ትኩረት የሳበው የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት
ረቡዕ፣ ሰኔ 20 2010በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ተጋርዶ የከረመው የመለያየት መንፈስ ትናንት መሰበሩ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። ኤርትራ ከኢትዮጵያ በኩል ለቀረበላት የሰላም ጥሪ ምላሽ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ የሚመራ የልዑካን ቡድኗን ልካለች። በሁለቱ ሃገራት መካከል በድንበር ሰበብ የተካሄደው ጦርነት ሁለቱንም ወገኖች ክፉኛ መጉዳቱ ሳያንሰው መዘዙ ለዓመታት አልለቃቸው ብሎ ዜጎች ተጎድተዋል። ትናንት የታየው ጅምር ለሁለቱ ሃገራት ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ ለአፍሪቃ ቀንድ ሰላም ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። ኖርዌይ የሚኖሩት ኤርትራዊ ጸሐፊ እና ብሩህ መጻኢ ዕድል ለኤርትራ የተሰኘ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ለሆኑት ደሳለኝ በረከት ግን ይህ አዲስ ግንኙነት ለኤርትራ ሕዝብ የሚያመጣው ነገር የለም ባይ ናቸው።
«ኤርትራ ስልን አሁን ሕዝቡን ነው የምንለው መንግሥቱን ነው የምንለው? ሕዝብ ከሆነ እስካሁን እንደምታውቂው የኤርትራ ላይ ፓርላማ የለም፤ ሌላም ሚዲያም የለም አሁን የሕዝቡን,,,, እንትን አልሰማነውም። እስካሁን የሕዝቡ ድምፅ አይደለም የተሰማው።»
የኢትዮጵያ መንግሥት የድንበር ውዝግቡን ለመፍታት የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን መግለፁም አዲስ ነገር አይደለም ለእሳቸው። ድሮም ቢሆን ኢትዮጵያ እኮ ተቀብላው ነበር ይላሉ።
«ድሮም ቢሆን እኮ አንቀበልም አላሉም፤ በኤርትራ በኩል ደግሞ ከባድመ ኢትዮጵያ ካልወጣች በስተቀር ዉይይት ብሎ ነገር የለም ይሉ ነበር። አሁን ኢትዮጵያ ከባድመ የወጣች አይመስለኝም።»
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለተመራው የኤርትራ የልዑካን ቡድን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ በመሄድ ያደረጉት ደማቅ አቀባበል አዎንታዊ ገፅታ እንዳለው ኤርትራዊው የፖለቲካ ተንታኝና ጸሐፊ አብድራህማን ሰይድ ይናገራሉ።
«የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊቀበሏቸው ይችሉ ነበር በፕሮቶኮል ራሱ፤ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው መቀበላቸው የሚያሳየው አዲሱ የኢትዮጵያ አስተዳደር ከኤርትራ ጋር ላለው ሰላም ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እንዳለ ነው የሚያሳየው።»
እንዲያም ሆኖ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ያለው አስተዳደር እንደሚለያይም በመጥቀስ ልዩነት ያሉትን እንዲህ ይዘረዝራሉ። እንዲህ ሆኖም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተጀመረውን ይህን መቀራረብ በአዎንታዊ መልኩ የሚወስዱት አቶ አብዱራህማን የሁለቱ መንግሥት ሰላም ለአካባቢው ሃገራት ሰላም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው አፅንኦት ሰጥተዋል።
«ኤርትራ እና ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ቀንድ ትልቅ ሚና ነው ያላቸው። በሁለቱ አገሮች ውስጥ ሰላም ሲፈጠር ለሁለቱም ሕዝብ በጣም ነው የሚጠቅመው። በቁጠባ (ኤኮኖሚም) ይሁን በባህልም ይሁን በሌላም በሌላም ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት እና ለአካባቢው በተለይ ለአፍሪቃ ቀንድ ጥቅም አለው። ሌላው ይቅር ይሄ ፕሮክሲ ዎር የሚባለው እንደ ድሮው ኮልድ ዎር በአሜሪካ እና ሶቪየት ኅብረት የነበረው አይነት ተመሳሳይ ነገር በትንሹ በአፍሪቃ ቀንድ ይታይ ነበር። በተለይ ሶማሊያ ውስጥ ማለት ነው። እንደዛ ነገሮች አሁን ይቆማሉ። ስለዚህ ለሰላም ብዙ ያበረታታል። በዚያም ላይ ፕራይም ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እየተከተሉ ያለው ፖሊሲ ለሪጂናል ኢንቲግሬሽን በጣም የሚያመቻች እና የሚያበረታታ ነው።»
ይህ ደግሞ በተለይ ወደብ አልባ ለሆነችው ኢትዮጵያ የባህር አማራጮችን ለማመጠቀም የሚረዳ መሆኑንም አቶ አብዱራህማን አንስተዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ