1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በከሚሴና አጣየ ጥቃቶች ከ328 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 14 2013

በቅርቡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርር አካባቢዎች በተፈጠሩ ጥቃቶች ከ328 ሺህ በላይ ወገኖች መፈናቀላቸውን የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽን አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/3sRBJ
Äthiopien Amhara Katastrophenprävention   Komission
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ከ328 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገልጧል

በቅርቡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርር አካባቢዎች በተፈጠሩ ጥቃቶች ከ328 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ርዳታ ማድረሱንና አሁንም የእለት ምግብ እየላከ እንደሆነ አመልክቷል- ተፈናቃዮች ግን «ርዳታ አላገኘንም» እያሉ ነው። የ10 ሚሊዮን ንብረት ባለቤት የነበሩ ተፈናቃይ ዛሬ በልመና ላይ ተገኝቻለሁ ሲሉ የጥፋቱን መጠን ይገልጣሉ።

በቅረቡ በአማራ ክልል ስር በሚገኙት በሰሜን ሸዋና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ብዙዎቸ ሕይወታቸው አልፏል በርካቶች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከሞትና ከአካል ጉዳት የተረፉት ደግሞ ለአመታት ያካበቱት ንብረታቸው ወድሞ ቀያቸውን ለቅቀው ለመፈናቀል በቅተዋል።  በአጣየ ከተማ ለዓመታት የኖሩትና ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረታቸው ወድሞ ወደ ከሚሴ ከተፈናቀሉት መካከል አንዱ ዛሬ «ለማኝ ሆኛለሁ» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ በስልክ ተናግረዋል፣ እርዳታም አላገኙ።

ሌላው ተፈናቃይም በነበረው ውድመት ንብረታቸው ወድሞ በችግር ላይ እንደሆኑ አመልክተዋል። በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የአደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ይማም በበኩላቸው በብሔረሰብ አስተዳደሩ በመጀመሪያው ግጭት 78 ሺህ ሰው መፈናቀሉን አመልክተዋል። በሁለተኛው ግጭት ምን ያህል ሰው እንደተፈናቀለ እየተጠና መሆኑን አመልክተው፣ የአማራ ክልል መንግስት የእለት ምግብ እርዳታ ማድረጉንና ለተፈናቃዮች እተከፋፈለ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የአደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወርቃለማሁ ኮስተሬ በበኩላቸው በነበሩ ግጭቶች ከዞኑ አጠቃላይ ከ250 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል ብለዋል፣ እርዳታም እየተሰጠ እንደሆነና ተጨማሪ እርዳታ እየተጓጓዘ መሆኑንም አመልክተዋል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽነር ዘለዓለም ልጃለም እንዳሉት በመጀመሪያው ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች እርዳታ መድረሱንና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በሁለተኛው ግጭት ምን ህል ወገኖች እንደተፈናቀሉ ሪፖርት አላደረገም ብለዋል። በሁለቱ አስተዳደር ዞኖች ያለውን ግጭት ለማስቆም የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን የእዝ ጣቢያ አቋቁሞ ወደስራ ገብቷል።

ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ