌላ ነገር ማፈላለግ አያስፈልግም። እኔ አርመን ነኝ ኢትዮጵያዊም ነኝ። እኔ ራሴን ሳስተዋዉቅ የኢትዮጵያ አርመን ነኝ ብዬ ነዉ የምጠራዉ። ኢትዮጵያን ነዉ የማስቀድመዉ። ሁሉም እንዲህ ማድረግ አለበት ብዬ ነዉ የማምነዉ»

Äthiopien | Vartkes Nalbandian "I Want To Die With A Flag"
ቫርትኬስ ናልባንድያን ምስል Vartkes Nalbandian

ቫርትኬስ ናልባንድያን ይባላሉ፤ በቅርቡ «ባንዲራ ሳይኖርኝ እንዳልሞት» በሚል ርዕስር ከንቱ ህልም እና ሰቀቀናቸዉን በመጸሐፍ መልክ ከትበዉ ለአንባብያን ካቀረቡ በኋላ በኢትዮጵያዉያን ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን ተቸረዋል። ከአርመን እናት እና አባት ኢትዮጵያ ዉስጥ ተወልደዉ ያደጉት የ 75 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ-አርመን ቫርትኬስ ናልባንድያን፤ ኢትዮጵያዊ የሚል የዜግነት መታወቅያን ሲያገኙ ብሔር በሚለዉ አወዛጋቢ መለያ ስር  አማርኛ በመናገራቸዉ ብቻ አማራ ተብለዉ ተሰይመዉም እንደነበር አንዴ በቀልድ ሌላ ጊዜም ከንቱ እሳቤ መሆኑን በማሳየት በድምፅ አልባዉ የሰዉነት እንቅስቃሴ ያሳያሉ። ባንዲራ ሳይኖረኝ እንዳልሞት በሚለዉ መጽሐፋቸዉ ታሪክን ያስታዉሳሉ። አንዲት ሙሉ እድምያቸዉን በኢትዮጵያ የኖሩ፤ የእድሜ ባለፀጋ አርመን ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየታቸዉ ጥቂት ወራት በፊት የኢትዮጵያ ዜግነት እንዲሰጣቸዉ ለኢሚግሬሽን ቢሮ በድጋሚ አመልክተዉ፤ ሲመላለሱ መንቀሳቀስ እንኳ እንደተሳናቸዉ የታዘበዉ የኢሚግሬሽን ክፍል ቢሮ አንድ ኃላፊ በሁኔታዉ ተደንቆ፤ «እማማ ግን ይህ ዜግነት ምን ያደርግሎታል ?» ሲል ጠየቃቸዉ እማማም «ባንዲራ ሳይኖረኝ» ብለዉ መለሱለት ። እኝህ አረጋዊት  በህጻንነት እድሚያቸዉ በአርመን በደረሰዉ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እናት አባታቸዉን አጥተዉ በማያዉቁት አንድ ሰዉ ርዳታ፤ሊባኖስ ዉስጥ በሚገኝ እናት አባት በሌላቸዉ ማዕከል ተጥለዉ፤ በመጨረሻም በሙሽርነት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸዉን ቫርተኬስ ይተርካሉ።  እኝ ሴት በርጅና መምክንያት መራመድ እስኪያቅታቸዉ እስካለዉ እድምያቸዉ ድረስ ኢትዮጵያ ዉስጥ ኖረዉ እድምያቸዉን ሙሉ ዜግነት አልባ ሆነዉ መኖራቸዉ አጥንታቸዉ ድረስ ይሰማቸዉ እንደነበር ቫርተኬስ ናልባንድያን ተናግረዋል። አዛዉንቷ በመጨረሻ ህይወታቸዉን ሙሉ ሲመኙት የነበረዉን የኢትዮጵያ ባንዲራን አገኙ ፤ ኢትዮጵያዊነት፤ አዛዉንትዋ የኢትዮጵያ ዜግነትን እንዳገኙ የነበራቸዉ ኩራትና የትምክህት ስሜት በቃላት የሚገለፅም እንዳልነበር ቫርተኬስ ናልባንድያን እንዲህ ነግረዉናል።

Äthiopien | Vartkes Nalbandian "I Want To Die With A Flag"
ቫርትኬስ ናልባንድያን ያደጉበት እና በደርግ ዘመነ መንግሥት የተወረሰዉ አራት ኪሎ የሚገኘዉ ቤት ምስል Vartkes Nalbandian

«ባንዲራ የአንድ አገር መለያ ነዉ። በዚህ ምክንያት ነዉ ይህንን ያል ለመጽሐፍ ርዕሴ ያደረኩት። የእድሜ ባለፀጋዋ ሴት አነጋገር ልቤን ስለነካኝ ነዉ። አሮጊትዋ በዘጠና ምናምን ዓመታቸዉ ዜግነት ለመጠየቅ መሄዳቸዉ አስገርሞኝ ነዉ። «ልጄ ባንዲራ ሳይኖረኝ እንዳልሞት»ያሉት አነጋገር ሁኔታዉን በጣም ገላጭ የሆነ በመሆኑ ነዉ። በመፅሐፉ ጀርባላይ የሚታየዉ ፎቶ ስምጥ ሸለቆን ያሳያል። አካባቢዉ አርመኖች ኢትዮጵያ ዉስጥ ህይወታቸዉ ሲሻሻል በ 60ዎቹ ዉስጥ እንዲሁም  50ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በአብዛኛዉ የረፍት ጊዜያቸዉን የሚያሳልፉበት ቦታ ነበር። በዝያ መሰረት ሻላ፤ ላንጋኖ እንዲሁም ሃራ ሮምቢ ሶምቧይ የሚባል ቦታ መዝናኛ ስፍራ ነበር።  ይህን ቦታ አብዛኛዉ የኢትዮጵያ አዲስ ትዉልድ አያዉቀዉም።»

Armenier in Äthiopien 1903
በጎአ 1903 አርመናዉያን አዲስ አበባ ላይ የአፄ ምኒሊክን ምስል ይዘዉምስል Aramazt Kalayjian

አቶ ቫርትኬስ ናልናንዲያን መጽሐፎት በተለይ በዜግነት ጥያቄ ላይ ያተኩራል። በህመም ምክንያት ቁጭ በማለቶና በዛዉም ለማስበeያ ለመጫጫርያ ጊዜ ስላገኙ ታሪክን የመጻፍ ህልሞን ሀ ብለዉ እንዲጀምሩ ሆንዋል። የዜግነት ጥያቄ ምን ያህም አስፈላጊ ነዉ ይላሉ?

«የዜግነት ጥያቄ በጣም መሰረታዊ ነዉ። አንድ ሰዉ የሆነ ቦታ ይሄ የኔ ነዉ፤ ይሄ የኔ አገር ነዉ መቻል አለበት። በአርመኖች ታሪክ፤ የአርመኖች እድል ጥሩ አልነበረም። እኛ ከአገራችን ተባረን ተሰደን ነዉ የወጣነዉ። በሄድንበት በመካከለኛዉ ምስራቅም ቢሆን፤ በግብፅም ቢሆን በሱዳንም በኢትዮጵያም እንደ አገራችን አድርገን ቆጥረን ነዉ የኖርነዉ። ሀገሪቱ ዉስጥ የሰራነዉም የተንከባከብነዉም በዚህ እምነት ነዉ። እንደሚታወቀዉ አፄ ኃይለሥላሴ፤ ወደ ኢትዮጵያ ያመጥዋቸዉ እናት አባት የሌላቸዉ ከአርባ የአርመን ህጻናት መካከል ሦስቱ ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ከኢትዮጵያዉያን ጋር ሆነዉ የጣልያንን ወራሪ ኃይል ለመዉጋት ዘምተዋል፤ መስዋዕትም ሆነዋል። አርመኖች እንግዳ በሆኑበት ሀገር የሚያሳዩት ቁርቋሬ እስከዛ ድረስ ነበር። እኛ ራሳችን እንግዳ ብንሆንም፤ እንግዳ ነን ብለን አይደለም ራሳችን የምናየዉ። ስለዚህ  የዜግነት ጥያቄ በጣም መሰረታዊ ጥያቄ ነዉ። ዜግነት የአንድ ሰዉ መታወቅያ ነዉ፤ የአንድ ሰዉ መለያ ነዉ። የዜግነት አልባ መሆን በጣም አስቸጋሪ ነዉ።»

Äthiopien Vartkes Nalbandiani - Vorsitzender der hier lebenden Armenier
ቫርትኬስ ናልባንድያን ከባለቤታቸዉ ጋርምስል Vartkes Nalbandiani

ቫርትኬስ ናልባንድያን  በኢትዮጵያ ስለሚኖሩ አርመኖች ጉዳይ የዛሬ 10 ዓመት የባህል ዝግጅታችን እንግዳ ነበሩ። በዚሁ ዝግጅት ላይ፤ አፈሩ ይቅለላቸዉ እና አንጋፋዉ የኪነ-ጥበብ ሰዉ ጸሐፊ ተዉኔት ጌታቸዉ ደባልቄ አርመኖች ለኢትዮጵያ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ እንዲሁም አርባ ልጆች ከሚባሉት መካከል በቅርብ ስለሚያውቋቸዉ የሙዚቃ ባለሞያ ነርሲስ ናልባንድያንን የሚከተለዉን አጫዉተዉን ነበር።

«አርባ የአርመን ልጆች ወደ ኢትዮጵያ የመምጣታቸዉ ታሪክ፤ ግርማዊ ጃንሆይ፤ በአልጋወራሽነታቸዉ ፤ ከኢትዮጵያ ዉጭ ዉጭ ሀገርን በጎበኙበት ጊዜ እነዚህ የአርመን ህፃናት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ጠይቀዋቸዉ ነዉ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የበቁት። በሙዚቃ ኮርነት አገልግለዋል። ከዝያ መካከል በጣም የማዉቃቸዉ ኬቦርክ ናልባንድያን ናቸዉ። ከህፃናቱ መካከል ከሙዚቃዉ ዓለም ወጥተዉ ሌላ ህይወት የጀመሩም ብዙ ነበሩ። ከነርሲስ ናልባንድያን ጋር አብሬ ሰርቻለሁ። የኔንም የሙዚቃ ግጥቦምች የሌሎችንም እንዲሁ እያቀናበሩ ብዙ ሰርተዋል። ለምሳሌ አፍሪቃ አፍሪቃ ሀገራችን የሚለዉን ታዋቂ የህብረት ዝማሪ የሰሩ እሳቸዉ ናቸዉ። ቀደም ሲል ደግሞ ከቦርክ ናልባንድያን የመጀመርያዉን የኢትዮጵያ የህዝብ መዝሙር ዜማ የሰሩ ናቸዉ። በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መዘጋጃ ትያትር ቤት የመጣነዉን ሁሉ ያሳለጠኑ ሙዜ ነርሲስ ናልባንድያን ናቸዉ። ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት አስተምረዋል። በአገሪቱ የሙዚቃ ባንድን የመሰረቱ ለዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ መሰረት የሆኑ ናቸዉ ማለት እችላለሁ። ከአርባዎቹ አርመን ህጻናት ከሚባሉት መካከል በሙዚቃ ብቻ ሳይሆን፤ ጫማ ይሰሩ የነበሩ ነበሩ። ሰዓት እንዲሁም በወርቅ ስራ ላይም የተሰማሩ ነበሩ።»  

Äthiopien Vartkes Nalbandiani - Vorsitzender der hier lebenden Armenier
ምስል Vartkes Nalbandiani

አርመኖች በተለይ ደግሞ የናርሲስ ናልባንድያን ቤተሰቦች በተለያዩ ዘርፎች በተለይም በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ በኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋፅ ማድረጋቸዉ ይታወቃል። በህዝብም ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ነበራቸዉ። ዜግነት አለማግኘታቸዉ ትንሽ የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን የሚያሳፍር መሆኑንም ቫርትኬስ ናልባንድያን ተናግረዋል።   

አቶ ቫርትኬስ በአዕምሮ ሁለት የሚመላለስ መሰረታዊ ጥያቄ እንዳለም ያነሳሉ። አንዱ የደሃ ሃገራት ምጣኔ ሃብት ጉዳይ፤ እንዲሁም አላስፈላጊ ጦርነት ብለዋል። እኛም አሁን አላስፈላጊ ጦርነት ዉስጥ ገብተናል፤ ቢሆንም ይላሉ ፖለቲካዊ መፍትሄን ያገኛል፤ ሲሉ ተስፋቸዉን ገልፀዋል። አርመኖች በተለይ ደግሞ የናርሲስ ናልባንድያን ቤተሰቦች በተለያዩ ዘርፎች በተለይም በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ በኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋፅ ማድረጋቸዉ ይታወቃል። በህዝብም ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ነበራቸዉ። ዜግነት አለማግኘታቸዉ ትንሽ የሚያሳዝን ነዉ።  

Zwei-Etagenhaus im Stadtteil Piazza Äthiopien Addis Abeba
ፒያሳ አካባቢ የሚገኘዉና የአዲስ አበባ ከተማ ዕቅድ ፕላን አዉጭ የነበሩት አርመናዊ ሙሴ ሚናስ ጌርቤካን ይኖሩበት የነበረ ቤትምስል Aramazt Kalayjian

አርሜንያዉያን በኦቶማን ግዛት ዘመን ጀምሮ በስደት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት መጀመራቸዉን በኢትዮጵያ የብሄራዊ ትያትር የመጀመርያዉ የሙዚቃ አስተማሪ ልጅ ቫርትኬስ ነርሲስ ናልባንድያን ቀደም ሲል ነግረዉናል። ቫርትኬስ ናልባንድያንን በማመስገን መጻሐፋቸዉን ብትፈልጉ በአማርኛ አልያም በእንጊሊዘኛ ማንበብ እንደምትችሉ በመጠቆም እንወዳለን።

ሙሉ ጥንቅሩን የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን እንድታደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ