1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቲክ ቶክ ቀነገደብ በዩናይትድ ስቴትስ 

ረቡዕ፣ መስከረም 13 2013

ቲክ ቶክ የተሰኘው የቪዲዮ መተግበሪያ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አገልግሎቱ እንዲቋረጥ በፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የተቀመጠው ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ ተቃርቧል። በቲክቶክ ባለቤት ቻይና እና ዩናይትድ ስቴትስ ግዙፍ ኩባንያዎች መካከል ግን አንዳች ስምምነት ላይ የተደረሰ ይመስላል።

https://p.dw.com/p/3itBZ
USA App Tiktok WeChat
ምስል Dado Ruvic/Reuters

የቻይና መተግበሪያዎች ብርቱ ፈተና በአሜሪካ

ቲክ ቶክ የተሰኘው የቪዲዮ መተግበሪያ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አገልግሎቱ እንዲቋረጥ በፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የተቀመጠው ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ ተቃርቧል። በቲክቶክ ባለቤት ቻይና እና ዩናይትድ ስቴትስ ግዙፍ ኩባንያዎች መካከል ግን አንዳች ስምምነት ላይ የተደረሰ ይመስላል። ስለዚህም ለጊዜውም ቢኾን መተግበሪያው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አገልግሎቱ አልተቋረጠም።

ቲክ ቶክ የተሰኘው አጫጭር የተንቀሳቃሽ መልእክቶች የሚሠራጩበት መተግበሪያን ለመቆጣጠር ዩናይትድ ስቴትስ አዲስ ዕቅድ ይዛ ብቅ ብላለች። በእርግጥ ዕቅዱ በቻይና ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም። እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ እቅድ ከኾነ፦ በአሜሪካ ቊጥጥር ሥር የሚገኙት ኦራክል የኮምፒውተር እና ኢንተርኔት ሥነ ቴክኒክ ኩባንያ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ የሚሸቅጠው ዋልማርት ተቋም የቻይናው ቲክ ቶክ ውስጥ እጃቸውን በረዥሙ ሊያስገቡ ይገባል። 

USA TikTok Bürogebäude in Kalifornien
ምስል Getty Images/M. Tama

አዲሱ የቲክ ቶክ ኩባንያም ዋና መቀመጫውን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ቴክሳስ እንዲያዛውር ይፈልጋሉ ፕሬዚደንቱ። የቻይና መንግሥት ቲክ ቶክ ላይ ያደርጋል ያሉትን ቊጥጥር ለመገደብ የቲክ ቶክ ተጠቃሚዎች ሠነድ የሚከማችበት ግዙፍ ቋትም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እንዲኾን ይሻሉ። ያም ብቻ አይደለም፤ ቻይና በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ማፍሰስ ይጠበቅባታል እንደ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ዕቅድ። 

«የደኅንነቱ አስተማማኝነት መቶ በመቶ ይኾናል። እጅግ በጣም ኃይለኛ በርካታ የደኅንነት ማስጠበቂያዎች ያሉት ከእነሱ የተነጠለ ሠነድ ማከማቻ ጥቅም ላይ ይውላል። በተጨማሪም ለትምሕርት የሚውል የአምስት ቢሊዮን ዶላር አስተዋጽዖ ያደርጋሉ።»

ይኽን የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ዕቅድ ለቻይና መንግሥት የሚቀርበው «ግሎባል ታይምስ» ጋዜጣ፦ «የቻይናን ብሔራዊ ደኅንነት፣ ጥቅም እና ክብር የሚጎዳ» ብሎታል። ንብረትነቱ የቻይና የኾነው እና በዓለም ዙሪያ በተለይ በብዛት ታዳጊ ወጣቶች የሚያዘወትሩት ቲክ ቶክ መተግበሪያ መረጃዎችን አልግባብ ይጠቀማል በሚል ነው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሊታገድ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ የሰነባበተው። 

TikTok
ምስል picture-alliance/dpa/Jiji Press/Y. Kurose

ከ100 ሚሊዮን በላይ የቲክ ቶክ ተጠቃሚዎች ያሏት ዩናይትድ ስቴትስ ባይትዳንስ (ByteDance) የተሰኘው የቻይናው መተግበሪያ መረጃዎችን አላግባብ ለቻይና መንግሥት አሳልፎ እየሰጠ ነው ባይ ናት። ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ቲክ ቶክን ለጊዜው ማዘጋታቸውን ትተው አዲስ በማለት ያቀረቡት ሐሳብ በበርካታ ሺህዎች ለሚቆጠሩ የሀገራቸው ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ይኖርበታል።  

«እንደሚመስለኝ ሐሳቡ ለዩናይትድ ስቴትስ ድንቅ የሚባል ነው። ቢያንስ 25.000 ሰዎችን ይቀጥራሉ።»
ይኽን ዕቅድ ይዛ ብቅ ያለችው ዩናይትድ ስቴትስ ቲክ ቶክ መተግበሪያ በሀገሯ ከአገልግሎት ውጪ የሚኾንበትን ቀነ ገደብ በአንድ ሳምንት አራዝማለች። ቲክ ቶክ የስምምነት ሐሳብ ከዩናይትድ ስቴትስ እንደቀረበለት አረጋግጧል። በመግለጫውም ኦራክል ኩባንያ የቲክቶክን 20 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለሚገኙ የቲክ ቶክ ተጠቃሚዎችም ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ዐሳውቋል። 

የኦራክል ኃላፊ ሣፍራ ካትዝ በበኩላቸው ድርጅታቸው ዓለም አቀፍ ይኾናል ከተባለው የቲክ ቶክ ድርሻ 12,5 ከመቶውን እንደሚወስድ አረጋግጠዋል። ከዋልማርት ጋር የሚኖረው ስምምነት፦ «የማስታወቂያ ትብብር» እንደኾነ ቲክ ቶክ ጠቊሟል። መረጃዎች የሚያመላክቱት ግን ዎልማርትም 7,5 ከመቶ ድርሻ ሊኖረው እንደሚችል ነው። የዶናልድ ትራምፕ ዕቅድን የቻይና መንግሥት ይቀበለው ወይንም ሙሉ ለሙሉ ያጣጥለው ገና የሚታይ ጉዳይ ነው። አኹን በውል የሚታወቀው የቻይናው ቲክቶክን የዩናይትድ ስቴትሱ ግዙፍ ኩባንያ ማይክሮሶፍት ጠቅልሎ ይግዛው የሚለውን ሐሳብ ቻይና ውድቅ ማድረጓ ነው። 

Symbolbild TikTok Logo
ምስል picture-alliance/NurPhoto/N. Economou

ከቲክ ቶክ ጋር ይደረጋል የሚለው ስምምነት የሚደናቀፍ ከኾነ በቀጣይ ዩናይትድ ስቴትስ ዊቻት የተባለው የቻይና የአጭር መልእክት መላላኪያ መተግበሪያ ላይም ርምጃ ትወስዳለች ተብሎ ይጠበቃል። ምናልባትም ከእሁድ አመሻሽ አለያም ከሰኞ ማለዳ አንስቶ ዊቻት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከአገልግሎት ውጪ ሊሆንም ይችላል። ባለፈው ዐርብ ብቻ ዊቻትን ከዐሥር ሺህ በላይ ሰዎች ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ ጭነው ነበር። በፍጥነት እያደጉ ለሚገኙት የቻይና መተግበሪያዎች ብርቱ ፈተናዎች ከፊታቸው ተደቅኗል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ/ካታሪና ቪልሔልም