በጦርነቱ ተዘርፈዉ ለዉጭ ገበያ ቀረቡ የተባሉት ቅርሶች ጉዳይ
ሐሙስ፣ የካቲት 10 2014«ይሄ በመላዉ ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዉያንን ያሳሰበ ጉዳይ ነዉ። ቅርስ ማለት ዉርስ ነዉ። ታሪክ ነዉ። የማነነት መገለጫ ነዉ። የአንድ ሃገር ቅርስ ሲዘረፍ ፤ ማንነትን ለማሳጣት የተካሄደ ድርጊት ነዉ። ይህ የቅርስ ዘረፋ የጦሩነቱ አንድ አካል ሆኖ መታየት አለበት። » በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰዉን ጦርነት ተከትሎ ሃይማኖታዊ እና ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቅርሶች እየተመዘበሩ ለዓለም አቀፍ ገበያ በአነስተኛ ዋጋ ለሽያጭ መቅረባቸዉ፤ ማንነት ለማሳጣት የተካሄደ ከጦርነቱ ያልተናነሰ ጥቃት ነዉ ሲሉ ያወገዙት በብሪታንያ የዲያስፖራ ሙዚየም መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለባቸዉ ደሳለኝ ናቸዉ። በሰሜንኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ትግራይን ጨምሮ በወሎ እና ሰሜን ጎንደር የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ልዩ ልዩ ቅርሶች የሚገኙባቸው ሙዚየሞች መዘረፋቸ፤ አብያተ-ክርስትያናት እና ገዳማት እንዲሁም መስጊዶች መዉደማቸዉ በተለያዩ ጊዜያት ተዘግቦአል። ሰሞኑን የብሪታንያዉ ዘ ኢንዲፔንደንት የተባለዉ ጋዜጣ እና የብሪታንያ ብዙኃን መገናኛዎች እንደዘገቡት ደግሞ ኢቤይ በተባለው የሽያጭ ድረ- ገፅ ላይ ለሽያጭ ከቀረቡት ጥንታዊ ቁሳቁሶች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ጥንታዊ ቅርሶች ከሆኑት መካከል በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ አነስተኛ መጠን ያላቸው የብራና መጽሐፍት፣ ልዩ ልዩ ይዘትና ቅርጽ ያላቸው መስቀሎች ይገኙበታል። በብሪታንያ ለንደን የዲያስፖራ ሙዚየም መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለባቸዉ ደሳለኝ እንደተናገሩት፤ የተዘረፉ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶች ብዛት ባለፉት 6 ወራት እየጨመረ መሄዱን በሚደርሳቸዉ ጥቆማዎች እና ዘ ኢንዲፐንደንት የተባለዉ ጋዜጣም ማረጋገጡን ጠቅሰን በኢቤይ የበይነ መረብ ገበያ ለሽያጭ የቀረቡት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች በአስቸኳይ ከገበያ ላይ እንዲነሱ ለድርጅቱ ማሳሰቢያ ልከናል ሲሉ ተናግረዋል። አቶ አለባቸዉ እነዚህ ለሽያጭ የቀረቡት ቅርሶች በጦርነት ወቅት ከሀገሪቷ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያናት እና ገዳማት የተዘረፉ ሊሆኑ ይችላሉ ስንል ስጋትና ጥርጣርያችንን ጠቅሰን ለኢቤይ ጥቆማ ሰጥተናልም ብለዋል። ኢቤይ የተሰኘዉ የድረ ገጽ የሸቀጦች የገበያ መድረክ: በብሪታኒያ እና በዓለማቀፍ ሕግ ከሙዚምና ከሃይማኖት ተቋማት የተዘረፉ ቅርሶችን እንዳይሸጥ የተከለከለ በመሆኑ ዘራፊዎችን እንዳይተባበር፤ አሁንም ማሳሰባችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ አክለዋል።
የቱሪዝም እና ባህል ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት እንዲሁም እራሱ በቱሪዝም ጋዜጠኝነቱ እዉቅናን ያተረፈዉ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በበኩሉ፤ የሰሜን ኢትዮጵያዉ ጦርነት በቅርስ ላይ ከፍተኛ ዉድመት ማስከተሉን በተለይ በደሴ ከተማ እና ይስማላ ንጉስ ዉስጥ የሚገኙ ሙዚየሞችን ተዘዋዉሮ መመልከቱን ተናግሮአል።
ሰሞኑን ኢቤይ በተባለዉ የቁሳቁስ መሸጫ ድረ-ዓለማቀፍ ላይ ለሽያጭ የቀረቡት ቅርሶች የኢትዮጵያ ስለመሆናቸዉ ምንም ጥርጣሪ አለመኖሩን የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሚኒስቴር ገልፆአል። የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ድኤታ ስለሺ ግርማ በተለይ ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት የዓለም ቅርሶችን የሚጠብቀውና ፓሪስ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) ቅርሶቹ የኢትዮጵያ በመሆናቸዉ ለሽያጭ እንዳይውሉ እና ወደ አገር ቤት መመለስ እንዲቻል አዲስ አበባ ከሚገኘው የዩኔስኮ ኃላፊ ጋር መነጋገራቸውን ተናግረዋል። ይሁንና ቅርሶቹ አሁን በጦርነቱ ተዘርፈዉ የወጡ አልያም ቀደም ብለዉ የወጡ ስለመሆናቸዉ በርግጠኝነት መናገር አስቸጋሪ መሆኑን አክለዋል።
በአንድ ሃገር በሚካሄድ ጦርነት ወቅት በርካታ ቅርስ ይወድማል፤ ይዘረፋል ያሉት የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ስለሺ ግርማ፣ ቅርሶች ከሃገር ቤት በተለያዩ ዘዴዎች እንዳይወጡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ጠንካራ ቁጥጥር እንደሚደረግ ተናግረዋል። ይሁንና ይህን ሁሉ ቁጥጥር ሁሉ አልፈዉ ከሃገር የሚወጡ ቅርሶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሚኒስትር ድኤታ ስለሺ ግርማ አልሸሸጉም።
የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሚኒስቴር አቋምን የሚጋሩት ፤ በብሔራዊ ደረጃ በተቋቋመዉ ዓለም አቀፍ የቅርስ አስመላሽ ኮሜቴ አባል ዶክተር ዮሃንስ ዘለቀ እንደሚሉት ደግሞ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጥንታዊ ቅርሶች መሸጣቸዉ የአሁኑ የሚጀመርያ ጊዜ አይደለም። ዶ/ር ዮሃንስ ከትግራይ ወይም በሰሜን ኢትዮጵያ ያለዉን ጦርነት ተከትሎ የተዘረፉ የሃገሪቱ ቅርሶች ናቸዉ ኢቤይ ላይ እየተሸጡ ያሉት የሚባለዉን ዘገባ ማረጋገጥ አይቻልም። ብዙ ጥንታዊ ናቸዉ ተብለዉ የሚሰሩ ባህላዊ ቁሳቁሶች አሉ። መጀመርያ የተባለዉን እቃ ባለሞያ ሊያየዉ ይገባል። በዚህ ዘገባ ልንረበሽ አይገባም ። ይሁንና ኢትዮጵያዉያን ለቅርስ ያለን ግንዛቤ እና መቆርቆር እየጨመረ መሆኑን አይቻለሁ ሲሉ ዶ/ር ዮሃንስ አክለዋል።
በብሪታንያ የዲያስፖራ ሙዚየም መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለባቸዉ ደሳለኝ በበኩላቸዉ ቅርስ ከሃገር ሳይወጣ መንግሥት ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ አለበት፤ ከሃገር ከወጣ በኋላ ግን ለማስመለስም ሆነ የት እንደደረሰ ለማወቅ ከባድ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ስለሺ ግርማ የተዘረፉ ቅርሶችን ጉዳይ በተመለከተ መስርያ ቤታቸዉ ከዩኒስኮ ጋር እየሰራ ብሎም በተለያዩ ሃገራት ያሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶችን በማስመለስ ረገድ ከኢትዮጵያዉያን ጋር እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ