1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በወቅታዊ ጉዳዮች የው/ጉ ሚኒስቴር መግለጫ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 21 2014

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከርዕሠ ብሔር ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ ጋር ባደረጉት ውይይት ሁለቱ አገሮች ጥልቅ እና ታሪካዊ ፣ በመንግሥታት መለዋወጥ የማይዋዥቅ ጠንካራ የፖለቲካ ወዳጅነትና ግንኙነት ያላቸው መሆኑ ላይ በስፋት ተመክሮበታል ተብለዋል።

https://p.dw.com/p/4EnQG
Meles Alem, Ethiopia Ministry of Foreign affairs spokes person | Addis Abeba, Ethiopia
ምስል Solomon Muchie/DW

የውጭጉዳይ ሚኒስቴር ሳምንታዊ መግለጫ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ ከቀድሞ ሶቪየት ሕብረት ተበድራው ሲንከባለል የቆየ  162 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብድር በኢትዮጵያ ለልማት እንዲውል ሩሲያ መወሰኗን በአዲስ አበባ የአንድ ቀን ጉብኝታቸውን አጠናቀው ትናንት የተመለሱት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ አረጋግጠዋል። 

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገር ዜጎችን ሕጋዊ ለማድረግ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ምዝገባ መጀመሩ ታውቃል።
በዚህም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ 69 ሺህ የተለያዩ የውጭ አገራት ዜጎች ሕጋዊ አሠራርን ለማስፈን በሚል መመዝገባቸውን የሚኒስቴሩ ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው ሰሜን ኢትዮጵያ ላይ የተፈፀመን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለምመርመር ጥያቄ ያቀረበው የተባበሩት መንግሥታት የምርመራ ቡድን አሁን የመጣው "ምርመራ ለማድረግ ሳይሆን በቀጣይ በቡድኑ እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካክል በሚኖረው ዝርዝር የእንቅስቃሴ ማዕቀፍ ላይ ለመነጋገር ነው" ብለዋል።

ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ኢትዮጵያን ለአንድ ቀን የጎበኙት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከርዕሠ ብሔር ሳኅለ ወርቅ ዘውዴ ጋር ባደረጉት "ሰፊ እና ስኬታማ" ያሉት ውይይት ሁለቱ አገሮች ጥልቅ እና ታሪካዊ ፣ በመንግሥታት መለዋወጥ የማይዋዥቅ ጠንካራ የፖለቲካ ወዳጅነትና ግንኙነት ያላቸው መሆኑ ላይ በስፋት ተመክሮበታል ብለዋል።
ይህ በሁለቱ አገሮች መካከል የተገነባው ጠንካራ የፖለቲካ ወዳጅነት በሌሎች ዘርፎች ላይም በላቀ ደረጃ እንዲጠናከር ርዕሠ ብሔር ሳኅለ ወርቅ ዘውዴም ፣ ምክትል እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተናጠል ከላቭሮቭ ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች በስፋት መዳሰሳቸውን ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ "ይህንን ሀሳብ መጋራታቸውን" ብሎም በባለ ብዙ ወገን ጉዳይ ላይ አፍሪቃ ትልቅ አህጉር መሆኑን ጠቅሰው በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ መቀመጫ ሊኖረው እንደሚገባ አገራቸው የማያወላዳ አቋም እንዳለው መግለፃቸውን አብራርተዋል።
ከጉብኝቱ ተገኘ ያሉትን ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታ ቃል ዐቀባዩ ዘርዝረዋል። 

Äthiopien Wöchentliche PK Meles Alem, Addis Abeba
ምስል Getachew Tedla HG

ኢትዮጵያ ውስጥ በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገር ዜጎችን ሕጋዊ ለማድረግ ምዝገባ መጀመሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተነግሯል።
በዚህም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በአዲስ አበባ 60 ሺህ የተለያዩ አገራት ዜጎች "ሕጋዊ አሠራርን ለማስፈን" በሚል መመዝገባቸውን ቃል ዐቀባይ መለስ ዓለም ተናግረዋል። 
በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገር ዜጎችን መመዝገብ እና የመቆጣጠር ኃላፊነት መንግሥት እንዳለበት ያስታወቁት ቃል ዐቀባዩ ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የገቡ የውጭ አገር ዜጎች የ ቪዛ ጊዜያቸው እና የምኖሪያ ፈቃዳቸው ቀነ ገደብ ሲያልፍ ማሳወቅና ማደስ ግዴታቸው መሆኑን አስታውሰዋል።
ምዝገባው "የከተማ ስደተኛ ሆነው የስደተኛ መታወቂያ ያላቸውና ያንን በማደስ ሂደት ላይ ያሉትን፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትን እና  ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን እንደማያካትት ተናግረዋል።
ሥራው አዲስ አበባ ውስጥ በተከፈቱ 121 የምዝገባ ጣቢያዎ የሚፈፀም እንደሆነና ከአሜሪካ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከአፍሪካ አገሮች የመጡ የውጭ ዜጎች በምዝገባው ውስጥ እየተለዩ መሆኑንም አብራርተዋል።
አልሸባብ ከሰሞኑ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ስለፈፀመው ጥቃት የተጠየቁት ቃል ዐቀባዩ ድርጊቱ ሊወገዝ የሚገባው ተግባር ነው ብለዋል። 
የመንግሥታቱ ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ ተፈጽሟል ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የተናጠል የምርመራ ጥያቄን መንግሥት እንደማይቀበል አቋም ይዞ የነበረ ቢሆንም ከሰሞኑ የአቋም ለውጥ አድርጎ የምርመራ ቡድን አባላቱም በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባ ይገኛሉ።
ይህንን የተመለከተውን ጥያቄም ቃል ዐቀባዩ ምላሽ ሰጥተውበታል። 
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የሰጡትን አስተያየት መንግሥት የሰማው ከግብጽ መገነኛ ብዙኃን መሆኑን የተናገሩት አምባሳደር መለስ ዓለም ጉዳዩን የሶማሊያ መንግሥት አቋም ተደርጎ ለመውሰድ አስቸጋሪ ነው ብለዋል።
"ትልቁ ቁምነገር የግድቡ ግንባታ ከኢትዮጵያ ባልተናነሰ ሱዳንንም ፣ ግብጽንም ይጠቅማል ፣ ይህንንም እነሱ ያውቁታል ብለዋል።"  በሌሎች ላይ ትርጉም ያለው ተጽእኖ ሳናደርስ እንደ አገር ፣ ይህንን የማድረግ መብት አለን። መንግሥት ይህንን  ለመገንባት የማንንም ፈቃድ መጠየቅ አይጠበቅበትም ሲሉም ተናግረዋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

ሽዋዬ ለገሠ