1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱ ኤርትራውያን ቁጥር እየጨመረ ነው

ሰኞ፣ ግንቦት 26 2011

ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ፍልሰተኞች መጠን በየወሩ እየጨመረ እንደሚገኝ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች ኤጀንሲ ገለጸ። በየወሩ በአማካይ ስምንት ሺህ ገደማ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ኤጀንሲው ለዶይቼ ቬለ (DW) አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/3Jlld
Eritrea Flüchtlingslager in der Region Tigrai Äthiopien
ምስል Reuters/T. Negeri

ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱ ኤርትራውያን እየጨመረ ነው

ወደ ኢትዮጵያ የሚፈልሱ የኤርትራ ስደተኞች መጠን እያሻቀበ መምጣት ከሁለቱ ሀገራት ድንበር መከፈት እና መዘጋት ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች ኤጀንሲ ገለጸ። በኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ያሲን አልይ ለዶይቼ ቬለ (DW) እንደተናገሩት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የኤርትራ ስደተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ የመጣ ነው። 

አቶ ያሲን በአሁኑ ወቅት በወር በሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልሰተኞች ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ አስረድተዋል። “በአማካይ በየወሩ ያለ የኤርትራ የስደተኞች ፍልሰት መጠን 8,058 ነው” ሲሉ ኃላፊው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።    
 
በኢትዮጵያ በስደተኛነት የተመዘገቡ ኤርትራዊያን ቁጥር 263 ሺህ 707 መድረሱን ከስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ አብዛኞቹ ስደተኞች በትግራይ ክልል ሽሬ አካባቢ በሚገኙ አምስት የስደተኞች መጠለያዎች ይኖራሉ። በአፋር ክልል በርሃሌ እና አሳይታ አካባቢ ያሉ ሁለት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችም ኤርትራውያን ስደተኞችን እያስተናገዱ ይገኛሉ። 

Bildergalerie Flüchtlingscamp Tigray in Äthiopien
ምስል Milena Belloni

በሰባቱ ጣቢያዎች ውስጥ ከሚኖሩ ከእነዚህ ስደተኞች ባሻገር ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ ኤርትራውያን ስደተኞች “የከተማ ስደተኛ” ተብለው በአዲስ አበባ ህይወታቸውን እየገፉ ይገኛሉ። ቁጥጥር ከሚደረግበት የስደተኞች ጣቢያ ውጭ በከተማ የሚኖሩት ስደተኞች በሃገራዊ ደህንነት ላይ የሚደቅኑት አደጋ ይኖር እንደው የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተጠይቀዋል። በከተማ እንዲኖሩ ፍቃድ ላገኙ ስደተኞች መታወቂያ እንደሚሰጣቸው፣ ማንነታቸው እና የት አካባቢ እንዳሉ በመረጃ እንደሚታወቅ ኃላፊው ገልጸዋል። “እነርሱን የሚከታተል ክፍል አለ” የሚሉት አቶ ያሲን “ያን ያህል የደህንነት ስጋት የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።      

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ሀገሮች ተቀብላ ያስጠለለቻቸው ስደተኞች ቁጥር 1. 5 ሚሊዮን መድረሱን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ከስደተኞቹ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት የደቡብ ሱዳን ዜጎች ሲሆኑ ሶማሊያውያን እና ኤርትራውያን ስደተኞች በሁለተኛነት እና ሶስተኛነት ይከተላሉ። በኢትዮጵያ ያሉ ስደተኞች መብዛት “በሀገሪቱ ባለው የኑሮ ውድነት ላይ የራሱ ተጽእኖ አለው” የሚሉ ወገኖች አሉ። የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ያሲን ግን ስደተኞቹ “በኑሮ ውድነት የሚያሳርፉት ጫና የለም” ሲሉ አስተባብለዋል። 

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን በማስጠለሏ በዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች በምትወደሰው ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ በተፈጠረ ቀውስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ ከቀያቸው ተፈናቅለውባታል። በየአካባቢው የተጠለሉ እነዚህ ተፈናቃዮች በቂ እርዳታ እና ድጋፍ እንደማያገኙ በየጊዜው እሮሮ ያሰማሉ። 

ሰለሞን ሙጬ

ተስፋለም ወልደየስ