በጋዛ አል-ሺፋ ሆስፒታል በሦስት ቀናት 32 ሕሙማን መሞታቸውን የፍልስጤም ባለሥልጣናት ገለጹ
ሰኞ፣ ኅዳር 3 2016በጋዛ ከተማ በሚገኘው አል-ሺፋ ሆስፒታል ባለፉት ሦስት ቀናት 32 ሕሙማን መሞታቸውን የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አሽራፍ አል ቂድራ አስታወቁ። በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ ሰርጥ ምክትል የጤና ሚኒስትር ይሱፍ አቡ ሪሽ በበኩላቸው በግዛቲቱ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኙ ሁሉም ሆስፒታሎች በኃይል እጥረት ሳቢያ አገልግሎት ማቆማቸውን ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።
በጋዛ ሰርጥ ትልቁ የሆነው አል-ሺፋ ሆስፒታል በሣምንቱ መጨረሻ በእስራኤል ወታደሮች ሲከበብ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከመጨረሻ መጠለያቸው ለመሸሽ ተገደዋል። ይሁንና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕሙማን እና ተፈናቃዮች አሁንም በሆስፒታሉ እንደሚገኙ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም አል-ሺፋ “እንደ ሆስፒታል እየሰራ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል። አል-ሺፋ ሆስፒታል በነዳጅ እጥረት ሳቢያ ባለፈው ቅዳሜ ሥራ እንዳቆመ ሬውተርስ ዘግቧል።
የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አሽራፍ አል ቂድራ ባለፉት ሦስት ቀናት ብቻ 32 ሕሙማን በአል-ሺፋ ሆስፒታል ሕይወታቸው እንዳለፈ ተናግረዋል። ከሟቾቹ መካከል ሦስት ያልጠኑ ሕጻናት ይገኙበታል።
እስራኤል የአል-ሺፋ ሆስፒታልን ሐማስ የዕዝ ማዕከል አድርጎ ይጠቀምበታል ስትል ትከሳለች። እስራኤል ለውንጀላው ያቀረበችው ማረጋገጫ የለም። ሐማስ እና የሆስፒታሉ ሠራተኞች የእስራኤልን ክስ አስተባብለዋል።
በጋዛ የሚገኘው አል-ቁድስ ሆስፒታል ነዳጅ በመጨረሱ ምክንያት ትላንት እሁድ ሥራ ለማቆም ተገዷል። ሆስፒታሉን የሚያስተዳድረው የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ የእስራኤል ወታደሮች በአል-ቁድስ አቅራቢያ መስፈራቸውን እና 6,000 ገደማ ሕሙማን፣ የሕክምና ባለሙያዎች እና ተፈናቃዮችን ለማሸሽ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።
የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ከ11,000 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በጋዛ የሚገኘው የጤና ሚኒስቴር ገልጿል። ከተገደሉት ሰዎች ሁለት ሦስተኛው ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ 2,700 ሰዎች የገቡበት አይታወቅም።
በእስራኤል ወገን በትንሹ 1,200 ሰዎች ተገድለዋል። አብዛኞቹ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው። የእስራኤል ጦር በጋዛ የምድር ዘመቻ ከጀመረ ወዲህ 44 ወታደሮች መገደላቸውን አስታውቋል።
በእስራኤል ባለሥልጣናት መረጃ መሠረት ከአምስት ሣምንታት ገደማ በፊት ሐማስ ጥቃት በፈጸመበት ወቅት ሕጻናት እና አረጋውያንን ጨምሮ 239 ሰዎችን አግቷል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የታገቱ ሰዎች የሚለቀቁበት ሥምምነት ሊኖር እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል። “ሥምምነት ሊኖር ይችላል” ያሉት ኔታንያሁ ተግባራዊ የመሆን ዕድሉን ለማስፋት ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና የቃጣር ኢምር ሼይክ ታሚም ቢን ሐማድ አል ታኒ ትላንት እሁድ የታገቱ ሰዎች በሚለቀቁበት ሁኔታ ላይ መነጋገራቸው ዋይት ሐውስ ገልጾ ነበር።