በኤርትራ የተማረኩትን ኮሎኔል ለማስለቀቅ ዘመቻ
ሐሙስ፣ የካቲት 21 2011በኤርትራ መንግሥት እጅ በምርኮ የሚገኙት ኢትዮጲያዊው ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ያሉበትን ሁኔታ ግልጽ እንዲያደረግ የሚጠይቅ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ በመካሄድ ላይ ነው። የዘመቻው እስተባባሪዎች እንዳሉት የዘመቻው ዓላማ የኤርትራ መንግሥት በኮሎኔሉ ዙሪያ ትክክለኛ መረጃ እንዲሰጥ ግፊት ለማድረግ ነው። ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ በመካሄድ ላይ በሚገኘው በዚሁ ዘመቻ አስከአሁን በቡዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ድጋፋቸውን እየሰጡ እንደሚገኙ የዘመቻው አስተባባሪዎች ለ «DW» ገልጸዋል።
በኢትዮጲያ የወታደራዊ አየር ኃይል ታሪክ ውስጥ በብዙዎች ዘንድ የብሔራዊ ጀግና ተምሳሌት ተደርገው ይቆጠራሉ። ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ። በተለይም በ 1969 ዓ.ም በተካሄደው የኢትዮ ሶማሌ ጦርነት / ሚግ 23 ጀት በማብረርና ሞቃዲሾ ድረስ በመዝለቅ / በሰይድ ባሬ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ላይ ያደረሱት ተደጋጋሚ ጥቃት ዛሬም ድረስ ይነገርላቸዋል። ኮሎኔሉ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት ለተመሳሳይ ግዳጅ ሲያበሩት የነበረው ጀት ተመቶ መውደቁን ተከትሎ / በምርኮ በኤርትራ ወታደሮች እጅ ከገቡ በኋላ / እስከዛሬ ከምናልባት በስተቀር ስለአሳቸው አውነተኛ መረጃዎችን ማግኘት አልተቻለም። ይሁን እንጂ የኮሎኔል በዛብህ ጉዳይ ያሳስበናል የሚሉት ወዳጆቻቸውና አድናቂዎቻቸው / የኤርትራ መንግሥት ኮሎኔሉ ያሉበትን ሁኔታ ግልጽ ያድርግልን ሲሉ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ይፋ አድርገዋል። ከዘመቻው አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ እዩኤል አረጋ፤ ዘመቻው በኮሎኔሉ በዛብህ ጴጥሮስ ዙሪያ ትክክለኛ መረጃ እንዲሰጥ ግፊት ለማድረግ ያለመ መሆኑን ለ «DW» ገልጸዋል።
ሌላው የዘመቻው አስተባባሪ አቶ ታምራት በየነ በበኩላቸው፤ እስከአሁን ከኤርትራም ሆነ ከኢትዮጲያ መንግሥት በኩል በኮሎኔሉ ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ መረጃ ባለመቅረቡ፤ ከቅርበ ጊዜ ወዲህ ምንጫቸው ያልተረጋገጡ መረጃዎችና ምላምቶችና እንዲበራከቱ ምክንያት እየሆነ ይገኛል ብለዋል። ምላሽ ለማግኘት በቅድሚያ ጠያቂ ሊኖር ይገባል የሚሉት አቶ ታምራት፤ በዚህ ዘመቻ የኢትዮጲያ መንግሥት ለኤርትራ መንግሥት ይፋዊ ጥያቄ እንዲያቀርብ የሚጠይቁ መልዕክቶች እየተላለፉ ይገኛሉ ብለዋል። ባለፈው ሰኞ የተጀመረው ይሄው ዘመቻ ለቀጣይ አንድ ሳምንት እንደሚቆይ የተናገሩት አስተባባሪዎች፤ አስከአሁን በተገኙ ደጋፎች ዙሪያም ተከታዩን ብለዋል። እየተካሄደ በሚገኘው ዘመቻ ዙሪያ የኮሎኔል በዛብህ የቅርብ ቤተሰቦችን በማነጋገር በዚህ ዘገባ ለማካተት ያደረኩት ሙከራ አልተሳካም። ሙሉ ዘገባዉን የድምፅ ማድጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!
ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ