1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኤርትራ የሰብዓዊ መብት ላይ የመከረ አውደ ርዕይ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 11 2012

በፍራንክፈርቱ አዉደ ርዕይ የተለያዩ ዓለማቀፍ ሽልማቶች ተሸላሚና ከ 18 ዓመታት በላይ በእስር የሚማቅቀው አንጋፋው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ዳዊት ይስሃቅ ልጅ ቤተልሄም ዳዊትን ጨምሮ በኤርትራ የእስር ሰቆቃ ሰለባ የነበሩ ደራሲያንና ጋዜጠኞች በአገሪቱ የተንሰራፋውን የመብት አፈናና ጭቆና ለታዳምያኑ አስረድተዋል።

https://p.dw.com/p/3Riry
Diskussion über die Menschenrechtssituation in Eritrea in Frankfurt am Main
ምስል DW/E. Fekade

 

የኤርትራ መንግስት ለበርካታ ዓመታት ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ በወታደራዊ እስር ቤቶች አስሮ የሚያሰቃያቸውን ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈታና በአገሪቱ የዜጎችን ሰብአዊ መብት እንዲያከብር ተጠየቀ። በፍራንክፈርት ከተማ በሚገኘው ትልቁ የኤግዚቪሽን ማዕከል በተዘጋጀው እና ከ300 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ጎብኚዎች በታደሙበት 71ኛው የመጻሕፍት እና የሕትመት ውጤቶች ልዩ ዓወደ ርዕይ በጨቋኝ መንግሥታት እስር እና እንግልት ለሚፈጸምባቸው ደራሲያን ጋዜጠኞች ጦማሪያን እና ሃያሲያን መብት የሚታገለው ዓለማቀፉ የፕሬስ ተሟጋች ድርጅት ፔን የጀርመን ኦስትሪያ እና ኤርትራ አመራሮች የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች እንዲሁም የስዊድኑ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች የቦርድ ተጠሪዎች በኤርትራ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ዙሪያ ባካሄዱት ውይይት እስር እና አፈናው አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን አውስተዋል።

Diskussion über die Menschenrechtssituation in Eritrea in Frankfurt am Main
ምስል DW/E. Fekade

በውይይቱ ላይ የተለያዩ ዓለማቀፍ ሽልማቶች ተሸላሚ  እና ከ 18 ዓመታት በላይ በእስር የሚማቅቀው አንጋፋው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ዳዊት ይስሃቅ ልጅ ቤተልሄም ዳዊትን ጨምሮ በኤርትራ የእስር ሰቆቃ ሰለባ የነበሩ ደራሲያን እና ጋዜጠኞች በአገሪቱ የተንሰራፋውን የመብት አፈና እና ጭቆና ለታዳምያኑ አስረድተዋል።

ዓለማቀፉ የፔን ድርጅት ተጠሪዎች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችም በተባበሩት መንግስታት እና በአውሮጳ ሕብረት የስብሰባ መድረኮች ድምጻቸውን በማሰማት መንግስታት እና ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በኤርትራ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እና ተጽዕኖውን እንዲያጠናክር ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት። 

አዜብ ታደሰ 

እንዳልካቸው ፈቃደ

ተስፋለም ወልደየስ