ቻይና እና የጦር ኃይል ወጪዋ
ረቡዕ፣ የካቲት 27 2005
የቻይና መንግሥት የሰላማዊ መከላከያ ፖለቲካን ለማራመድ በማሰብ የጦር ኃይሉን በጀት ከፍ ማድረጉን አስታውቋል። በዚህም የተነሳ ማንም ሀገር ከቻይና የጦር ጥቃት ሊሰነዘርበት ይችላል በሚል ስጋት ሊያድርበት እንደማይገባ የቻይና ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፉ ዪንግ ትናንት በቤይዢንግ በተከፈተው የቻይና ብሔራዊ ሸንጎ ስብሰባ ላይ አስታውቀዋል። ሀይ ቻዎ ያዘጋጀችውን ዘገባ አርያም ተክሌ እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች።
የጦር ኃይሉን ወጪ በተመለከተ ጠንከር ያለ ጥያቄ ከቻይና ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም የቻይና ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፉ ዪንግ እንዳመለከቱት፡ ሀገራቸው በያመቱ የመከላከያ ዘርፏን ለምን እንደምታጠናክርና የጦሩንም በጀቷን ለምን እንደምታሳድግ ማስረዳታ ያለባት ይመስላል። የቻይና የጦር ኃይል በጀት አሁን ካለበት ከ10 እስከ 11 ከመቶ ጭማሪ ያሳየበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ብሎም፡ ከ2005 እስከ 2009 ዓም ድረስ የጦር ኃይሉ በጀት በያመቱ ከ 15 እስከ 20 ከመቶ ጭማሪ ሲያሳይ ነበር የቆየው። ቻይና አሁን እየተከተለችው ያለው ፖሊሲ ሌሎች ሀገራት ያለፉበት መሆኑን በቦን ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ የጦር ኃይል በጀት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሹ ጉ አስረድተዋል። ይህንን ቻይና የጀመረችውን የጦር ኃይሏን ዘመናይ የማድረጉን ሂደት ሌሎች ሀገራት በቅርብ መከታተላቸውን ፕሮፌሰሩ ቢረዱትም፡ ተጋኖ ሊታይ አይገባም ባይ ናቸው።
በርግጥ፡ ቻይና ውስጥ የሚነገረው የጦር ኃይሉን ዘመናይ ስለማድረግ እና በጦር ኃይሉ ውስጥ ተሀድሶ ስለማነቃቃት እንጂ ስለጦር መሣሪያ ትጥቅ ማሳደግ አለመሆኑን ያስረዱት የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ተቋም ተንታኝ ወይዘሮ ናዲን ጎደሀርት ርምጃው አስፈላጊ ነው ይላሉ።
« ይህ በተለያዩ ሁኔታዎች ሲታይ በርግጥ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ አነስተኛ የጦር ኃይል ቡድናት እንዳላት፡ ልዩ ሥልጠና እንደምትሰጥ፡ የጦር መሣሪያዎችዋን ዘመናይ እንደምታደርግ፡ እነዚህ ሁሉ በከፊል ሀቅ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው፤ ግን፡ ይህ ጎረቤት ሀገራት በዚህ አኳያ ሌላ አስተያየት እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል። »
በቻይና ዜና ወኪል ሺንዋ ዘገባ መሠረት፡ ሀገሪቱ አዳዲስ የጦር መሣሪያ እንደሚገዛ እና የሀገሪቱ ጦር ኃይል በሽብርተኝነት እና በተለያዩት የተፈጥሮ መቅሠፍቶች አንፃር ለሚያደርጉት ትግል ልዩ ሥልጠና እንደሚወስዱ ተመልክቶዋል። የቦን ዩኒቨርሲት ባካሄደው ጥናት መሠረት፡ ቻይና ከጠቅላላ ብሔራዊ ገቢዋ መካከል ከ 1,3 እስከ 1,8 ከመቶ ለጦር ኃይሉ ስትመድብ፡ በአንጻርዋ ሌሎች ጀርመን፡ ፈረንሣይ እና ብሪታንያን የመሳሰሉ ኢንዱስትሪ ሀገራት ለጦር ኃይል የመደቡት ወጪ ከጠቅላላ ብሔራዊ ገቢዋ መካከል ከ 2,5 እስከ 3,5 ከመቶ መሆኑ ተገልጾዋል። ዩኤስ አሜሪካ ካለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ወዲህ ለጦር ኃይሉ ያዋለችው ወጪ ከ 4,5 እስከ 5 ከመቶ ነው።
በቻይና እና በእሥያውያቱ ጎረቤት ሀገራት መካከል በግዛት ይገባኛል ጥያቄ ንትርኩ ከቀጠለ ወዲህ በቻይና ባህር አካባቢ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ዓለም አቀፍ ትኩረት አርፎበታል። ከቻይና ጋ በሚያከራክሩት ደሴቶች መካከል ብዙዎቹ ይገቡናል በሚሉት ጃፓን፡ ቪየትናም እና ፊሊፒንስ ውስጥ ፀረ ቻይና አስተያየት ካለፉት ጊዚያት ወዲህ እየተበራከተ በመምጣቱ ቻይና ቀስ በቀስ ስጋት ሳያድርባት እንዳልቀረ የቦን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሹ ጉ ገምተዋል። ምክንያቱም፡ ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡ የኤኮኖሚ ዕድገቱን የተያያዘችው ቻይና በወቅቱ ለአወዛጋቢዎቹ ግዛቶች እንደምትፈልገው ከለላ ለመስጠት ላትችል ትችል ይሆናል። በዚህም ሰበብ የጦር ኃይሏን ዘመናይ ለማድረጉ ዕቅድ ትኩረት መስጠቷን፡ በተለይ የባህር ኃይሏን ለማስፋፋት የወሰነችበትን መልዕክት ለማስተላለፍ ተነሳስታለች፡ በሌላ አነጋገር፡ በሚቀጥሉት ዓመታት ለጦር ኃይሉ ብዙ ገንዘብ እንደምትመድብ ነው የሚጠበቀው።
ይሁንና፡ የቻይና የጦር ኃይል በጀት ለምን እንደሚውል በትክክል ማወቁ አዳጋች መሆኑን የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ተቋም ተንታኝ ወይዘሮ ናዲን ጎደሀርት አስታውቀዋል።
« ከዚሁ በጀት መካከል አንድ ሦስተኟው ለሰራተኛው ፡ ለተነቃቁ ፕሮዤዎች ማራመጃ እና ለጦር መሣሪያ መግዣ ልታውለው እንደምትችል ይገመታል። »
ሀይ ቻዎ/አርያም ተክሌ
ሸዋዬ ለገሰ